ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሩሲያ እና የቤላሩስ አትሌቶች በፓሪስ ኦሊምፒክ በግል እንዲሳተፉ ሃሳብ አቀረበ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ የሩሲያ እና ቤላሩስ አትሌቶች በቀጣይ ዓመት በሚደረገው የፓሪስ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በገለልተኛ ባንዲራ እንዲሳተፉ ሃሳብ አቀረበ።
ገና የመጨረሻ ውሳኔ ያልተሰጠው ይህ ምክረ ሃሳብ፤ አትሌቶቹ እንደ ግለሰብ እንጂ በቡድን ሆነው በኦሊምፒክ አይሳተፉም ተብሏል።
የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ በዩክሬን እየተካሄደ ያለውን ጦርነት የሚደግፉ ወይም ከጦር ሠራዊት ጋር ውል የገቡ አትሌቶች በግልም ቢሆን በውድድሩ እንዲሳተፉ እንደማይፈቀድላቸው ለዓለም አቀፍ ፌዴሬሽኖች እና መረሃ ግብር አዘጋጆች ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
ኮሚቴው በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ እና የሚላን 2026 የክረምት ኦሊምፒክ ተፈጻሚ የሚሆነው የዚህ ውሳኔ አተገባበርን በቅርበት እየመረመርኩ ነው ብሏል።
የሁለቱ አገራት ዜጎች በዓለም አቀፍ ውድድሮች እንዳይሳተፉ ተደጋጋሚ ጥሪ ሲቀርብ ቆይቷል።
ከሳምንታት በፊት ፖላንድ ኮሚቴው የሩሲያ እና የቤላሩስ ዜጎች በፓሪስ ኦሊምፒክ እንዲሳተፉ የሚፈቅድ ከሆነ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አገራት ከውድድሩ አራሳቸውን ሊያገሉ ይችላሉ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥታ ነበር።
ፖላንድ፣ ሊቱዋኒያ፣ ኢስቶኒያ እና ላትቪያ የሩሲያ እና ቤላሩስ አትሌቶች የኦሊምፒክ ተሳትፎን አጥብቀው የሚቃወሙ ቢሆንም፣ ኮሚቴው ግን የትኛውም አትሌት በፓስፖርቱ ምክንያት ከውድድር መታገድ የለበትም የሚል አቋም ሲንጸባርቅ ቆይቷል።
“በዓለም አቀፍ ውድድሮች የሩሲያ እና የቤላሩስ ፓስፖርትን የያዙ አትሌቶች ተሳታፊ ሊሆኑ ይችላሉ” ሲሉ የኮሚቴው ፕሬዝዳንት ቶማስ ባህ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ የሁለቱን አገራት ፓስፖርት የያዙ አትሌቶች ከሜዳ ቴኒስ እስከ የብስክሌት ውድድሮች በአሜሪካ እና በአውሮፓ እየተሳተፉ መሆኑን አስታውሰው በአንዳቸውም ውድድር ላይ አትሌቶቹ ተሳታፊ በመሆናቸው የደኅንነት ችግር አልተከሰተም ብለዋል።
ዩክሬን ከዚህ ቀደም የሁለቱ አገራት አትሌቶች በውድድሩ ተሳታፊ የሚሆኑ ከሆነ በውድድሩ አልገኝም ያለች ሲሆን፣ ከቀናት በፊት ደግሞ የዩክሬን የስፖርት ሚኒስትር ቫድይም ጉተሳኢት ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ የሩሲያ እና የቤላሩስ አትሌቶች በፓሪስ ኦሊምፒክ ሊወዳደሩ ይችላሉ ማለቱን አጥብቀው ተቃውመዋል።
ዩክሬን ላይ ወራረ የፈጸመችው ሩሲያ እና አጋሯ ቤላሩስ በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የታገዱ ሲሆን፤ እግዱ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በሁለቱ አገራት እንዳይዘጋጅ ከመከልከሉ በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የሁለቱ አገራት ሰንደቅ ዓላማ እንዳይወለበለብ፣ ብሔራዊ መዝሙራቸው እንዳይሰማ እንዲሁም የአገራቱ ብሔራዊ ምልክቶች እንዳይታዩ አግዷል።
በዚህ ወር ከተካሄደው የሴቶች የቦክስ ቻምፒየንሺፕ ላይ የሩሲያ እና ቤላሩስ አትሌቶች በአገራቸው ሰንደቅ ዓላማ ተወክለው እንዲሳተፉ መፈቀዱን ተከትሎ አሜሪካ፣ ታላቋ ብሪታኒያ እና አየርላንድን ጨምሮ በርካታ አገራት በተቃውሞ ከውድድሩ እራሳቸውን አግልለዋል።












