ሩሲያ እና ዩክሬን ስምምነት ላይ ለመድረስ 'መቃረባቸውን' ትራምፕ ተናገሩ

ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሩሲያ እና ዩክሬን ስምምነት ላይ ለመድረስ 'መቃረባቸውን' አስታወቁ።

የትራምፕ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ከተወያዩ ከሰዓታት በኋላ ነው ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት።

"ጥሩ ድርድር" መደረጉን ጠቁመዋል። በድርድሩ ዩክሬን አልተገኘችም።

ሩሲያ እና ዩክሬን በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ ተገናኝተው "ስምምነቱን እንዲያገባድዱ" ትራምፕ ጠይቀዋል።

ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ሩሲያ ላይ "ጫና መደረግ አለበት" ብለዋል።

አሜሪካ ባቀረበችው የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረት ዩክሬን የተወሰኑ ግዛቶቿ በሩሲያ ሥር እንዲሆኑ ትፈቅዳለች።

ሩሲያ የክሬሚያ ቀጣናን በይዞታዋ ሥር እንድታስቀጥል እንደሚፈቅዱ ትራምፕ ተናግረዋል።

ዜሌንስሊ ግን ይህንን ሐሳብ ነቅፈዋል።

ሩሲያ 20 በመቶ የዩክሬንን ግዛት በጦርነቱ አማካይነት በቁጥጥሯ ሥር አድርጋለች።

የትራምፕ መልዕክተኛ እና ፑቲን ሞስኮ ውስጥ ሲገናኙ ለአራተኛ ጊዜ ነው። የፑቲን አማካሪ ዩሪ ዩሽካቭ ውይይቱ "በጣም ጠቃሚ" ነበር ብለዋል።

"በዩክሬን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን በተመለከተም የአሜሪካ እና የሩሲያ ተወካዮች እንዲቀራረቡ በር ከፍቷል" ሲሉም አክለዋል።

ፑቲን ጦርነቱ ከተጀመረ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዜሌንስኪ ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን ባለፈው ሳምንት ገልጸዋል።

ለፋሲካ የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት ለ30 ቀናት የማራዘም ዕቅዶች ነበሩ።

ዜሌንስኪ የክሬሚያ ቀጣናን በሩሲያ እጅ መተው ተቀባይነት የሌለው ነው ብለው ሲከራከሩ ቢቆዩም፤ አሁን ግን ከተኩስ አቁም ስምምነት በኋላ ሌሎች ነጥቦች ላይ መነጋገር እንደሚቻል ገልጸዋል።

ቀጣናውን ለማስመለስ በቂ መሣሪያ እንደሌላቸውም አክለዋል።

አሜሪካ ለተኩስ አቁም ስምምነት ለአውሮፓ ባለሥልጣናት ባቀረበችው እና ሮይተርስ በተመለከተው ዕቅድ እንደተጠቀሰው፣ የዩክሬንን ደኅንነት ማስጠበቅ አንደኛው ግብ ነው።

ለዩክሬን ደኅንነት ማስተማመኛ መስጠት እንዳለ ሆኖ ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅትን (ኔቶ) እንዳትቀላቀል ይደረጋል ተብሏል።

የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ በሩሲያ ይዞታ ሥር ስላሉ የዩክሬን ግዛቶች ውይይት እንደሚጀመር ይህ የተኩስ አቁም ሰነድ ያመለክታል።

"ውይይቱ ሲጠናቀቅ ጥሩ ስምምነት ላይ እንደርሳለን" ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል።

በየሳምንቱ 5,000 ዩክሬናውያን እና ሩሲያውያን የሚሞቱበትን ጦርነት እንደሚያስቆሙ ትራምፕ ገልጸዋል።

አሜሪካ ለምታቀርበው የተኩስ አቁም ስምምነት ዕቅድ በምላሹ የዩክሬንን የከበሩ ማዕድናት እንደምታገኝ ሲገለጽ ቆይቷል።

የአሜሪካው መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ለመገናኘት ሞስኮ በነበሩበት ዕለት ከሩሲያ ከፍተኛ ጄነራሎች አንዱ የሆኑት ያሮስላቭ ሞስካሊክ በዋና ከተማዋ ውስጥ መኪና ላይ በተጠመደ ቦምብ ተገድለዋል።

ሁለቱን አገራት ለማሸማገል ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ቢቀጥሉም ሩሲያ በዩክሬን የምትፈጽመው ጥቃት ባለፈው ሳምንትንም ቀጥሏል።