በፍልስጤም የተንቀሳቃሽ ትምህርት ቤት ዲዛይን ውድድር 'ያሸነፉት' ኢትዮጵያውያን አርክቴክቶች

ዳንኤል ዋጁ፣ ቢኒያም በዕውቀቱ እና ፍሬዘር አብረሃ ይባላሉ። 30 እንኳ አልደፈኑም።
ከኪነ ሕንጻ ትምህርት ቤት የተመረቁበት ዲግሪ'ንኳ ቀለሙ አልደረቀም።
ዓለም አቀፍ ውድድር ማሸነፋቸው ዜና ያደረገውም ይኸው ነው።
ሦስቱም እጃቸውን ያፍታቱት በታዋቂው 'አለበል ደስታ አርክቴክና አማካሪ' ቢሮ ነው።
ጎምቱው ነዳፊ አለበል "ብዙ ነገር ገልጦልናል" ይላሉ።የሙያ አባታቸው ነው።
ፍሬዘር እና ቢኒያም አሁንም እዚያው ነው የሚሠሩት። ቢሯቸው ብሥራተ ገብኤል ነው የሚገኘው። ከሥራ ወጥተው ይገናኛሉ።
ሦስቱም ቀልድ እና ዋዛ ይወዳሉ። እርስ በእርስ ሲቀላለዱ በጭራሽ ለቁም ነገር ጊዜ ያላቸው አይመስሉም።
ከመካኒሳ ቢሮ እንደወጡ በር'ረው ሜክሲኮ።
እዚያ የሚያዘወትሩት አንድ ካፌ አለ። ዳንኤልን ይጠብቁታል።እሱ ከሌላ ቦታ ነው የሚመጣው።
"ሁልጊዜም ሜክሲኮ ዋቢ ሸበሌ ሥር የሚገኘው ካፌ ነው የምንገናኘው" ይላል።
ለምን ያን ካፌ እንደሚመርጡት ሲጠየቁ ሦስቱም ተመሳሳይ መልስ ይሰጣሉ።
"የድሮ ሆቴል ስለሆነ አስተናጋጆቹ 10 ጊዜ እዘዙ እያሉ አይጨቀጭቁንም።"
ብዙውን ጊዜ ግማሽ ሊትር ውሃ ነው የሚያዙት። ኬክ ለማዘዝ የሚሆን 'ቻፓ' የለማ።
ቅመም የበዛበት ቀጭን ሻይ በሎሚ አ'ዘው፣ 10 ጊዜ እያማሰሉ፣ ለ10 ሰዓት ተቀምጠው፣ 10 ብር ከፍለው የሚወጡ ዓይነት ደንበኞች ናቸው።ምንም ማድረግ አይቻልም።
እና እነ ቢኒ፣ እዚህ ካፌ ዘለግ ላለ ሰዓት ቁጭ ብለው ወሬ ያወራሉ።
ሦስቱም ወረኞች ናቸው፤ በእርግጥ ወሬያቸው ሁሉ ግን ስለ ንድፍ ነው። ስለ ኪነ ሕንጻ ነው። ስለ መስመሮች፣ማገሮች እና ምሰሶዎች አወቃቀር ነው።
ወደ ኢንተርኔት ከዘለቁም ዓለም አቀፍ የኪነ ሕንጻ ውድድርን ለማደን ነው እንጂ ለሌላ አይደለም። በተለይ ለኪነ ሕንጻ ባለሙያዎች መረጃ ለሚሰጠው 'አርክስቶርሚንግ' የሚባለው ድረ ገጽ ቀንደኛ ደንበኛ ናቸው።
ከስንትና ስንት ሙከራ በኋላ ተሳካላቸው።
በፍልስጤም አገር፣ በዌስት ባንክ፣ 'ካን አል አህማር' መንደር ለአደጋ ጊዜ የሚሆን ተንቀሳቃሽ ትምህርት ቤት የመንደፍ ዓለም አቀፍ ውድድር ተሳትፈው አሸነፉ።
እርግጥ አንደኛ አልወጡም። አንደኛ የወጣው ጣሊያናዊ ነው።ጣሊያኖች ንድፍ ላይ ብርቱ ናቸው። የብር ሜዳሊያውን ግን ወደ ኢትዮጵያ አምጥተውታል።

ውድድሩ ያን ያህል ከባድ ነበር?
እርግጥ ነው በዚህ ዘመን ብዙ ዓይነት የሰፈር ውድድር አለ።ድል ሁሉ ድል አይደለም።
እነ ቢኒያም የተሳተፉበት ውድድር ግን የዋዛ ውድድር አልነበረም።
231 የኪነ ሕንጻ ወጣት ነዳፊዎች ከመላው ዓለም ተሳትፈውበታል።ቻይናውያን፣ ኢራናውያን፣ አሜሪካውያን፣ ሩሲያውያን...። ነገሩ 'የነዳፊያን ጦርነት' ይመስላል።
የውድድሩን ክብደት አንዱ ማሳያ የተወዳዳሪዎች ቁጥር እና ስብጥር ብቻ አይደለም። የዳኞቹ ማንነት ብዙ ይናገራል።
ቢኒያም እንዲህ ይላል፤ "ለምሳሌ የመሐል ዳኛው አሌሃንድሮ አራቬና ነው፤ አስበኸዋል በእርሱ መደነቅ?"።
ማን ነው ደግሞ አሌሃንድሮ?
ቺሊያዊ ነዳፊ ነው። በኪነ ሕንጻ 'ሎሬት' የሚባል ሰው ነው።
በአውሮፓውያኑ 2016 የፕሪትዝከር ኪነ ሕንጻ ሽልማት አሸናፊ ነው።
ፕሪትዝከር ሽልማት (Pritzker Prize) የኪነ ሕንጻ 'የኖቤል ሽልማት' እንደማለት ነው።
እርሱ የፍርድ ሸንጎው (Jury) የመሀል ዳኛ ይሁን እንጂ ''የመስመር ዳኞችም'' በዘርፉ 'ከባድ ሚዛን' የሚባሉ ናቸው።
እነ ሌዝሊ ሎኮ፣ ቶሲን ኦሺኖዎ፣ ሎትፊ ሐማዲ፣ ዴቪድ ሳንደርሰን . . . በሙያው ያሉ ያውቋቸዋል።
በዚህ ውድድር ነው እንግዲህ እነ ቢኒያም፣ ዳኒ እና ፍሬዘር 'የብር ሜዳሊያውን' ወደ ኢትዮጵያ ያመጡት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"ከማሸነፋችን በፊት ብዙ ጊዜ ተሸንፈናል'
በአገራችን ወጣት ነዳፊዎችን ከቁም ነገር የሚጥፍ ብዙ ሰው የለም።
በወጣቶች የሚያምን ደንበኛ ማግኘት ብርቅ ነው። ለወጣት ነዳፊዎች ብዙ ሥራ የለም።
በእነሱ ቋንቋ 'ወፍ የለም'።
ይህ ነገር እነ ቢኒያምን ወደ ዓለም አቀፍ ውድድር ፊታቸውን እንዲያዞሩ ሳያደርግ አልቀረም። ቀላል ግን አልነበረም።
በዓለም አቀፍ መድረክ ያለው ትግል መራራ ሆኖ ነው ያገኙት።
"ከፍልስጤሙ ውድድር በፊት ብዙ ውድድር ተወዳድረን ወድቀናል" ይላሉ።
እነ ቢኒያም ጥሩነቱ ወድቀው አይቀሩም። አቧራቸውን አራግፈው እየተቀላለዱ ይነሳሉ። አንድ ጊዜ ለሁለት፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ለሦስት ሆነው እየተቧደኑ ይታገላሉ።
ለምሳሌ በሴኔጋል ለሚገነባ የሕጻናት መንደር ከአራት ዓመት በፊት ተወዳድረው ነበር። አልቀናቸውም።
ከዚያ ደግሞ በሞዛምፒክ የሴቶች ትምህርት ቤት ንድፍ ውድድር ላይ ተሳተፉ። ስማቸውን ያነሳም የለም።
ለዛምቢያ የስደተኞች ማዕከል ንድፍ ሥራ ተወዳደሩ፤ የመጀመሪያውን ዙር ቢያልፉም አልተመረጡም።
እጅ ሳይሰጡ ፖላንድ የተዘጋጀ የቱሪስት ማማ (Watching Tower) ንድፍ ሞከሩ። ከቁብ የቆጠራቸው አልነበረም።
ለአምስተኛ ጊዜ ሕንድ አገር የማኅበረሰብ ማዕከል ግንባታ ሞከሩ። አልሆነም።
ከብዙ ጥረት በኋላ ነበር የፍልስጤምን ተንቀሳቃሽ ትምህርት ቤት ዲዛይን የሞከሩት።

የፎቶው ባለመብት, Schools for Palestine page
ውድድሩ ምን ነበር?
ሐሳቡ በፍልስጤም፣ በዌስት ባንክ፣ ካን አል አሕማር በሚባል ሰፈር ለአደጋ ጊዜ የሚሆን ትምህርት ቤት ዲዛይን ማቅረብ እንደሆነ ገልጸናል።
እንዴት ዓይነት ትምህርት ቤት ይሁን? እንደ ድግስ ድንኳን የሚተከል- የሚነቀል?
ንድፉ ምን ይምሰል የሚለው ጥናት ብቻውን ሦስት ወር ፈጅቶባቸዋል።
እርሳስ ከመቅረጻቸው በፊት አእምሯቸውን መቅረጽ ነበረባቸው።
ፍልስጤምን ማጥናት አስፈለጋቸው። የአካባቢውን መስተጋብር፣ መጠነኛ ታሪክ፣ ባሕልና አኗኗር ለማወቅ ብዙ አነበቡ።
ይህን ለማጥናት የተገደዱት በራስ ፍላጎት ሳይሆን ለንድፉ እንዲረዳቸው ነው።
በጥናቱ ያገኟቸው ጥሬ ሐቆች ግን አስነገጧቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ ዓይን ገላጭ ነበሩ።
"አንዳንድ ነገሮችን ስትፈትሽ፣ በፈታኝ ሁኔታ ነው ፍልስጤሞችን የሚያኖሯቸው" ይላል ዳንኤል።
ሌሎች ነገሮች ሚዲያ ስለ ፍልስጤም ከሚያወራው በተቃራኒ ሆነው አገኟቸው።
ለምሳሌ ፍልስጤም በጨርቅ ምርት እና በንግድ በአንድ ወቅት ገናና እንደነበረች አወቁ።በሆነ ዘመን ፍልስጤማውያን ከግመል እና ከፍየል ፀጉር ጨርቅ ያመርቱ ነበር።አምርተው ለዓለም ገበያ ያቀርቡ ነበር።
ጎዝ (Gauze) የሚባለው የሕክምና ፋሻ የተፈጠረው በፍልስጤም ነው፤ በ13ኛ ክፍለ ዘመን። 'ጎዝ' የሚለው የእንግሊዝኛ ስሙ ጋዛ ከሚለው የመጣ መሆኑን አወቁ።

የፎቶው ባለመብት, AFP
እነ ቢኒያም የፍልስጤሞችን አኗኗር ሲያጠኑ ሌላ ያስገረማቸው እስራኤል በኃይል በያዘቻቸው ግዛቶች (ለምሳሌ ዌስት ባንክ) ፍልስጤማውያን የሚኖሩበት አሁናዊ ሁኔታ ነው።
"ፍልስጤሞች ቤቶቻቸውን በምን ዲዛይን እና በምን ዓይነት ቁስ መሥራት እንዳለባቸው የምትወስንላቸው እስራኤል ናት።"
ብረትን ለኮንስትራክሽን መጠቀም አይችሉም። ክልከላው መሠረት አለው። ፍልስጤሞች ኋላ ብረቱን ለጦር መሣሪያ እንዳይጠቀሙበት በሚል ነው።
የነ ቢኒያም ተንቀሳቃሽ ትምህርት ቤት ዲዛይን ብረትን ሊጠቀም እንደማይችል ተረዱ። ፌሮን ከዲዛይናቸው ውጭ ማድረግ ነበረባቸው።
"የግንባታ ዕቃዎች ማዕቀብ ስላለ ዲዛይናችን ላይ 'ኢኖቬቲቭ' እንድንሆን አስገድዶናል" በማለት ፈጠራን ሌላ አማራጭ መፈለግ እንዳስፈለጋቸው ዳንኤል ይናገራል።
ሌላው ያስገረማች የጣሪያ ቀለም ጉዳይ ነው።
"ፍልስጤማውያን ከእስራኤላውያን ጋር በሚኖሩባቸው ሰፈሮች የፍልስጤማውያን ቤቶች ጣሪያ ቀይ ቀለም መቀባት አይችሉም" ይላል ዳንኤል።
ይህ የሚደረገው ችግር ቢፈጠር ፍልስጤሞችን ከአየር ላይ ለይቶ ለመምታት እንዲረዳ ነው።
እነዚህ ዝርዝር ጥናቶች የዲዛይኑን ጽንሰ ሐሳብ ለማጎልበት ተጠቀሙባቸው። ተንቀሳቃሽ ትምህርት ቤቱን ለመገንባት የሚውሉ ቁሳቁሶችም በዚህ ጥናት ተለዩ።
"ትምህርት ቤቱ ቶሎ ቶሎ ተነቃቅሎ ወደሌላ ቦታ የሚወሰድ መሆን አለበት። ወደሌላ ቦታ ለማንቀሳቀስ ቀላል መሆን አለበት። ከተነቃቀለ በኋለ ደግሞ ቶሎ መገጣጠም መቻል አለበት። በአጭሩ ፍልስጤማውያንንና አካባቢያቸውን መምሰል አለበት።"
"የጨርቅ ሕንጻ" ይሉታል እነ ፍሬዘር፤ በእንጨት የተዋቀረ፣ ግን ደግሞ እንደ አኮርዲዮን ሙዚቃ መሣሪያ የሚሰበሰብ፣ ተመሳሳይ መጠነ ዙርያ ያላቸው (Modular) መማሪያ ክፍሎች።
በሌላ አነጋገር ትምህርተ ቤቱ ጦርነት ሲጀመር ልክ እንደ ቦርሳ በፍጥነት ተሸክፎ የሚወሰድ ሊሆን ይገባል።

የፎቶው ባለመብት, Schoolforpalestine page
"አርክቴክት እንድሆን ያነሳሳኝ ግንበኛ ነው"
ሦስቱ ወጣቶች ኪነ ሕንጻን ለመምረጣቸው የየራሳቸው ምክንያት ነበራቸው።
ዳንኤል ትዝ የሚለው ከልጅነቱ ጀምሮ የሥዕል ዝንባሌ ነበረው። ክረምት ሲመጣ አዲስ ደብተር ያዘጋጃል።
ወንበር፣ ጠረጴዛ፣ መወጣጫ ደረጃ ሊስልባቸው።
ሁለተኛ ደረጃ ሲደርስ "ኪነ ሕንጻ'' የሚባል ለእሱ በልኩ የተሰፋ የትምህርት ዘርፍ መኖሩን አወቀ።
"አርክቴክቸር ባልማር ወደ ስፔስ ሳይንስ ዘርፍ የማዘነብል ይመስለኛል" ይላል።
ፍሬዘር ደግሞ 12ኛ ክፍል ሲደርስ ነው በደንብ ነገሩ የተገለጠለት።
የቅርብ ጓደኛው አርክቴክቸር ይማር ስለነበር በዚያው ተሳበ። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሲገባ አርክቴክቸር መግባት ፈተና እንደሆነ ሲያውቅ ደነገጠ። ኪነ ሕንጻ ባይሳካልኝስ? ምን ይውጠኛል ብሎ አሰበ። መጠባበቂያ የሚሆን ሌላ የትምህርት ዘርፍ አስፈለገው።
ዩኒቨርስቲ ሳሉ አርክቴክት ዘገየ ኪነ ሕንጻን ለተማሪዎች ሲያስተዋውቅ ፍሬዘር ልቡ ሸፈተ።
ተፈትኖ የሚወደውን ትምህርት ተማረ። "አርክቴክት ባልሆን ምናልባት ሜካኒካል ኢንጂነር እሆን ነበር" ይላል።
የቢኒያም ከሁለቱ ይለያል። ድሮ ሕጻን እያለ ቤታቸውን ሊገነባ የሚመጣ ግንበኛ ነበር። አናጺም አብሮት ነበር። እነሱ ናቸው 'ንሸጣ' ውስጥ የከተቱት።
"ግንበኛ እና አናጺውን በጥያቄ አደርቃቸው ነበር" ይላል ልጅነቱን ሲያስታውስ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"ያጨቃጭቅ የነበረው ሒሳብ ማን ይክፈል የሚለው ነው"
ተግባብቶ በጋራ መሥራት ቀላል አይደለም። በተለይ የፈጠራ ሥራን በደቦ መሥራት ፈታኝ ነው።
ሁሉም ሰው የራሱ ፈጠራ የላቀ ይመስለዋል። እነ ቢኒያም እንዴት ተወጡት?
ብዙ ይጨቃጨቁ እንደነበር አይክዱም፤ "ይሄ ነገር ትምህርት ቤት እያለን ጀምሮ የነበረ ነው" ይላል ቢኒያም።
በሂደት ግን እየበሰሉ መጡ። ዛሬ ተጨቃጭቀው የተለያዩበትን ሐሳብ ነገ ጭራሽ ቦታ ተቀያይረው 'ልክ ነበርክ' መባባል መጣ።
"ቁም ነገሩ ጭቅጭቁ የኢጎ ነው ወይስ የሐሳብ የሚለው ነው" ይላል ፍሬዘር።
ቢኒያም ደግሞ፣ "እንዲያውም በጣም ያጨቃጭቀን የነበረው ከዲዛይን ሐሳብ ይልቅ የሻይ ሒሳብ ማን ይክፈል የሚለው ነበር" ሲል ይቀልዳል።
"ውጤቱን ስሰማ ቢሮ ውስጥ ጮኽኩኝ''
አንዳቸውም ይወዳደሩ እንጂ እናሸንፋለን አላሉም ነበር። ቢሆንም ግን ተስፋ ማድረጋቸው አልቀረም።
ዳንኤል ውጤቱ ይፋ በሚሆንበት ሰዓት ለክፋቱ ስልኩ ባትሪው ተሟጠጠ። ወደ ጉዳዩ ሄዶ፣ ቢሮ ገብቶ፣ ስልኩን ኃይል ቀልቦ ሲመለከት ያየውን ማመን አቃተው።
"አላስቻለኝም፤ ቢሮ ውስጥ ጮኽኩኝ" ይላል።
መጀመሪያ ደውሎ ዜናውን ያበሰረው ታዲያ ላፕቶፕ ላዋሰው ጓደኛው ነበር፤ለባለውለታው።
ፍሬዘር ደግሞ ውጤት በሚገለጽበት ወቅት ወደ ቢሾፍቱ እየተጓዘ ነበር። ባልደረባው ቢኒያም ነው ደውሎ የነገረው። "ሚኒባስ ውስጥ ለመጮኽ ፈለ'ኩ፤ ግን አልተመቸኝም - የተሳፋሪ ትዝብት ፈራሁ" ይላል።
ቢኒያም በበኩሉ አለወትሮው ድረ ገጹ ላይ አፍጦ ነው የዋለው፤ ያን ቀን። አንደኛ ከወጣው ጣሊያናዊው ቀጥሎ ስሙን ሲመለከት ግን አላመነም።
ዳኞቹ የሰጡትን አስተያየት ሲያነብ ይበልጥ ተነካ።
በተለይ የዓለም የኪነ ሕንጻ ሎሬት የሚባለው አሌሃንድሮ አራቬና ስለ ሥራቸው የሰጠውን አስተያየት ሲያነብ "ስሜታዊ ሆኜ አለቀስኩ" ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Biniam
አሌሃንድሮ ኢትዮጵያውያኑ ወጣቶች ስለሠሩት የትምህርት ቤት ንድፍ አስተያየት ሲሰጥ ". . . ሰላማዊ ዓውድ የሚያሰፍን፣ በነውጥ ውስጥ ያሉ ተማሪዎችን እርግት የሚያደርግ . . ." ሲል ጽፏል።
''የእኛ ዲዛይን ጽንሰ ሐሳብም ያን መፍጠር ነበር፤ በቀላል ቁሳቁስ እና በጨርቅ የሚሠራ፣ ሲያስፈልግ የሚሸከፍ ትምህርት ቤት ነው የነደፍነው" ይላሉ ቢኒያም።
ሐሳቡን ወይም ንሸጣውን (Inspiration) ያገኙት በደዊይን ከሚባሉ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ የመኖር የሕይወት ዘይቤ ከነበራቸው እና ጥንት ፍልስጤም ምድር ከኖሩ ጎሳዎች ነው።
እነ ቢኒያምን አሁን ታላቁ አሌሃንድሮ ብቻ ሳይሆን ወላጆቻቸው ኮርተውባቸዋል። ወላጆቻቸው ምን እንደሠሩ በቅጡ ባይረዱም። "'ልጄ ትልቅ ደረጃ ደረሰ' ይሉናል" ይላሉ፤ ሦስቱም።
ዝናቸው ግን ከቤተሰብ ብዙ ርቀት አልሄደም። እንደእነሱ ወጣት በሆኑ ነዳፊያን ዘንድ ግን ገነዋል።
"ሰሞኑን ወጣት አርክቴክቶች እየመጡ ያማክሩናል፣ 'መንገዱን ለእኛም አሳዩን' ይሉናል" ይላል ፍሬዘር።
ቢቢሲ፣"ድሉ ምን አዲስ በር ከፈተላችሁ?" ብሎ ጠይቋቸው ነበር፤ ወጣቶቹን።
"ምንም" አሉና ዝም አሉ።
ቢኒያም ግን ለአፍታ አስቦ እንዲህ አለ፤ "አዲስ በር አልከፈተልን ይሆናል፤የራሳችንን የውስጥ በር ግን ከፍቶልናል።"
አሁን በራሳቸው ማመን ጀምረዋል። ቢኒያም "የውስጥ በር ተከፈተልን" ያለውም ይህንኑ ነው።
የ'ከቤት እስከ ከተማ'' የተሰኘው የሬዲዮ ፕሮግራም አሰናጅ እና የኪነ ሕንጻ መምህር አርክቴክት ማኅደር ገብረመድኅን ወጣቶቹን እንግዳ ባደረገበት አንድ መሰናዶው ላይ እንዲህ ሲል አድናቆቱን ገልጾላቸዋል።
"በዳኝነት የተሰየሙት ስመ ጥር የዓለም አርክቴክቶች አእምሮ ውስጥ፣ ችሎታ ያላቸው 'ወጣት ኢትዮጵያውያን አርክቴክቶች' አሉ ብለው እንዲያስቡ ማድረግ በራሱ ቀላል (አገራዊ ድል) አይደለም።"
ልክ ሳይሆን አይቀርም።












