የአይኤስ አባል በነበረችው የቀድሞዋ የአየርላንድ ወታደር ላይ እስር ተፈረደባት

የፎቶው ባለመብት, BRIAN LAWLESS/PA
አይኤስ (እስላማዊ መንግሥት) በመባል የሚታወቀው ሽብርተኛ ቡድን አባል ሆና የተገኘችው የቀድሞዋ የአየርላንድ ወታደር እስራት ተፈረደባት።
የ40 ዓመቷ ሊሳ ስሚዝ አራት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ የአይኤስ ቡድን አባል ሆና መቆየቷ ባለፈው ግንቦት ወር በመረጋገጡ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብላ ነው የ15 ወራት አስር የተፈረደባት።
ግለሰቧ ላይ ብይኑን ያስተላለፈው በአየርላንድ ዋና ከተማ ደብሊን ውስጥ የሚገኝ ልዩ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት ነው።
ጉዳዩን የተመለከተው ችሎት ከቀረቡባት ክሶች ለአንድ ግለሰብ ገንዘብ በመላክ ሽብርተኛ ቡድኑን ደግፋለች የሚለውን ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል።
ውሳኔውን ያሳለፉት ዳኛ ጀስቲስ ሃንት በችሎቱ ላይ፣ አንዲት የአየርላንድ መከላከያ ኃይል አባል ለውጭ የሽብር ድርጅት ቃል በመግባት አባል መሆን ለየትኛውም የአገሪቱ ዜጋ አሳሳቢ ነገር ነው ብለዋል።
ጨምረውም ሊሳ ስሚዝ ምን እያደረገች እንደነበረ እንደምታውቅ ምንም የሚያጠራጥር ነገር የለም በማለት፤ ነገር ግን ግለሰቧ ቀደም ሲል የነበራትን ባህርይ እንዲሁም ሶሪያ ውስጥ በነበረችበት ጊዜ በቤት ውስጥ በደረሰባት ጥቃት ያሳለፈችውን ሁኔታ ችሎቱ ከግምት አስገብቷል ብለዋል።
ዳኛው ምንም እንኳን ሊሳ በእራሷ ውሳኔ ወደ ሶሪያ ብትሄድም፣ በተሳሳተ መንገድ ተመርታ ሶሪያ ውስጥ ያጋጠማትን መራራ ሕይወት እስከመጨረሻው ተቀብላ መቆየቷን አመልክተዋል።
አሁን ያለችበት ሁኔታ እና ከልጇ ጋር ጥብቅ ትስስር የነበራት እናት እንደሆነች በመጥቀስ፣ ከዚህ በኋላ ስጋት ልትሆን እንደምትችል የሚያሳይ ምንም ምክንያት የለም ብለዋል ዳኛው።
ሃይማኖቷን ወደ እስልምና እምነት ቀይራ የነበረችው ሊሳ ስሚዝ፣ የአይኤስ ሽብር ቡድን መሪ የነበረው አቡ ባካር አል-ባግዳዲ ሁሉም ሙስሊሞች ቡድኑን እንዲቀላቀሉ ሲያደርግ ነበር ወደ ሶሪያ የሄደችው።
ችሎቱ ውሳኔውን ከማሳለፉ በፊት ጉዳዩን ለተመለከቱት ዳኞች ሊሳ ለችግር የተጋለጠች እንደነበርና የተለያዩ የሥነ ልቦና ችግሮች አጋጥመዋት እንደነበር ተነግሯቸው ነበር።
ጠበቃዋም ሦስት የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ስለደንበኛው ያቀረቡትን ሪፖርት በመጥቀስ ሊሳ ከልጅነት ጀምሮ ያሳለፈቻቸውን ችግሮች ችሎቱ ከግንዛቤ እንዲያስገባ ጠይቋል።
በተጨማሪም ሶሪያ ውስጥ የቆየችበትን አደገኛ ጥቃት ሲደርስባት የነበረውን የጋብቻ ሁኔታዋን በማንሳት ምን ያህል አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ሰቆቃ ውስጥ እንደቆየች በዝርዝር ለዳኞቹ አስረድቷል።
ሊሳ ስሚዝ ከአይኤስ ከተለየች በኋላም በተለያዩ የእስር ማዕከላት ለረጅም ጊዜ መቆየቷን በመጥቀስ፣ ያሳለፈችው ሁኔታንም “ፍጹም አስቀያሚና በጣም አስፈሪ” እንደነበር ጠበቃዋ ገልጿል።
ዳኞቹም የቀረቡትን ማስጃዎች በመመዘን በተጨማሪም ሊሳ ያለፈችበትን ሰቆቃ ከግምት በማስገባት የአንድ ዓመት ከሦስት ወር አስር ፈርዶባታል።












