የናይጄሪያ መንግሥት በመላው አገሪቱ ሞተር ብስክሌቶች እንዳይንቀሳቀሱ ሊያግድ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP
በሞተር ብስክሌት የሚጓዙ ታጣቂዎች በሰሜን ምዕራብ የናይጄሪያ ግዛት ካትሲና ውስጥ በተለያዩ ስፍራዎች ላይ በፈጸሟቸው ጥቃቶች አምስት ፖሊሶችን ጨምሮ 17 ሰዎችን ከተገደሉ በኋላ መንግሥት ሞተር ብስክሌቶች ለማገድ አያሰበ ነው።
ይህንንም ጥቃት ተከትሎ የአገሪቱ ባለሥልጣናት በእስላማዊ ቡድኖች አማካይነት ሞተር ብስክሌቶችን በመጠቀም የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመቆጣጠር በመላው ናይጄሪያ ሞተር ብስክሌቶችን ለማገድ እያሰቡ መሆኑ ተነግሯል።
በዚህ ሳምንት ረቡዕ ዕለት 300 የሚሆኑ በሞተር ብስክሌት የመጡ ታጣቂዎች ካንካራ በሚባል ቦታ ላይ የሚገኝን ፖሊስ ጣቢያ ኢላማ አድርገው ጥቃት ፈጽመዋል።
በተጨማሪም እነዚሁ ታጣቂዎች በፖሊስ ጣቢያው አቅራቢያ በሚገኝ አንድ መንደር ውስጥ በመግባት ሦስት ሰዎችን ገድለዋል።
በተመሳሳይ ሌላ ጥቃት ደግሞ ታጣቂዎች ፋሳካሪ በሚባለው አካባቢ በሚገኙ በርካታ መንደሮች ውስጥ በፈጸሙት ጥቃት ዘጠኝ ሰዎችን ሲገድሉ፣ ከብቶችን ጨምሮ ሌሎች ንብረቶችን ዘርፈዋል።
ካትሲና ግዛት በናይጄሪያ በታጣቂዎች ከፍተኛ ጥቃት ከሚፈጸምባቸው ቦታዎች አንዷ ስትሆን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሙሐመዱ ቡሃሪ ትውልድ ስፍራ ናት።
የናይጄሪያ መንግሥት በመላዋ ናይጄሪያ እየጨመረ ያለውን የደኅንነት ችግር ለመቆጣጠር ባለመቻሉ ከፍተኛ ትችት እየገጠመው ነው።
በአገሪቱ በተደጋጋሚ በሞተር ሳይክል በመታገዝ በእስላማዊ ታጣቂዎች የሚፈጸሙትን ጥቃቶች ተከትሎም የደኅንት ጥበቃውን ለማጥበቅ እየወሰዳቸው ካሉት እርምጃዎች መካከል የሞተር ብስክሌቶች እንቅስቃሴዎችን ማገድ ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል።
ናይጄሪያ ውስጥ “ኦካዳስ” በመባል የሚታወቁት ሞተር ሳይክሎች በተለይ ሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል በአማጺያን እና በወንጀለኛ ቡድኖች በቀላሉ ጥቃት ለመፈጸምና በሕዝቡ ውስጥ ፍርሃት ለማንገስ ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው ተብሏል።
በዚህም ሳቢያ ሞተር ብስክሌቶችን ማገድ ከተቻለ የወንጀል ቡድኖችን እንቅስቃሴ በቀላሉ መቆጣጠር ይቻላል ብሎ መንግሥት ያምናል።
ከሞተር ብስክሌቶቹ እገዳ በተጨማሪም በግለሰቦች ደረጃ የማዕድን ማውጣት ሥራዎችንም ለመከልከል መንግሥት እያሰበ መሆኑን የናይጄሪያው የፍትህ ሚኒስትር አቡባካር ማላሚ ተናግረዋል።
ናይጄሪያ ካሏት 36 ግዛቶች መካከል አስካሁን ሁለቱ ብቻ ናቸው ሞተር ብስክሌቶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ እገዳ የጣሉት።
በሰሜናዊ ምዕራብ ናይጄሪያ በምትገኘው ዛምፋራ ግዛት ሞተር ብስክሌቶች በመታገዳቸው የፀጥታ ኃይሎች ሞተር ሳይክል የሚያሸከረክርን ተኩስው መግደል እንዲችሉ ፈቃድ ሲሰጥ፣ በሌጎስ በሚገኙ አንዳንድ ስፍራዎች ሞተር ሳይክልን ለንግድ የትራንስፖርት አገልግሎት ማዋል ተከልክሏል።












