የዓለም ጤና ድርጅት ለዝንጀሮ ፈንጣጣ አዲስ ስያሜ ሰጠ

የዝንጀሮ ፈንጣጣ (ኤምፖክስ) ቫይረስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዝንጀሮ ፈንጣጣ (ኤምፖክስ) ቫይረስ

የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ያንሰራራውን የዝንጀሮ ፈንጣጣ (ሞንኪፖክስ) በሽታን ስም በመቀየር ኤምፖክስ ተብሎ እንዲጠራ ወሰነ።

ድርጅቱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ቀደም ያለው የቫይረሱ ስያሜ ከዘረኝነት እና ከማግለል ጋር የተያያዘ ነው በሚል ቅሬታዎች ከተሰሙ በኋላ ነው።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ የሚለው መጠሪያ ከአገልግሎት ውጪ የሚሆነው ለአንድ ዓመት ያህል ከአዲሱ የቫይረሱ ስያሜ ጋር ጎን ለጎን ከቆየ በኋላ ነው።

ኤምፖክስ የሚለው አዲሱ ስም ላይ ውሳኔ ላይ የተደረሰው ከባለሙያዎች፣ ከአገራት እና ከአጠቃላይ ሕዝቡ ጋር ከተደረገ ረዥም ጊዜ በወሰደ ውይይት መሆኑም ተገልጿል።

የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለው አዲሱ ስያሜ በእንግሊዝኛ እና በሌሎችም ቋንቋዎች በቀላሉ ሊጠራ እና ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል።

በሰው ላይ የሚከሰተው የዝንጀሮ ፈንጣጣ መኖሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቀው በአውሮፓውያኑ 1970 ሲሆን፣ ስያሜውንም ያገኘው ቫይረሱ በሰው ላይ ከመከሰቱ በፊት ከአስር ዓመታት ቀደም ብሎ በዝንጀሮዎች ላይ የተገኘ በመሆኑ ነው።

ከዚያ ጊዜ አንስቶም የዓለም ጤና ድርጅት ለተለያዩ የበሽታ አይነቶች መጠሪያ በማውጣት በኩል ምክር ሲሰጥ ቆይቷል።

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ለበሽታዎች የሚሰጡ ስያሜዎች በንግድ፣ በጉዞ፣ በቱሪዝም ወይም ከእንስሳት ደኅንነት አንጻር የሚፈጥሩትን አላስፈላጊ አሉታዊ ተጽእኖዎችን መቀነስ ላይ ትኩረት ይሰጣል።

በተጨማሪም ከስሞች ጋር ተያይዞ በየትኛውም ባህላዊ፣ ማኅበራዊ፣ ብሔራዊ እና የጎሳ ቡድኖች ላይ ምንም አይነት ጉዳትን የማያስከትል መሆን አለበት።

በዓለም ላይ የኮቪድ ወረርሽኝ በተከሰተበት ጊዜ ድርጅቱ ለቫይረሱ የተለያዩ ዝርያዎች መለያነት “የማያገሉ” እና በቀላሉ ለመጥራት የማያስቸግሩ ያላቸውን የግሪክ ፊደላትን በመጠሪያነት ሰጥቷል።

ካለፈው ዓመት አጋማሽ ወዲህ የፈንጣጣ ቫይረስ ቤተሰብ የሆነው ዝርያ ኤምፖክስ፣ በብዛት ከሚገኝባቸው ከማዕከላዊ እና ከምዕራብ አፍሪካ አገራት ውጪ በበርካታ የዓለም አገራት ውስጥ ተስፋፍቷል።

የዚህ ቫይረስ ክስተትም የአውሮፓ አገራትን፣ ካናዳን፣ አውስትራሊያን እና አሜሪካን ጨምሮ በ29 አገራት መገኘቱ ተመዘግቧል። በዚህም ሳቢያ ለቫይረሱ በእጅጉ ታጋላጭ ናቸው የተባሉ ሰዎችን ለመከላከል የቫይረሱ የክትባት ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

የኤምፖክስ (የዝንጀሮ ፈንጣጣ) በዓለም ዙሪያ በከፍተኛ ደረጃ በመስፋፋቱ እና በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከፍተኛ ትኩሳት እና የቆዳ ሽፍታ ወይም ቁስለትን ጨምሮ ሌሎችም ምልክቶችን በማሳየታቸው፣ የዓለም ጤና ድርጅቱ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ በሽታውን አሳሳቢ የምድራችን የጤና ስጋት ነው በማለት አውጆ ነበር።

ነገር ግን ላለፉት በርካታ ወራት በዓለም ዙሪያ ያለው ዝንጀሮ ፈንጣጣ የወረርሽኝ ክስተት እየቀነስ ቆይቷል።

ለዚህም በሽታው በአሜሪካ እና በአውሮፓ አገራት ውስጥ በስፋት የተከሰተ በመሆኑ፣ አገራቱ ባካሄዱት የክትባት ዘመቻ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር እንደተቻለ ይታመናል።

በዚህ በሽታ ከተያዙት ውስጥ አብዛኞቹ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን የሆኑ ወንዶች ናቸው።