ዕድገት በኅብረት ዘመቻ፡ የሦስቱ ጓደኛሞች የ50 ዓመታት ትዝታ

የሰላ ድንጋይ ዘማቾች

የፎቶው ባለመብት, KIDIST

የምስሉ መግለጫ, የሰላ ድንጋይ ዘማቾች

ወ/ሮ አፀደ ወልደሚካኤል፣ ወ/ሮ ቅድስት በለጠ እና ዶ/ር ጌታቸው እንዳላማው አፍላ ወጣት ሳሉ ነው የተዋወቁት።

በአሥራዎቹ መጨረሻ ቢሆናቸው ነው ዕድገት በኅብረት ሲዘምቱ። ከ50 ዓመት በኋላ ባለፈው ቅዳሜ (ሚያዝያ 4/2017 ዓ.ም.) ተገናኙ።

ከመካከላቸው ግማሾቹ ሞተዋል። ግማሾቹ ሸብተዋል። ግማሾቹ አብረው ኬክ ቆርሰዋል።

የያኔዎቹ ሦስት ወጣቶች የተመደቡት በሰሜን ሸዋ፣ ሰላ ድንጋይ ከተማ ነበር። በእነሱ ጣቢያ የተመደቡት ዘማቾች 130 ይደርሳሉ።

ከሁለት ዓመት የዕድገት በኅብረት ዘመቻ በኋላ በተለያየ የሕይወት አቅጣጫ ተበተኑ።

ከ15 ዓመታት በፊት የሰላ ድንጋይ ዘማቾች ዳግመኛ ተገናኙ። ወደ 30 ገደማ የሚሆኑት ተሰባስበው ይጠያየቁ ጀመር።

አሁንም ድረስ 15 ያህሉ ይገናኛሉ። ዘንድሮ ደግሞ 50ኛ ዓመታቸውን በፊንፊኔ አዳራሽ አክብረዋል።

በ1966 ዓ.ም. ነሐሴ ላይ ነበር ብሔራዊ የዕድገት በኅብረት የዕውቀት እና የሥራ ዘመቻ የታወጀው።

ከ10ኛ ክፍል እስከ ዩኒቨርስቲ ያሉ ተማሪዎች እና መምህራን ናቸው በዘመቻው የተካተቱት።

ዘመቻው በይፋ ታኅሣሥ 12 ቀን 1967 ዓ. ም. ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም በተገኙበት በጃንሜዳ ተጀምሯል።

ወደ 48 ሺህ ገደማ ዘማቾች መሰማራቸውን የታሪክ መዛግብት ያወሳሉ።

ጥላሁን ገሠሠም ዘፍኖላቸዋል። ለነገሩ ጥላሁን ያልዘፈነበት ጉዳይ ይኖር ይሆን?

"ለዕድገት በኅብረት እንዝመት

ለዕድገት በኅብረት እንዝመት

ወንድና ሴት ሳንል በአንድነት

ስንፍና የለብን አያሻም እረፍት

እንገስግስ ወደፊት ለዕድገት በኅብረት"

ታምራት ሞላም ለዘማቾች መልካም ምኞቱን በዜማ ገልጾ ነበር።

"በሕይወት ግቡ በሕይወት

ዘመቻ የምትሄዱ ለዕድገት በኅብረት

ዕውቀት የጠማውን ከርታታ ገበሬ

እንድትመግቡት የጥበብብን ፍሬ

እዚህ ላይ ነውና የለውጡ ቁም ነገር

ደንቆሮ እንዲሰማ ዲዳው እንዲናገር"

ጥላዬ ጨዋቃ ደግሞ "አሸወይና ማለቴ ለዘማቿ እህቴ" ሲል ሴት ዘማቾችን አሞግሷል።

"ለኢትዮጵያ ትቅደም አባሪ ለሆንሽው

ለዕድገት በኅብረት ቀድመሽ ለዘመትሽው

ለወገንሽ መድኅን አንቺን የሰዋሽው

ታሪክ ነው ቤዛ ነው ለትውልድ የተውሽው. . ."

የዕድገት በኅብረት ዘማቾች በእነዚህ ሙዚቃዎች እና በኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ተስፋ ወደየክፍለ አገሩ ከተሸኙ 50 ዓመት ሞልቷቸዋል።

ዓመታት በዓመታት ላይ ተደራርበው ያንን ዘመን የራቀ ቢያስመስሉትም ወ/ሮ አፀደ፣ ወ/ሮ ቅድስት እና ዶ/ር ጌታቸው በትዝታ ጋሪ ወደኋላ ይመልሱናል።

ደስታ እና ፍርሃት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዛሬ 50 ዓመት ወ/ሮ አፀደ ዕድገት በኅብረት ሲዘምቱ 20 ዓመት ቢሆናቸው ነው።

የተወለዱት ደብረ ሲና ነው። ለዘመቻ የተመደቡበትን ሰላ ድንጋይ በስም ይሰሙት ነበር እንጂ ሄደው አያውቁም።

በራድዮ የዘማቾች ስም ዝርዝር እና የት እንደተመደቡ ተነገረ። ወ/ሮ አፀደ ማስታወቂያው ሲነገር የዘመድ ለቅሶ ላይ ስለነበሩ አልሰሙም።

እናታቸው ማስታወቂያውን ሰምተው ለዘመቻ የሚሆን ልብስ አዘጋጅተውላቸው ደብረ ብርሃን ወስደው አቀበሏቸው።

ወ/ሮ አፀደ ብቸኛ ልጅ ናቸው። ከቤተሰብ ተለይቶ መዝመት ቀላል አልነበረም። ዘመቻው ለእሳቸው አጓጊም፣ አስፈሪም ነበር።

"ዘምተን ምን እንደምናደርግ ምኑን አወቅነው ብለሽ። ያው የልጅነት ነገር እንደ ሽርሽርም ትቆጥሪዋለሽ" ሲሉ ያስታውሳሉ።

ሰላ ድንጋይ ሲደርሱ ነበር ኃላፊነታቸው ምን እንደሆነ የተነገራቸው። ወታደራዊ አዝማቾች እና ሲቪል አዝማቾች ናቸው ይህንን የነገሯቸው።

ወታደራዊ አዝማቾች የክብር ዘበኛ ወታደሮች ናቸው። ዘማቾችን ይጠብቃሉ። ሲቪል አዝማቾች ደግሞ የሁለተኛ ደረጃና የዩኒቨርስቲ መምህራን ናቸው። ለአርሶ አደሩ ስለሚሰጠው ትምህርት መመሪያ ይሰጣሉ።

ወ/ሮ አፀደ ቤተሰባቸውን በስልክ ተሰናብተው ወደ ሰላ ድንጋይ አቀኑ።

"በአካል ሳልሰናበት በመሄዴ ሆዴን ባር ባር አለኝ . . . ደስታም ግን አለው፤ በቃ የተደበላለቀ ስሜት።"

አብረዋቸው ከተማሩ ጓደኞቻቸው ጋር አብሮ መዝመት በጣም አጓጓቸው።

"አብረውሽ ከተማሩ ጓደኞችሽ ጋር መዝመት ጭፈራ ነው፤ ደስታ ነው። ወዴት ይሆን የምንሄደው የሚለውም ትንሽ ያስፈራል። የቤቱ የመጀመሪያም የመጨረሻም ልጅ ስለሆንኩ እናቴ ትንሽ ተቸግራ ነበር።"

የዘመቻ ቀን ሰዓቱንም ሰከንዱንም ሳያሳልፉ ሻንጣቸውን ይዘው በዘማቾች መነሻ ቦታ ተገኙ።

ሰላ ድንጋይ ሲገቡ የተደረገላቸው አቀባበል ደማቅ ነበር።

"ገበሬ ማኅበሩ ተሰልፎ፣ ሴቱ ወንዱ ወጥቶ ጠበቁን። እልልል ብለው፤ ጨፍረው ነው የተቀበሉን። በጣም ነው ደስ ያለን፤ አበረታታን።"

የወንዶች እና የሴቶች ዘማቾች እንዲሁም የአዝማቾች ማረፊያ ተዘጋጅቶ ጠበቃቸው።

ኃላፊነታቸው ማንበብ እና መጻፍ እንዲሁም የሒሳብ ስሌቶች ማስተማር ብቻ አልነበረም።

"አፈር መሬት የሚያስበላ ቁልቁለትና ዳገት እየወጣን ምንጭ እናጎለብታን። ሠርቶ ማሳያ ውስጥ ቆፍረን ተክለን ለገበሬው እናሳያለን" ሲሉ ያስታውሱታል።

በዕድገት በኅብረት ዘመቻ የገበሬ ማኅበር አደራጅተዋል። ገበያ ዞረው እየቃኙ ለአርሶ አደሩ ምክር ይለግሱ ነበር።

አንድ ቀን በዘማቾች ሕይወት

ጠዋት ማልደው ነው የሚነሱት። ወጥ ቤት ተረኛ የሆኑት በምግብ ዝግጅት ያግዛሉ።

የፊልድ ተረኞች ከዘማቾች ማቆያ ውጭ ኃላፊነቶችን ይወጣሉ።

የሰላ ድንጋይ ዘማቾች በሁለት ንዑስ ጣቢያ፣ በጣርማ በር እና በሳሲት ከተሞች ተከፍለው ነበር።

ወ/ሮ አፀደ የመሠረተ ትምህርት ተጠሪ ነበሩ።

ከሰላ ድንጋይ ተነስተው በየቀኑ በእግራቸው እስከ ደብረ ምጥማቅ ማርያም ይጓዛሉ። ከሦስት ሰዓታት በላይ የሚወስድ ከባድ መንገድ ነው።

በቦታው ካለ አንድ ሎንችን ውጪ መኪና የለም።

የትኛው ቀበሌ ገበሬ ማኅበር እንደሚሄዱ የሚነገራቸው ማታ ነው። ጠዋት ይሰማራሉ።

"ምግብ እንደልብ ነው። የፈለግነውን ያህል በልተን እንሄዳለን። እዚያ ውለን እንገባለን።"

አካባቢው ወጣ ገባ ስለሆነ "ደም ተፍተን ወጥተን፣ ደም ተፍተን ነው የምንወርደው" ሲሉ ያስታውሱታል።

ግን ፈተናውን በሳቅ እና በጨዋታ ነበር የሚያሳልፉት። "በሳቅ፣ በጨዋታ፣ በግርግር፣ በሆታ እና እርስ በርስ በመጓተት እናልፈው ነበር" ይላሉ።

የሰላ ድንጋይ ዘማቾች

የፎቶው ባለመብት, KIDIST

ሽፍታው

ዘማቾቹ በነበሩበት አካባቢ አንድ ታዋቂ ሽፍታ ነበር። በጣም የሚፈራ።

ቁምጣውን ለብሶ፣ ጎፈሬውን አበጥሮ፣ መሣሪያውን አንግቶ ይንጎማለላል። የአካባቢው ነዋሪዎች ቢፈሩትም ሽፍታው ከዕድገት በኅብረት ዘማቾች ጋር በቀላሉ ተወዳጀ።

"ስሙን ረሳሁት እንጂ በጣም፣ በጣም የታወቀ ሽፍታ ነበር። ከእኛ ጋር ሲገናኝ ግን በሰላማዊ መንገድ ነበር . . . ያኔ ጊዜውም ገራገር ነበር" ይላሉ ወ/ሮ አፀደ።

በእርግጥ በተለያዩ አካባቢዎች ይንቀሳቀሱ የነበሩ ሽፍቶች ዘማቾች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ዘማቾች ይናገራሉ።

የሰላ ድንጋይ ዘማቾች

የፎቶው ባለመብት, KIDIST

'ሂድን' ዶርም

ዘማቾቹ ለእያንዳንዱ መኝታ ክፍል እና ለዘማቾችም ቅጽል ስም ይሰጡ ነበር። ወ/ሮ አፀደ የነበሩበት 'ሂድን ዶርም' ተባለ።

ትልቅ አዳራሽ ውስጥ ባለ መኝታ ክፍል ውስጥ ስለሚገኙ ነበር 'ሂድን' ብለው ስም የሰጡት።

አበጋዝ ዶርም፣ ግድንግድ ዶርም፣ ማዘር ዶርም. . . ያሏቸውን ዶርሞችንም ያስታውሷቸዋል።

በዶርሙ በየቀኑ ፋኖስ የመወልወል ኃላፊነት ይሰጣቸዋል። ተረኛ ዘማች ፋኖስ ሳትወለውል ከቀረች ትቀጣላች።

"ቅጣቷ ምን መሰለሽ? በልተን የተረፈንን ከራሷ ምግብ ጋር አድርገን ሙሉውን እንድትጨርስ እናደርጋለን። ውሃም እንሰጣትና ጨርሰሽ ጠጪ እንላታለን። በልታ እና ጠጥታ ካልጨረሰች አምስታችንም በትራስ እንደበድባታለን።"

ሕይወት ዶርም ውስጥ እና ከዶርም ውጪም በትውስታ የተሞላ ነው።

ሜዳ ላይ እና ዛፍ ሥር ነበር የሚያስተምሩት።

"እንደ እናንተ ክፍል ውስጥ'ኮ አልነበረም ትምህርቱ፤ ትልልቅ ዛፍ ሥር ነበር። በቃ እዚያው ስንጯጯህ እንውላለን።"

አርሶ አደሮቹ ትምህርቱ ደስ ቢላቸውም ከግብርና፣ ከቤት ሥራ፣ ከከብት ጥበቃ መስተጓጎላቸው አንዳንዴም ቅር ያሰኛቸዋል።

የሰላ ድንጋይ ዘማቾች

የፎቶው ባለመብት, KIDIST

'ዘማቾች ተቃጠሉ'

ዘማቾቹ ሰላ ድንጋይ ሳሉ ዐቢይ ፆም ገባ። በዚያን ጊዜዋ ኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ሃይማኖት 'ቢነቀፍም' የአካባቢው ማኅበረሰብ ግን በፆም አይደራደርም።

ታዲያ ወጣት ዘማቾች ሌሊት ተነስተው ሥጋ ጠበሱ። ሽታው መንደሩን አወደው። የአካባቢው ነዋሪ ደንግጦ ተነሳ።

"ዘማች ልጆቻችን በእንቅልፍ ልባቸው ተቃጠሉ ብለው ወጡ። ሲመጡ ሥጋ ጠብሰው እየበሉ አገኟቸው" ሲሉ ወ/ሮ አፀደ ያስታውሳሉ።

በአካባቢው ያኔ እንቁላል፣ ቂቤ እና የቀንድ ከብት ርካሽ ስለነበር እንደልባቸው ጥሩ ምግብ እያዘጋጁ ይመገቡ ነበር።

የሰላ ድንጋይ ዘማቾች

የፎቶው ባለመብት, KIDIST

'የታጨሁት ዘመቻ ላይ ነው'

በወቅቱ በዘማቾች መካከል የፍቅር ግንኙነት በይፋ ባይፈቀድም፣ የፍቅር ወዳጅነት የመሠረቱ እና የተጋቡም አሉ።

የወ/ሮ አፀደ ጓደኛ የሆነች ዘማች እጮኛ እና የወ/ሮ አፀደ የአሁኑ ባለቤታቸው እርሻ ሚኒስቴር (የአሁኑ ግብርና ሚኒስቴር) ነበር የሚሠሩት።

የጓደኛቸው እጮኛ ለጥየቃ ሰላ ድንጋይ ሲሄድ የወ/ሮ አፀደ የአሁኑ ባለቤትም አብሮ ይሄድ ነበር።

"ሲመጣ ለካ ያየኛል። እኔ ነገሬም አላልኩም . . . በኋላ ደብረ ብርሃን በጋራ በምናውቀው ሰው አማካይነት ተገናኘን። ከዚያ ተዋወቅን፤ ኮተቱን ይዞ መጣ። በቃ፤ እህል ውሃ ሆነ፣ ተጋባን።"

47 ዓመታት በትዳር ቆይተዋል። ሦስት ልጆችም አፍርተዋል።

ባለቤታቸውን እንዲተዋወቁ ምክንያት ከሆነች ዘማች ጓደኛቸው ጋር አሁንም ድረስ ወዳጆች ናቸው።

ያኔ ወ/ሮ አፀደ ሲዘምቱ ምን ያህል ዋጋ እንዳለው አልተረዱትም ነበር።

ነገሩን በወጣትነታቸው ሲያዩት ሥራቸው "ቋት የሚሞላም አይመስለንም ነበር" ይላሉ።

አሁን ከ50 ዓመታት በኋላ መለስ ብለው ሲያዩት ነው "ምን ያህል ጥሩ ሥራ ነው የሠራነው" የሚሉት።

ዛሬ ላይ የዕድገት በኅብረት ዘመቻን ለልጆቻቸው ይተርካሉ። በተለይም ትልቁ ልጃቸው 'እስኪ እማዬ ስለ ዕድገት በኅብረት፣ ስለ ኢሠፓ አውሪልኝ' ይላቸዋል።

እሳቸውም የዚህ ታሪክ አካል መሆናቸው ያስደስታቸዋል።

የሰላ ድንጋይ ዘማቾች

የፎቶው ባለመብት, KIDIST

የምስሉ መግለጫ, የሰላ ድንጋይ ዘማቾች ከ15 ዓመታት በኋላ ዳግመኛ ሲገናኙ

የአብዮተኛ ወኔ

ሌላዋ የሰላ ድንጋይ ዘማች ወ/ሮ ቅድስት ሲዘምቱ 17 ዓመታቸው ነበር። የቤታቸው ሁለተኛ እና የመጨረሻ ልጅ ናቸው።

ተወልደው ያደጉት ደብረ ብርሃን።

ዕድገት በኅብረት ሲታወጅ 10ኛ ክፍል ጨርሰው ነበር።

"ያኔ ልጅ ነኝ። ዘመቻው ምን እንደሆነም፣ ምን እንደምንሠራም አናውቅም ነበር። ለዘመቻ ሆይ ሆይ ሲባል፣ መዝሙሩ ሲዘመር ግን የሚሰማ ነገር አለ። በዚያ ላይ ጊዜው የለውጥ ነበር።"

ከ1965 ዓ. ም. ጀምሮ (እሳቸው 9ኛ ክፍል ሳሉ) በመላው አገሪቱ የሚወራው ስለ ለውጥ ነበር።

ወ/ሮ ቅድስት ምክትል የክፍል አለቃ ስለነበሩ ከየክፍል አለቆች እና ምክትሎቻቸው ጋር የትምህርት ማቆም አድማ ስለማድረግ ሲመካከሩ ያስታውሳሉ።

ዘውዳዊውን ሥርዓት ለመገርሰስ የተነሳው አመጽ ወታደራዊውን ደርግ ወደ ሥልጣን ካመጣ በኋላ ወጣቶች ሕልማቸው ቃል የተገባውን ለውጥ መተግበር እንደነበር ያስታውሳሉ።

ኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያን ማለምለም፣ መሬት ላራሹን መተግበር፣ መሠረተ ትምህርትን ማስፋፋት ነበር ሕልማቸው።

"ወኔ ነበረን። ምን እንሆናለን የሚል ፍርሃት አልነበረንም። ቤተሰቦቻችን ግን ተጨንቀው ነበር።"

ሰላ ድንጋይ የሚወስዳቸው ሎንችን ደብረ ብርሃን ሲደርስ በአብዮተኛ መንፈስ ነበር የጠበቁት።

"እናቶቻችን እዚያ ያለቅሱ ነበር። እኛ አላለቀስንም። እቃችንን ጫንን። ሄድን። ቀድመውን የደረሱት የአዲስ አበባ ልጆች እና የአካባቢው ማኅበረሰብ ሲቀበለን የበለጠ ደስ አለን።"

ካኪ በካኪ ዩኒፎርማቸውን ለብሰው በደስታ ሕዝቡን ተቀላቀሉ። የዘማች ኃላፊነታቸውን መወጣትም ቀጠሉ።

ስለ መሬት ላራሹ ያስተምራሉ። ስብሰባ ይሳተፋሉ። አዝማቾች በሚሰጧቸው አቅጣጫ መሠረት ችግሮች ሲፈጠሩ አርሶ አደሩን ያወያዩና ያማክሩም ነበር።

የሰላ ድንጋይ ዘማቾች

የፎቶው ባለመብት, KIDIST

የምስሉ መግለጫ, የሰላ ድንጋይ ዘማቾች 50ኛ ዓመት መታሰቢያ ሲያከብሩ

'ኢቫክዌሽን'

ማታ ማታ ማርክሲዝም-ሌኒንዝም ያጠናሉ። ይወያያሉ። ይከራከራሉ።

'መሬት ላራሹ፣ ለላብ አፍሳሹ' እንዴት ይተግበር? የሚለውን የሚያስተምሯቸው የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ነበሩ።

በዚህ ውይይት ወቅት ነበር "ለውጡ እንደተጠበቀው አይደለም" ብለው መነጋገር የጀመሩት።

አንድ ዓመት ገደማ በዘመቻ ቆይተው በማርክሲዝም ጥናት የተጀመረው የምሽት ውይይት ዘመቻውን ጥለን እንሂድ ወደሚል ተለወጠ።

በምሥጢር ተወያይተው በምሥጢር ወሰኑና በምሥጢር ዘመቻ ጣቢያውን ጥለው ወጡ።

"ኢቫኩዌት እናድርግ ተባለ . . . ትልቅ የጭነት መኪና አስመጥተን እቃችንን ጫንን። የደብረ ብርሃን ልጆች እቃ ለመረከብ ቀድመን በመኪናው ተጭነን በሌሊት ደብረ ብርሃን ገባን። ያኔ ጥበቃው ጠንካራ ስለነበር እንኳን ሌሊት ቀንም ያስፈራ ነበር።"

የተቀሩት አብዛኞቹ ዘማቾች ከሰላ ድንጋይ ጣርማ በር፣ 22 ኪሎሜትር ገደማ በእግራቸው በሌሊት ተደብቀው ተጉዘው፣ ከዚያ መኪና እየለመኑ ተሳፍረው ደብረ ብርሃን ገቡ።

ብዙም ሳይቆይ መንግሥት ዘመቻ ጥላችሁ የወጣችሁ እስከዚህ ቀን ድረስ ካልተመለሳችሁ ሰርተፍኬት አይሰጣችሁም፣ ሥራም አትቀጠሩም፣ ትምህርትም አትማሩም ብሎ በራድዮ ማስታወቂያ አስነገረ።

እስካሁን ለፍተን እንዴት መና እንቀራለን ብለው ወደ ዘመቻ ጣቢያ ተመለሱ።

የሰላ ድንጋይ ዘማቾች 50ኛ ዓመት መታሰቢያ ሲያከብሩ

የፎቶው ባለመብት, KIDIST

የምስሉ መግለጫ, የሰላ ድንጋይ ዘማቾች 50ኛ ዓመት መታሰቢያ ሲያከብሩ

የቅድስት ራድዮ

ዘመኑ የአብዮተኛነት ብቻ አልነበረም። በሰላ ድንጋይ ዘመቻ ጣቢያ ሙዚቃ እና የእሳት ዳር ጨዋታም ይዘወተራል።

ዘማቾቹ አንድ ራድዮ ነበራቸው። የራድዮው ባለቤት ደግሞ ወ/ሮ ቅድስት ነበሩ።

በእሳቸው ስም ራድዮው ይመዝገብ እንጂ "የሁሉም ራድዮ ነበር" ሲሉ ያስታውሳሉ።

በኢትዮጵያ ራድዮ ዜና ይሰማሉ። በአብላጫው ሙዚቃ ነበር የሚያዳምጡት። ዘማቾች ለዘማቾች በራድዮ መሰናዶ ሙዚቃ ይገባበዙም ነበር።

"እከሌ እንዲህ ነው፣ ከዚህ ነው የመጣው፣ ሃይማኖቱ ይሄ ነው፣ ዘሩ ይሄ ነው አንልም። በአንድነት እና በፍቅር እሳት ዳር እንጨፍር ነበር።"

ከራድዮ ጋር ካላቸው ትዝታ አንዱ ዶርም ውስጥ ነው።

"ዶርም ከእህቶች ጋር የመኖር ያህል ነበር የምንዋደደው። ከጎኔ የምትተኛው 'ጠዋት ጠዋት ራድዮ ላዳምጥ' ስትለኝ እንዲያውም በቃ ጠዋት ጠዋት ራድዮው ያንቺ ነው ስላት በደስታ ተነስታ የዘለለችው ዝላይ እስካሁን ድረስ በዓይኔ ላይ አለ።"

ያን ራድዮ ቤተሰቦቻቸው ቤት ካስቀመጡት በኋላ አሁን የት እንደደረሰ እርግጠኛ አይደሉም።

የሰላ ድንጋይ ዘማቾች 50ኛ ዓመት መታሰቢያ ሲያከብሩ

የፎቶው ባለመብት, KIDIST

የምስሉ መግለጫ, የሰላ ድንጋይ ዘማቾች 50ኛ ዓመት መታሰቢያ ሲያከብሩ

የኢሕአፓ 'ሴል'

ዘመኑ ወጣቶች በቀላሉ ፖለቲከኛ የሚሆኑበት ነበር።

ወ/ሮ ቅድስት ከዘመቻ ተመልሰው 11ኛ ክፍል እየተማሩ ሳለ አንድ ቀን በአማርኛ ክፍለ ጊዜ ግጥም አቀረቡ።

ግጥሙ የፖለቲካ ነበር። አማርኛ አስተማሪያቸው ከክፍል ሲወጡ ጠራቸው።

በጥቆማ ከአንድ ሰው እንዲገናኙ ተነገራቸው። ከዚያም ኢሕአፓ 'ሴል' ውስጥ ገቡ። ገና ከጅምሩ ግን ታሰሩ።

"12ኛ ክፍል ልንፈተን ስንል ነበር የታሰርነው። አላጠናንም ነበር። የፖለቲካ እንጂ የትምህርት ፍላጎትም አልነበረንም።"

ታስረው ሲፈቱ 'ፖለቲካ አይሆነኝም' ብለው ወደ ትምህርታቸው ተመለሱ።

ኮሜርስ ገብተው አካውንቲንግ አጠኑ። ኋላ ላይ የራሳቸውን መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ከፍተዋል። አሁን የቅን ኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ ናቸው።

ወ/ሮ ቅድስት ለሁለት ልጆቻቸው "እኔ በእናንተ ዕድሜ ዘምቻለሁ" ይሏቸዋል።

"ልጆቼ፣ መጽሐፍ አንብበውም በስሚ ስሚም 'እናንተ ዘምታችሁ ምንም ሳትሠሩ ነው የመጣችሁት' ይሉኛል። ግን ደግሞ በጣም ጠንካራ ነበራችሁም ይላሉ።"

የሰላ ድንጋይ ዘማቾች 50ኛ ዓመት መታሰቢያ ሲያከብሩ

የፎቶው ባለመብት, KIDIST

የምስሉ መግለጫ, የሰላ ድንጋይ ዘማቾች 50ኛ ዓመት መታሰቢያ ሲያከብሩ

ፖሊስም አስተዳዳሪም

"ሁሉም ነገር በአንዴ ተለውጦ፣ እኛ የምንፈልገው ሶሻሊዝም መጥቶ፣ አብዮት ግቡን መትቶ፣ ኢትዮጵያ ቀድማ የምናይ ይመስለን ነበር" ይላሉ ወ/ሮ ቅድስት።

ለውጥ ዛሬውኑ ይምጣ ከሚለው ፍላጎታቸው የተነሳ እንደ ፖሊስም እንደ አስተዳዳሪም ለመሆን መሞከራቸውን ያስታውሳሉ።

"ያኔ አልተረዳነውም። አሁን ላይ ሳስበው ግን ሁሉም እኛ ባልነው ይሁን እንል ነበር... እንደ ወረዳ አዛዥም እንደ ፖሊስም ያደርገን ነበር። ሁሉንም ነገር ልንለውጥ የሄድን ነበር የሚመስለን። ሁሉም ውስጥ እንግባ፣ ሁሉም እኛን ይመለከታል እንል ነበር። አሁን ሳስበው ያስደነግጠኛል።"

በዚህ አቋማቸው ከኅብረተሰቡ ጋር አንዳንዴም ቢሆን መጋጨታቸው አልቀረም።

በአብዛኛው ግን አርሶ አደሩ ዘማቾችን ቤቱ ወስዶ እንደ ልጆቹ ጠላ እና ዳቦ ሰጥቶ ነበር በፍቅር የያዛቸው።

እነሱም ዝናብና ጭቃ ያዘን ሳይሉ ያስተምሩ ነበር።

እናቶች እና አባቶች ከምንም ተነስተው ማንበብ እና መጻፍ ሲችሉ ማየት "አሁንም የሚያስደስተኝ ትልቅ ሥራ ነው" ይላሉ ወ/ሮ ቅድስት።

እንኳንም ዘመትኩ። እንኳንም እዚያ ታሪክ ውስጥ ኖርኩ ያስብላቸዋል።

የሰላ ድንጋይ ዘማቾች

የፎቶው ባለመብት, KIDIST

የምስሉ መግለጫ, የሰላ ድንጋይ ዘማቾች 50ኛ ዓመት መታሰቢያ ሲያከብሩ

'ከመጠን ያለፈ ፍቅር'

ሌላኛው የሰላ ድንጋይ ዘማች ዶ/ር ጌታቸው፣ ዘማቾች ሲሰማሩ ታመው ለአንድ ወር ሆስፒታል ነበሩ።

"አቀባበሉን ስላላየሁ ይቆጨኛል" ይላሉ።

ዘመቻ ጣቢያ ከገቡ በኋላ ከነበረው ቆይታቸው በጉልህ የሚያስታውት በዘማቾች መካከል የነበረውን 'ከመጠን ያለፈ ፍቅር' ነው።

እሳቸው በሳሲት ንዑስ ካምፕ ነው የነበሩት።

ዕድገት በኅብረትን ሲያስቡ፣ በኢትዮጵያ መሠረታዊ የአስተዳድር መዋቅር ውስጥ የመጨረሻው እርከን የሆነውን ቀበሌ በመመሥረት ረገድ የነበራቸውን ሚና ሳይጠቅሱ አያልፉም።

ይህም ከማኅበረሰቡ ጋር የበለጠ አቀራርቧቸዋል።

ከአንድ ዓመት የዘመቻ ቆይታ በኋላ 'ኢቫኩዌት' ካደረጉት ዘማቾች አንዱ ዶ/ር ጌታቸው ናቸው። በእግራቸው ነበር ካምፑን ጥለው የወጡት።

በአንድ አቅጣጫ ወደ ደብረ ብርሃን ከተመለሱ መንግሥት ጥርጣሬ ስለሚገባው በተለያየ አቅጣጫ ዘማቾች እንዲጓዙ ማድረግ የእሳቸው ኃላፊነት ነበር።

"እኛ ስንመለስ፣ እናቴ ወደ ለቅሶ ስትሄድ ድልድይ ላይ አገኘኋት። በጣም ደነገጠች። የተሰጠኝ ዘማቾችን የመጠበቅ ኃላፊነት ከባድ ስለነበር እናቴን ከብዙ ጊዜ በኋላ ቢሆንም ያገኘኋት ሁለት ደቂቃም ሳላዋራት ቻው ብያት ሄድኩ።"

ደብረ ብርሃን ተመልሰው ከገቡ በኋላ የትራንስፖርት ገንዘብ የሌላቸውን ዘማቾች አሳፍረው ወደ አዲስ አበባ እና ሌሎችም ከተሞች ልከዋቸዋል።

ብዙም ሳይቆይ ግን ወታደራዊው መንግሥት መኪና አቅርቦ ወደ ዘመቻ ጣቢያ መልሷቸዋል።

ዋሻው

አብዛኞቹ ዘማቾች ወጣቶች ነበሩ። ከቤተሰቦቻቸው እና ከከተማ ርቀው ስለሚኖሩ ራሳቸውን ከአካባቢው ጋር ማላመድ የመጀመሪያ ሥራቸው ነበር።

አብረው በሥራም፣ በማስተማርም፣ በመዝናናትም የሚያሳልፉት ጊዜ ሲጨምር የፍቅር ግንኙነትም መመሥረት ጀመረ።

ያኔ በዘማቾች መካከል የተመሠረቱ የፍቅር ግንኙነቶች በትዳር ዘመናትን ተሻግረዋል።

ዶ/ር ጌታቸው እንደሚያስታውሱት፣ የሴቶች እና የወንዶች ዶርም የተለያየ ቢሆንም ፍቅረኛሞች 'መገናኛ መንገድ' አያጡም ነበር።

ከዘማቾች ጣቢያ ውጪ ያሉ ፍቅረኞቻቸውን ወደ ዘመቻ ጣቢያው የሚጋብዙም ነበሩ።

"ያኔ ሞባይል የለም። ፍቅር በመነጋገር ነበር የሚገለጸው" ይላሉ።

ጥንዶች የሆድ የሆዳቸውን ለማውራት ታዲያ ሽርሽር ይወጣሉ።

በአካባቢው አንድ ሸለቋማ ቦታ ነበር። ጥንታዊ አርበኞች ለውጊያ የፈለፈሉት ዋሻ ይገኝበታል። ዋሻው መስኮት እና የተለያዩ ክፍሎች አሉት።

ጥንዶች እና ሌሎችም የፍቅር ጓደኛ የሌላቸው ዘማቾችም ይሄን ዋሻ ይጎበኛሉ።

አንዳንዴ ታዲያ ዘማቾች ወደ ዘመቻ ጣቢያ ሲመለሱ 'መንፈስ ታይቶኛል' ይሉ እንደነበር ዶ/ር ጌታቸው ያስታውሳሉ።

የሰላ ድንጋይ ዘማቾች

የፎቶው ባለመብት, KIDIST

'ቡዳ የበላቸው ዘማቾች'

ዘማቾች 'ቡዳ በላን' ይሉ ነበር።

ከዚያም የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ጣቢያው ይጠራሉ። የዘልማድ 'መድኃኒት' ለዘማቾች ይሰጧቸዋል። ከዚያም ዘማቾቹ 'ይድኑ' እንደነበር ዶ/ር ጌታቸው ትዝ ይላቸዋል።

"ያንን 'ቡዳ ይበላል' የሚባለውን ነገር ምንነቱን አሁንም ለመግለጽ ይከብደናል" ይላሉ። አንድ የማይረሱት ገጠመኝም አላቸው።

"... አንድ ፀጉሯ በጣም የሚያምር ቆንጆ ጓደኛችንን 'ቡዳ ይበላሻል ተሸፈኚ' እንላት ነበር። አንድ ቀን ፀጉሯን ለቃ ገበያ ወጣች። ማታ ስንመለስ 'ፀጉሬን አቃጥሉት' ብቻ መጮህ ጀመረች። የአካባቢውን ሰዎች ጠርተን 'የቡዳ' መድኃኒት ተሰጣት። እሷ እህታችን በቅርቡ ነው በሞት የተለየችን።"

የሰላ ድንጋይ ዘማቾች

የፎቶው ባለመብት, KIDIST

የውሻ ጭራ ተኩሶ የመታው ወታደር

ሳሲት የዘማቾች ጣቢያ ሳሉ አንድ ቀን የውሻ መንጋ ገባ።

ዘማቾቹን እንዲጠብቅ የተመደበውን ወታደር 'ኧረ ተኩስና አድነን!' ብለው ተማጸኑ።

ወታደሩ ቢተኩስ፣ ቢተኩስ፣ ቢተኩስም አልተሳካለትም።

"የአንድን ውሻ ጭራ ብቻ መታ። ከዚያ 'አንተማ ምንም አትጠብቀንም' ብለን መሣሪያውን ቀምተን ወደ ዋናው ጣቢያ አባረርነው።"

ከውሾች በላይ ዘማቾች የሚፈሩት ሽፍቶችን ነበር።

ሽፍቶች ከሩቅ ሲመጡ የአካባቢው ማኅበረሰብ ዘማቾቹን ያስጠነቅቃቸዋል።

"የክብር ዘበኛው ኃይለኛ ስለሆነና እኛም የተዋጊነት መንፈስ ያድርብን ስለነበር በድንጋይም በዱላም እናባርራቸዋለን" ይላሉ ዶ/ር ጌታቸው።

ኤም-1 ሲተኩሱ ድምጹ ስለሚያስተጋባ አካባቢውን ይነቀንቀዋል። 'ብዙ መሣሪያ አላቸው' ተብሎ ስለሚታሰብም እምብዛም የሚዳፈራቸው አልነበረም።

የሰላ ድንጋይ ዘማቾች

የፎቶው ባለመብት, KIDIST

ዘመነ ራድዮ

እነ ዶ/ር ጌታቸው ከሰላ ድንጋይ ሳሲት፣ ከሳሲት ሰላ ድንጋይ ወይ በእግራቸው ወይ የመኪና አናት ላይ ተጭነው ይሄዱ ነበር።

ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት መጽሐፍ በማንበብ፣ የፖለቲካ ውይይት በማድረግ እና ራድዮ በማዳመጥ ነበር።

ከማርክሲዝም-ሌኒንዝም ባሻገር፣ 'ፍቅር እስከ መቃብር'፣ 'አደፍርስ'፣ 'ከአድማስ ባሻገር' እና ሌሎችም ልብ ወለዶችን ያነባሉ።

የጀርመን ድምጽ ራድዮ ጣቢያ (ዶቸ ቨለ) እና የኢትዮጵያ ራድዮ ይሰማሉ። የውጭ አገር ዜናም ይከታተላሉ።

"ፊሊፕስ ተንቀሳቃሽ ራድዮ በ60 ወይም በ70 ብር ይገኝ ነበር። ማንጠልጠያ ስላለው ራድዮውን አንግተን እንጓዛለን" ሲሉ ያስታውሳሉ።

ዘማቾቹ 'ኢቫኩዌት' አድርገው ከተመለሱ በኋላ የፖለቲካ አቅጣጫም አቋምም ለውጠው እንደነበር ዶ/ር ጌታቸው ያስታውሳሉ።

እሳቸውም ኢሕአፓን ተቀላቅለዋል።

ከሌላ ጣቢያ መረጃ ማድረስ ከተፈለገ በአካል ነበር የሚላኩት። መረጃው ለኢሕአፓ ወይም መኢሶን ተወካዮች ይደርሳል።

ያኔ ተንቀሳቃሽ ስልክ አለመኖሩ ከፖለቲካው አልፎ ፍቅርንም በደብዳቤ አድርጎታል።

የሰላ ድንጋይ ዘማቾች

የፎቶው ባለመብት, KIDIST

ፍቅር በኤሮግራም

ዶ/ር ጌታቸው ኤሮግራምን በልዩ ሁኔታ ያስታውሳሉ።

ኤሮግራም በ10 ሳንቲም፣ ቴምብር በ5 ሳምንቲም ነበር የሚገዛው።

"ኤሮገራሟ ውሃ ሰማያዊ ናት፣ ተዘርግታ ይጻፍባታል... ቀጭንና ሦስት ቦታ የምታጠፍ ናት፤ ደግሞም የራሷ ማጣበቂያ አላት። ለፍቅረኛ እና ለቤተሰብ ሲጻፍ 'ስታይሉ' ይለያል።"

ለፍቅረኛ ሲጻፍ ኤሮግራሙን እያሽከረከሩ በክብ ይጽፋሉ። የፍቅር ደብዳቤ በፈጠራ የተሞላ ነው።

'የሰማይ ርቀቱ፣ የአሸዋ ብዛቱ፣ የፀሐይ ግለቱ. . . ' እየተባለ ይጀመራል፤ ፍቅርን ለመግለጽ።

አበባ መሳል፣ ልብ መሳል እና በልብ ቅርጽ ጽፎ በመካከሉ ጦር ማሳለፍ የተለመደ ነበር።

ራቅ ያለ ቦታ ሲሆን ኤሮግራሙ በአደራ በፖስታ ቤት ይላካል።

ስልክ መደወል ካስፈለገ ቴሌኮምንኬሽን ጣቢያ ሄዶ ወረፋ ይያዛል።

ተራቸው ሲደርስ የስልኩን እጀታ ያነሳሉ። የገመድ ስልክ ስለነበር እየጮሁ ነበር የሚያወሩት። ከጎን የሚደውለውም ስለሚሰማ ምሥጢር ለመነጋገር አይመችም።

የሰላ ድንጋይ ዘማቾች

የፎቶው ባለመብት, KIDIST

የያኔው ሰቆቃ

ዶ/ር ጌታቸው የዘመቱት ከ11ኛ ክፍል ነበር።

ከዘመቻ ተመልሰው በ1969 ዓ.ም. 12ኛ ክፍል ሊጨርሱ ሲሉ ቀይ ሽብር መገባደጃው ላይ ነበር።

ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ከገቡ በኋላ ታስረዋል። ሲፈቱ ትምህርታቸውን ጨርሰዋል።

በተለያዩ ጣቢያዎች በጎርፍ የተወሰዱ፣ በግጭት ወይም በሽፍታ የተገደሉ እንዲሁም የት እንደገቡ የማይታወቅ ዘማቾች እንደነበሩም ያስታውሳሉ።

የዚያን ዘመን የፖለቲካ መገዳደል፣ የ77ቱን ድርቅ እና አጠቃላይ ዘመኑን ሲያስታውሱ "እንደ መፈተኛ ነው የማያቸው" ይላሉ።

ስለ ድርቅ ሲነገር ሰምተው እንጂ አይተው ስለማያውቁ በ77 ያዩት ሰቆቃ እስከ ወዲያኛው ባህሪያቸውን እንደለወጠው ይናገራሉ።

የሰላ ድንጋይ ዘማቾች

የፎቶው ባለመብት, KIDIST

ዶ/ር ጌታቸው አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል ያስተምራሉ።

ከዘማቾች መካከል የዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዝዳንት፣ ኮሎኔል፣ ዶክተር፣ ነጋዴም የሆኑ አሉ።

መምህርነት በጣም የሚወዱት ሙያ ነው።

"ኃይለኛ መምህር ነኝ" ይላሉ። ተማሪዎቻቸው ግን እስከ ዛሬም ጓደኞቻቸው ናቸው።

የሁለት ልጆች አባት የሆኑት መምህሩ "የመንፈስ ልጆቼ ግን ብዙ ናቸው" ሲሉ ነው ተማሪዎቻቸውን የሚገልጹት።

ስለ ስኬት፣ መክሊትን ስለማግኘት እና ስለ ደስታ ሲናገሩ መምህርነትን ሳይጠቅሱ አያልፉም።

የሰላ ድንጋይ ዘማቾች

የፎቶው ባለመብት, KIDIST

ያ ትውልድ. . .

"የኔ ትውልድ በአብዛኛው አገር አገር ነው የሚለው" ይላሉ ዶ/ር ጌታቸው።

ትውልዳቸው ላመነበት ዓላማ እስከ መጨረሻው እንደሚዋደቅ ያምናሉ።

"እኔም፣ ያኔም አሁንም ላመንኩበት የትም ድረስ መሄድ እችላለሁ። ጀምሬ ሳልጨርስ አላቋርጥም። ለዓላማ መጽናት ትልቁ ቃል ኪዳናችን ነው።"

50 ዓመት መለስ ብለው ዕድገት በኅብረትን ሲቃኙ፣ አርሶ አደሩ ቀድሞ ከነበረው ማኅበራዊ ውቅር ወጥቶ ዕሳቤውን እንዲለውጥ ተደርጓል ብለው ያምናሉ።

"የሚጠበቀውን ያህል ባይሆንም ለውጥ አለ። አርሶ አደሩ ጥያቄ ማንሳት እንደሚችል ያወቀበት ነው። የታዘዙትን ከመሥራት ወጥቶ መጠየቅ መቻል ትልቅ ነገር ነው።"

የሰላ ድንጋይ ዘማቾች

የፎቶው ባለመብት, KIDIST

ዘማቾቹ ከ50 ዓመታት በኋላ

ወ/ሮ አፀደ፣ ወ/ሮ ቅድስት እና ዶ/ር ጌታቸው ዕድገት በኅብረትን ሲያስታውሱ፣ እርስ በእርስ መተባበር የተማርንበት ነው ይላሉ።

በአንድነት መሥራትን፣ አብሮ መኖርን፣ ፍቅርን እና መቻቻልን ከዕድገት በኅብረት አግኝተዋል።

ከ15 ዓመታት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት በፖሊስ ክበብ ነበር። ከዚያም ሲታመሙ መጠያየቅ፣ ለቅሶ መድረስም ቀጠሉ።

በዚህ ዓመት ደግሞ 50ኛ ዓመት የዕድገት በኅብረት ዘመቻ መታሰቢያን በፊንፊኔ አዳራሽ አካሂደዋል።

ወ/ሮ አፀደ ዘማቾች ሲገናኙ አንዳቸው የረሱትን ሌላቸው እያስታወሱ እንደሚጨዋወቱ ይናገራሉ።

ለዶ/ር ጌታቸው ዘማች ጓዶቻቸውን ማግኘት በትዝታ ወደኋላ ይመልሳቸዋል።

"የትዝታ መስመር መልሶ ይነቃቃል" ሲሉ ይገልጹታል።

ወ/ሮ ቅድስት ደግሞ ያኔ ያልተሰሙ ድብቅ የፍቅር ታሪኮችም ብቅ ብቅ እንደሚሉ ይናገራሉ።

"ዘማቾች ያኔ ተደብቀው ያደረጉት ነገር አሁን ይወጣል። ለበዓል የተሠራ ምግብ ሌሊት ገብተው መብላታቸውን ይነግሩናል . . . እንገረማለን እንስቃለን።"