ዳክዬዎችን መንገድ በማሻገር ላይ የነበረው አሜሪካዊ በመኪና አደጋ ሞተ

አደጋው በደረሰበት አካባቢ ከጎማ የተሰሩ አሻንጉሊት ዳክየዎችንና እቅፍ አበባዎችን በርካቶች በማስቀመጥ ኃዘናቸውን ገልጸዋል

የፎቶው ባለመብት, CBS

በካሊፎርኒያ ነዋሪ የሆነ አሜሪካዊ ዳክዬዎችን መንገድ ለማሻገር በመርዳት ላይ እያለ በመኪና ተገጭቶ ህይወቱ አለፈ።

ግለሰቡ አደጋው ከመድረሱም በፊት ዳክዬዎቹ የተጨናነቀውን መስቀለኛ መንገድ ለማሻገር ሲሞክር እንደነበርም የአካባቢው ፖሊስ አሳውቋል።

የ41 አመቱ ኬሲ ሪቫራ መኪናውን አቁሞ ዳክዬዎቹን በመርዳት ላይ እያለም አንድ ወጣት እንደገጨው የከተማዋ ፖሊስ ተናግሯል።

ኬሲ እየዋለሉ የነበሩትን ዳክዬዎች ካሻገረም በኋላ አደጋ እንደደረሰበት የዓይን እማኞች ተናግረዋል።

በግለሰቡ አደጋ ምክንያት እስካሁን በቁጥጥር ስር የዋለ አካል የለም።

“ግለሰቡ በመንገዱ መተላላፊያ ላይ የነበሩትን አንዳንድ ዳክዬዎችን ለመርዳት እየሞከረ ነበር” በማለት የሮክሊን ፖሊስ ዲፓርትመንት መግለጫ አውጥቷል።

“ቦሌቫርድ ወደተባለው መንገድ እያመራ የነበረ ወጣት አሽከርካሪ በመንገድ ላይ የነበረውን ኬሲን ገጭቶታል” ብሏል።

ሰመር ፒተርሰን የተባለች የዓይን እማኝ ለሲበኤስ የዜና ተባባሪ ሐሙስ ከምሽቱ 2፡15 አካባቢ የደረሰውን የመኪና አደጋ ልጆቿም መመልከታቸውን ተናግራለች።

“ልጆቼ ሰውየው ዳክዬዎቹን ሲያሻግር እያዩ ‘እውይ እንዴት ደስ የሚል ነገር ነው’። ‘ምን አይነት ደግ ሰው ነው’ እያሉም በነበረበት ወቅት ነው ድንገት ከየት እንደመጣ ያላወቅነው መኪና የገጨው” ብላለች ግለሰቧ።

አደጋው በደረሰበት አካባቢ ከጎማ የተሰሩ አሻንጉሊት ዳክየዎችንና እቅፍ አበባዎችን በርካቶች በማስቀመጥ ኃዘናቸውን ገልጸዋል።

በግለሰቡ ቤተሰቦችና ዘመዶች በተቋቋመ የገንዘብ ማሰባሳቢያ ላይም ኬሲ ልጆቹን ከመዋኛ ስፍራ ወደ ቤታቸው እየወሰዳቸው ባለበት ወቅት አደጋው እንደደረሰበት አስፍሯል።

“አንዲት እናት ዳክዬ ከልጆቿ ጋር ጋር ሆና በተጨናነቀ መስቀለኛ መንገድ ላይ ለመሻገር ስትታገል አስተውሏል” ይላል።

“ኬሲ በጣም ሩህሩህ፣ ደግ አስገራሚ ባል እና አባት ነበር” ይላል በዚህ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ድረ ገጽ ላይ በሰፈረው ጽሁፍ።

“ይህችን አለምም ከመሰናበቱ በፊትም የፈጸመው የመጨረሻው ተግባር የርህራሄው ማሳያ ነው” ይላል።

የሮክሊን ፖሊስ ዲፓርትመንት እስካሁን ድረስ በቁጥጥር ስር የዋለ ሰው አለመኖሩን ገልጾ “አደጋው በምርመራ ላይ ነው” ብሏል።

የሮክሊን ፖሊስ ኃላፊ ስኮት ሆሪሎ ለኤንቢሲ እንደተናገሩት በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኘው አሽከርካሪ የወንጀል ክስ ሊመሰርትበት እንደማይችል ጠቁመዋል።