ዋትስአፕ ተጠቃሚዎች የላኩትን መልዕክት ‘ኤዲት’ ማድረግ እንዲችሉ ሊፈቅድ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዋትስአፕ የተሰኘው መልዕክት መላላኪያ ድር ተጠቃሚዎች መልዕክታቸውን ከላኩ በኋላ አርትዖት ማድረግ እንዲችሉ ሊፈቅድ ነው።
የዋትስአፕ ተፎካካሪ የሚባሉት ቴሌግራምና ሲግናል ለተጠቃሚዎች ይህን ይፈቅዳሉ።
ኩባንያው እንዳለው መልዕክት ከተላከ በኋላ እስከ 15 ደቂቃ ባለው ጊዜ ‘ኤዲት’ ሊደረግ ይችላል።
ዋትስአፕ የግዙፉ አሜሪካዊ ድርጅት ሜታ አካል ሲሆን ፌስቡክ እና ኢንስታግራምም እንዲሁ የሜታ ቤተሰብ ናቸው።
ይህ አዲሱ ቴክኖሎጂ ለ2 ቢሊዮን የዋትስአፕ ተጠቃሚዎች በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ይፋ ይሆናል ተብሏል።
በሕንድ ብቻ 487 ሚሊዮን የዋትስአፕ ተጠቃሚዎች አሉ።
“የፊደል ስህተት ከማስተካከል ጀምሮ ቃላትን ጨምሮ መልዕክቱን ማስተካከል የሚያስችልዎ ቴክኖሎጂ አምጥተን እርስዎ የሚልኩትን መልዕክት እንዲቆጣጠሩ አድርገናል” ሲል መተግበሪያው ሰኞ ዕለት መግለጫ ለቋል።
“ማድረግ የሚጠበቅብዎ የላኩትን መልዕክት ተጭኖ መቆየት፤ ከዚያም አርትዖት የሚለውን መርጦ በ15 ደቂቃ ውስጥ ማስተካከል ነው።”
መልዕክቱ የደረሰው ሰው እንዲረዳ ‘ኤዲት’ የተደረጉ መልዕክቶች አርትዖት እንደተደረገላቸው የሚያሳይ ምልክት ይኖራቸዋል።
ነገር ግን መልዕክቱ ምን ያህል ‘ኤዲት’ እንደተደረገ ከሚልከው ሰው በቀር ማንም አያውቅም።
ቴሌግራም እና ሲግናል የተሰኙት የዋትስአፕ ተቀናቃኝ ኩባንያዎች ተጠቃሚዎች መልዕክታቸውን ‘ኤዲት’ እንዲያደረጉ ይፈቅዳሉ።
‘ኤዲት’ የተሰኘውን አማራጭ ለማሕበራዊ ሚዲያ ያስተዋወቀው ፌስቡክ ሲሆን ጊዜው 10 ዓመት ሊደፍን ጥቂት ቀርቶታል።
በወቅቱ ፌስቡክ ከግማሽ በላይ ደንበኞቹ በስልክ ስለሚጠቀሙና ተንቀሳቃሽ ስልክ ደግሞ ለስህተት የተጋለጠ ስለሆነ ነው ይህን ያስተዋወቀው።
ፌስቡክ ሲጠቀሙ ሰዎች አርትዖት ያደረጉባቸው መልዕክቶች ‘ኤዲትድ’ የሚል ስያሜ ይሰጣቸዋል።
አልፎም ደንበኞች ምን ያክል ጊዜ የላኩትን መልዕክት ‘ኤዲት’ እንዳደረጉት ማየት ይቻላል።
ባለፈው ዓመት የኢላን መስክ ማሕበራዊ ገፅ ትዊተር ከፍለው አገልግሎት ለሚያገኙ ተጠቃሚዎቹ ‘ኤዲት’ የተሰኘውን አማራጭ ማቅረቡ አይዘነጋም።
ተጠቃሚዎች ‘ትዊት’ ካደረጉ በኋላ ባለው 30 ደቂቃ ‘ኤዲት’ ማድረግ ይችላሉ።












