የጃፓን ፓስፖርት የዓለማችን ጠንካራው ፓስፖርት ተባለ፤ የኢትዮጵያስ?

ፓስፖርት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የጃፓናውያን ፓስፖርት የዓለማችን ‘ጠንካራው’ ፓስፖርት ተባለ።

ሄንሌይ የተሰኘው ተቋም የዓለም አቀፉን የአየር ትራንስፖርት ማኅበር አሃዞችን ተጠቅሞ ባወጣው ደረጃ መሠረት የጃፓን ፓስፖርት የዓለማችን ጠንካራው ፓስፖርት ነው ብሏል።

የጃፓን ፓስፖርትን የያዙ ሰዎች ወደ 193 አገራትና ግዛቶች ያለ ቪዛ መጓዝ ይችላሉ፣ አልያም ቪዛ በመዳረሻቸው ያገኛሉ።

የዓለማችን ምርጦቹ 10 ፓስፖርቶች

ሄንሌይ የፓስፖርቶችን ጥንካሬ የሚለከው፤ ተጓዦች በያዙት ፓስፖርት ምክንያት ቪዛ ቀድሞ ሳያስፈልጋቸው ወደ ስንት አገራት መጓዝ ይችላሉ የሚለውን በማጤን ነው።

በሄንሌይ ሪፖርት ላይ ቀድሞ ቪዛ አለማስፈለግ ማለት፤ ወደ መዳረሻ ለመጓዝ ቪዛ አለመጠየቅ አልያም በመዳረሻ ቪዛ የማግኘት መብት ማለት ነው።

ሄንሌይ የ2022 ሦስተኛው ሩብ ዓመት የፓስፖርት ደረጃዎችን ይፋ ያደረገው 199 ፓስፖርቶችን እና 227 መዳረሻዎችን ከመረመረ በኋላ መሆኑን አስታውቋል።

በዚህም መሠረት ሲንጋፖር እና ደቡብ ኮሪያ በእኩል ነጥብ የዓለማችን ሁለተኛው ጠንካራ ፓስፖርት ደረጃን ይዘዋል። የእነዚህ አገር ዜጎች ቀድመው ቪዛ ማግኘት ሳይጠበቅባቸው ወደ 192 መዳረሻዎች መጓዝ ይችላሉ።

ጀርመን እና ስፔን በሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሲሆን ፊንላንድ፣ ጣሊያን እና ላክሰመበርግ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ኦስትሪያ፣ ዴንማርክ፣ ኔዘርላንድስ እና ስዊድን ያለ ቪዛ ወደ 188 መዳረሻዎች በመጓዝ 5ኛ ድረጃ ላይ ናቸው።

ዩናትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ እና አውስትራሊያ ወደ 187፣ 186 እና 185 መዳረሻዎች ቀድሞ ቪዛ ሳያስፈልጋቸው ለመጓዝ በመቻል እንደ ቀደም ተከታላቸው 6ኛ፣ 7ኛ እና 8ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ፤ ሃንጋሪ እና ሉትዌኒያ ደግሞ 9ኛ እና 10ኛ ደረጃን ይዘዋል።

የኢትዮጵያ ፓስፖርት

ኢትዮጵያ

በሄንሌይ መረጃ መሠረት የኢትዮጵያን ፓስፖርት የያዙ ተጓዦች ቪዛ ሳያስፈልጋቸው ወይም በመዳረሻቸው ላይ ቪዛ ማግኘት የሚችሉባቸው መዳረሻዎች 46 ናቸው።

ይህም ከ112 ፓስፖርቶች የኢትዮጵያ ፓስፖርት 100ኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አድርጎታል።

የሄንሌይ የፓስፖርት ደረጃ ኢትዮጵያ ከሰባት የአፍሪካ አገራት የተሻለ ጠንካራ ፓስፖርት አላት ይላል።

ኢትዮጵያ የበለጠቻቸው አገራት ሶማሊያ፣ ሊቢያ፣ ሱዳን፣ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ፣ ናይጄሪያ፣ ኤርትራ እና ደቡብ ሱዳን ናቸው።

በፓስፖርት ጥንካሬ የዓለም የመጨረሻው ደረጃ ላይ የተቀመጡት 10 አገራት ደግሞ ሊቢያ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ኔፓል፣ የፍልስጤም ግዛት፣ ሶማሊያ፣ የመን፣ ፓኪስታን፣ ሶሪያ፣ ኢራቅ እና አፍጋኒስታን ናቸው።

ፓስፖርት የያዘች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፓስፖርት ጥንካሬ የሚወስነው በምንድነው?

የዓለም ባንክ እንደሚለው ከሆነ የአንድ አገርን የፓስፖርት ጥንካሬ ከሚወስኑ ዋነኛ ጉዳዮች መካከል አንዱ ዜጎች የሚያገኙ ገንዘብ መጠን ነው።

ከፍተኛ የነፍስ ወከብ ገቢ ያላቸው አገራት ከደሃ አገራት በተሻለ ወደ በርካታ አገራት ቪዛ ቀድሞ ማግኘት ሳይጠበቅባቸው መጓዝ ይችላሉ።

ይህ የሚሆነው ይላሉ የሄንለይ አጥኚ የሆኑት ኦመር ዛረፕሊ (ዶ/ር)፤ “ይህ የሚሆነው አገራት ከድሆች ይልቅ ለሃብታም አገራት ደንበሮቻቸውን ክፍት ስለሚያደርጉ ነው።”

ከፍተኛ የነፍስ ወከፍ ገቢ ካላቸው አገራት የሚመጡ ተጓዦች በመዳረሻቸው በቱሪዝም፣ በንግድ እና በኢንቨስትመንት መልክ ብዙ ገንዘብ ፈሰስ ስለሚያደርጉ ለተቀባይ አገር ምጣሄ ሃብታዊ ዕድገት አዎንታዊ አስተዋጽኦን ያበረክታሉ ይላሉ አጥኚው።

ይህም ብቻ አይደለም፤ ከሃብታም አገራት የሚመጡ ተጓዞች በሄዱባቸው አገራት ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን የማስከተል ዕድላቸው አነስተኛ ነው መሆኑ ጉዟቸውን እንደሚያቀለው ኦመር ዛረፕሊ (ዶ/ር) ጠቅሰዋል።

ሰላም እና የፓስፖርት ጥንካሬ

ሄንሌይ እንደሚለው የአንድ የአገር ሁለንተናዊ ሰላም ከአገሪቱ የፓስፖርት ጥንካሬ ጋር በቀጥታ ይገናኛል።

በአንድ አገር የሽብር ጥቃቶች እና ብሔርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች የበረከቱ ከሆነ፤ በተደራጁ ቡድኖች የሚፈጸሙ ወንጀሎች ካሉ የዚያች አገር ዜጎች ዓለም አቀፍ ጉዟቸው የተገደበ ይሆናል።

ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት የሌላቸው እና ከፍተኛ ተፈናቃይ ያለባቸው አገራት ዜጎችም በተመሳሳይ ቪዛ የሚጠየቁባቸው መዳረሻዎች ከፍተኛ እንዲሆኑ አድርጓል።

ለማሳያም ምጣኔ ሃብታቸው የደቀቀባቸው፣ ማዕከላዊ መንግሥታቸው የተዳከመባቸው አልያም የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች የበዙባቸው እንደ የመን፣ ሶሪያ፣ ኢራቅ እና አፍጋኒስታን ያሉ አገራትን ፓስፖርት የያዙ ዜጎች በብዙ መዳረሻዎች ቪዛ ይጠየቃሉ።