በቻይና በኮቪድ 19 ክልከላዎች ሳቢያ ለቀናት የዘለቀውን ተቃውሞ ተከትሎ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ፖሊስ ተሰማራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቻይና የተጣሉ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መቆጣጠሪያ ገደቦችን በመቃወም ባለፉት የእረፍት ቀናት የተጠናከረው ተቃውሞ በተለያዩ ከተሞች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ፖሊስ መሰማራቱን ተከትሎ መቀዛቀዙ ተሰምቷል።
በሻንጋይ ዋና ጎዳና ላይ ረጅም ማገጃ የተተከለ ሲሆን ፖሊስ በርካቶችን አስሯል።
ተቃዋሚዎችን ፎቶ እንዳያነሱ የከለከሉ ሲሆን ያነሱትንም ፎቶ እንዲሰርዙ እያስገደዱ ነው።
በቻይና ምዕራባዊ ክፍል በአንድ ረጀም ህንጻ ላይ እሳት ተቀስቅሶ 10 ሰዎች ከሞቱ በኃላ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተቃውሞው ተጠናክሯል።
በኮቪድ 19 ክልከላዎች ምክንያት ሰዎች ከእሳት አደጋው ማምለጥ እንዳልቻሉ ቢታመንም የአከባቢው ባለስልጣናት ግን ይህንን አይቀበሉትም።
ባለፈው ዕሑድ በሻንጋይ የነበረውን ተቃውሞ ሲዘግብ የነበረው የቢቢሲ ጋዜጠኛ ታስሯል።
ጋዜጠኛው ኤድ ላውረንስ ለሰዓታት ታስሮ ከመለቀቁ በፊት በፖሊስ ደብደባ ደርሶበት ነበር።
ይህንንም ተከትሎ የዩኬ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሃላፊ ጄምስ ቸሌቨርሊይ እሰሩ “እጅግ አሳሳቢ” ነው ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል።
ቻይና የኮቪድ 19 ስርጭትን ዜሮ ለማድረስ ከሚሰሩ ታላላቅ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት ብቸኛዋ ስትሆን በታችኛው መዋቅር የሚሰሩ የመንግስት ሃላፊዎች ለዝቅተኛ የኮቪድ ስርጭት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ምርመራ፣ ተነጥሎ መቆየትን እና የእንቅቃሴ ገደቦቸን እየጣሉ ይገኛሉ።
የእንቅስቃሴ ገደቦችን የሚቃወሙ ሰልፎችን የሚያስመለክቱ በርካታ ምስሎች ከሻንጋይ፣ ከዋና ከተማዋ ቤጂንግ እንዲሁም እንደ ውሃን ካሉ አነስተኛ ከተሞች እየወጡ ይገኛሉ።
በማህበራዊ ሚዲያዎች ሰዎች ተቃውሞዎቹን እንዳይመለከቱ እና እንዳይወያዩ ለማገድ ከባለፉት ቀናት ተቃውሞችን ተከትሎ የሚደረገው ሳንሱር መጠናከሩ ተነግሯል።
በ10 ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምስሎች ተጣርተው የተወገዱ ሲሆን መደበኛ ሚዲያዎች ደግሞ ተቃውሞ ላይ ዝምታ በመምረጥ ስለዓለም ዋንጫ እና የቻይናን የህዋ ስኬት በማሳየት ላይ ተጠምደዋል።
በማዕከላዊ ሆንግ ኮንግ በሚገኘው የቻይና ዩኒቨርስቲ ትላንት ሰኞ በቻይና ላሉ ታቃዋሚዎች ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት በርካታ ተቃዋሚዎች ተሰባስበው ታይተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቻይና የራሷን የኮሮና ክትባቶች ብታመርትም በተለያዩ ሀገራት ጥቅም ላይ የዋሉትን እንደፋይዘር እና ሞደርና ያሉ የኮቪድ ክትባቶች ግን ውጤታማ እንዳልሆኑ ይነገራል።
በሁለት ዙር የሚወሰደው ፋይዘር ክትባት ከባድ የበሽታውን ደረጃ የመከላከል አቅሙ 90 በመቶ ሲሆን የቻይና ሲኖቫክ ግን 70 በመቶ ብቻ ይከላከላል።
ጠጨማሪም ክትባቱ በቂ ቁጥር ላለው ሰው አልተዳረሰም። ኮቪድ የሞት አደጋ ለጋረጠባቸው አረጋውያንም በሚገባ አልተደረሰም።
የቻይና መንግሰት ስለተቃውሞቹ በየትኛውም መንገድ የሰጠው አስተያየት የለም።
የወቅቱ ፕሬዝዳንት ዢ ጂፒንግ እንዲህ አይነት ተቃውሞ ገጥሟቸው አያውቅም። መንግሥታቸው ምን አይንት ምላሽ እንሰሚሰጥም እየተጠበቀ ነው።
በርካታ ቁጥር ያለው ተቃዋሚዎች እስርን ወይም ሳንሱርን ለመቃውም ምንም ጸሁፍ የሌለበትን ወረቀት ይዘው ታይተዋል።
ሆኖም አንዳንዶች ከዚህም ከፍ ያለ ተቃውሞ ያሰሙ ሲሆን ዢ ይውረዱ እስከማለት ደርሰዋል።
እየተከናወነ ካለው ሰፊ ሳንሱር በተቃራኒ የተቃውሞ ዜናዎች፣ ፎቶዎች እና ቪዲየዎች እና ምስሎች በማህበራዊ ሚዲያ እና መልዕክት መለዋወጫዎች ተሰራጭተው ይገኛሉ።












