አዲሱ ምርጫ ለመጅሊሱ የመጨረሻ መፍትሄ ይኖረው ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲያወዛግብ የቆየው የመጅሊስ አመራር ጉዳይ የመጨረሻ መፍትሄ ያስገኛል ተብሎ በታሰበው ምርጫ አዲስ ሥራ አስፈጻሚ ምርጫ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ተካሂዷል።
በግንቦት ወር የዑለሞች ምክር ቤት ያደረገውን ምርጫ የቀደመው ሥራ አስፈጻሚ “ሕገ-ወጥ ነው፤ አንቀበለውም’’ ሲል መቃወሙን ተከትሎ ነው ምርጫው በድጋሚ እንዲካሄድ የተደረገው።
እነዚህን ልዩነቶች ለመፍታትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች የመንግሥት ባለሥጣናት የአረፋ በዓል መቃረቡን ተከትሎ ከሁለት ሳምንታት በፊት ከሁለቱም ወገኖች ጋር ስብሰባ ተቀምጠው እንደነበር ተሰምቷል።
ከቀዳሚው ብሎም አዲስ ተመርጦ ከቆየው ሥራ አስፈጻሚ በአጠቃላይ 50 ሰዎች የተገኙበት ይህ ጉባኤ፣ እንደ መፍትሄ የሸራተኑ ጉባኤ ተሳታፊዎች በድጋሚ ምርጫ እንዲያደርጉ ብሎም የዚህን ምርጫ ውጤት መንግሥት እንደሚያስፈጽም በመግለጹ ነበር ጠቅላላ ጉባኤው በድጋሚ የተጠራው።
ይህንንም ተከትሎ ነበር ሁለቱም ወገኖች በጋራ የአረፋ በዓልን በማስመልከት የጋራ መግለጫ የሰጡት።
በጠቅላላ ጉባኤው ላይ በታዛቢነት የተሳተፉት ኡስታዝ አህመዲን ጀበል ለቢቢሲ እንደተናገሩት ምርጫውን ተከትሎ የቀድሞው ሥራ አስፈጻሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጄይላን ከድር ቢሮውን ለአዲሱ ፕሬዘዳንት አስረክበዋል።
አዲስ የተመረጠው ሥራ አስፈጻሚም እንደ እስካሁኑ ጊዜያዊ ሳይሆን ለሦስት ዓመት የሚቆይ መሆኑንም አስረድተዋል።
በዚህም መሰረት በተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ ምትክ ሸኽ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል። ሸኽ አብዱልከሪም በድረዲን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሲሆኑ፣ ሸኽ አብዱልአዚዝ አብዱልዋሊ ደግሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ተመርጠዋል።
ለረጅም ጊዜ ሳይደረግ የቆየው የመጅሊሱ ጠቅላላለ ጉባኤ በግንቦት ወር 2014 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ በተጠራ ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎች ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በወቅቱ ጉባኤው ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከል የቀድሞ የዑለማዎች ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚን በማንሳት ወደ ፈትዋ ኮሚቴ በመመደብ አዲስ የሥራ አስፈጻሚ አባላትን መምረጥን ይጨምር ነበር።
አሁን ጠቅላላ ጉባኤው የመረጣቸው የሥራ አስፈጻሚ አባላት በግንቦቱ ምርጫ የተመረጡትን ደግሞ መርጧል።
የቀደመው መጅሊስ ውስጥ ያሉ የተወሰኑ ግለሰቦች የመረጣቸውን የሸራተኑን ጉባኤም ጭምር አንቀበልም የሚል አቋም በመያዛቸው ምክንያት ከመላው ኢትዮጵያ የተወጣጡ 300 በላይ ኡለሞች በተገኙበት አዲሱ ምርጫ መካሄዱን ሂደቱን በታዛቢነት የተከታተሉት አህመዲን ጀበል ተናግረዋል።
መንግሥት ከሁለት ዓመታት በላይ የዘለቀውን ይህንን ልዩነት ለመፍታት ብዙ ርቀት ሄዷል ሲሉም ይናገራሉ።
“ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከማሸማገል ባለፈ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር ኢድሪስ እግር ላይ ጭምር ወድቀው ይህንን ችግር እንዲፈቱ፣ እንዲሁም አገሪቱ አሁን ካለችበት ቀውስ በተጨማሪ ሌላ ክፍፍል እንዳይፈጠር እንዲሰሩ ጠይቀዋቸዋል’’ ሲሉም ይናገራሉ።
በተጨማሪም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የቀድሞው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አደን ፋራህ እንዲሁም ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚንስትር ዶ/ር አህመዲንን ያቃፈ ኮሚቴ በማቋቋም መፍትሄ ለመስጠት ተሞክሮም እንደነበረ አህመዲን ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በመጅሊሱ ውስጥ የተፈጠረው ልዩነት ምን ነበር?
ከ11 ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት ከሊባኖስ ተቀድቷል የሚባልለትን የአህባሽ አስተምሮ ወደ ኢትዮጵያ ‘በገንዘብ ኃይል በማምጣት በሕዝበ ሙስሊሙ ላይ ለመጫን ሞክሯል’ በሚል የዕምነቱ ተከታይ የሆኑ ምሁራን ጥያቄ አነሱ።
ይህ ጥያቄ በመንግሥት እና በምዕመኑ መካከል የፈጠረው ፍጥጫ ሌሎች ጥያቄዎች ተጨምረውበት ወደ ተቃውሞ ተሸጋገረ።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ተብሎ የሚጠራው እና በኡስታዝ አቡበከር አህመድ የሚመራው የምሁራን ቡድን መታሰሩን ተከትሎ 'ድምጻችን ይሰማ' የተሰኘው ንቅናቄ በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተመስርቶ ወደ ጠንካራ ተቃውሞ አደገ።
በወቅቱ ኮሚቴው ሦስት ዋና ዋና ጥያቄዎችን በይፋ አንስቷል። ጥያቄዎቹም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት (መጅሊሱ) በሕዝበ ሙስሊሙ በተመረጡ አመራሮች ይመራ፣ አህባሽ የተሰኘው አዲስ የሃይማኖት ምልከታ በግድ አይጫንብን እንዲሁም የአወሊያ ተቋም በመጅሊስ ሳይሆን በቦርድ ይተዳደር የሚል ነበር።
የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴው 17 አባላት የነበሩት ሲሆን በቀረበባቸው የሽብር ክስ በሐምሌ 2007 ዓ.ም ከ7 እስከ 22 ዓመት እስር ተፈርዶባቸው እንደነበረም ይታወሳል።
ከዚያም ከአራት ዓመት እስር በኋላ በ2008 ዓ.ም የአዲስ ዓመት ዋዜማ መንግሥት ምህረት ማድረጉን በመግለጽ ከእስር እንዲለቀቁ ተደረገ።
ታዲያ በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተውን የፖለቲካ አመራር ለውጥ ተከትሎ ሚያዚያ 23/2011 ዓ.ም. በተካሄደው ጉባኤ የተመሰረተው የሽግግር ምክር ቤት ለዓመታት ሲነሱ የቆዩትን የሕዝበ ሙስሊሙን ጥያቄዎች የሚመልስ ይሆናል ተብሎ ታምኖ ነበር።
ከሽግግር ምክር ቤቱ ባሻገር ዘጠኝ አባላት ያሉት የተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት የሚረዳ ኮሚቴ ተቋቋመ።
ከዚህ ኮሚቴ ውስጥ ከቀድሞው የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ሦስት፣ ተቃውሞ ሲነሳበት ከነበረው ከቀድሞው መጅሊስ ሦስት እንዲሁም ገለልተኛ የተባሉ ሦስት አባለት ተካተውበት ዘጠኝ አባላት ያሉት ሆኖ ተዋቀረ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ብሎም የወቅቱ የሰላም ሚኒስትር የነበሩት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በሸራተኑ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዚሁ ሸንጎ ላይ 500 የሚጠጉ ዑለሞች ከመላው ኢትዮጵያ ተወክለው የተገኙበት ሲሆን፣ አዲስ የተመረጠው ጊዜያዊ ጠቅላላ ጉባኤም እነዚህን ለዓመታት ሲነሱ የቆዩ ጥያቄዎችን ይመልሳል ተብሎ ተስፋ ተጣለበት።
ታዲያ የሸራተኑ ጉባኤ ሦስት ዓመት ካስቆጠረ በኋላ አዲስ ቋሚ መጅሊስ ምርጫ ለማካሄድ የተለያዩ ውዝግቦች ሲካሄዱ ቆይተው በግንቦት ወር አብላጫው የዑለሞች ምክር ቤት አባላት የተገኙበት ጉባኤ ተካሄደ።
የነባሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆነው የቆዩት እና ይህንን ምርጫ የሚቃወሙት ሸኽ አሕመድ አወል ሰኢድ “ማንንም ሰብስበው ጠቅላላ ጉባኤ በሚል ቃለ ጉባኤ ይዞ አንዱን መሻር መሾም ተገቢ አይደለም’’ ሲሉ ተቃውሟቸውን በወቅቱ ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
ከመላው አገሪቱ ዑለሞች ተሰብስበው መሳተፍ ነበረባቸው የሚሉት ሼሕ አህመድ እርሳቸው የዑለሞች ምክር ቤት አባል ሆነው ሳሉ ሳይሳተፉ መቅረታቸውንም ገልጸው ነበር።
በመጅሊሱ ውስጥ ሁለት ወገን እንዳለ እየታወቀ አንዱን ወገን ነጥሎ መሾም አግባብ አይደለም ሲሉ የተናገሩት ሸኽ አሕመድ አወል ሰኢድ፣ የሸራተኑን ጉባኤም “ሸራተን ሲመረጥም ትክክል የተሰራበት አይደለም። ሸፍጥ የተሰራበት ነው። ሁለቱንም ያጣጣመ እና እኩል ያደረገ አይደለም’’ ሲሉም ተቃውሟቸውን በወቅቱ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ኡስታዝ አሕመዲን እንደሚሉት አሁን የተደረገው ምርጫ መንግሥት ያስፈጽመዋል ተብሎ ይጠበቃል። በተጨማሪም አዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ቢሮውን ተረክቦ ሥራውን ጀምሯል።
ነገር ግን “አሁንም ያኮረፉ ሰዎች ይኖራሉ። በዚህ ረገድ ከሄድን የእነሱ ፍላጎት እስካልተሟላ ድረስ ችግሩ አይፈታም። በዚህኛውም ጉባኤ የተወሰኑ ሰዎች አልተገኙም። ነገር ግን መተግባር ስለ ኢትዮጵያ ሙስሊም ካወራን ግን ይህ ምርጫ ችግሩን ይፈታዋል’’ ሲሉ ተናግረዋል።












