“አንዳንዴ ኮሜዲውን የምጽፈው እያለቀስኩ ነው” ኮሜዲያን እሸቱ መለሰ

ኮሜዲያን እሸቱ ተምታታብን የተሰኘውን የኮሜዲ ሥራውን ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ በቢሾፍቱ ሲያቀርብ

የፎቶው ባለመብት, eshetu

የምስሉ መግለጫ, ኮሜዲያን እሸቱ ተምታታብን የተሰኘውን የኮሜዲ ሥራውን ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ በቢሾፍቱ ሲያቀርብ

ለኮሜዲያን እሸቱ መለሰ የኮሜዲ ሕይወት ንሸጣ ከፍተኛውን ድርሻ ያበረከተው ጥቁር አሜሪካዊው ኬቨን ኸርት ነው።

በእርግጥ በእሸቱ ልብ ውስጥ የኮሜዲያን ስሜት ለመቀስቀስ ደቡብ አፍሪካዊው ኮሜዲያን ትሬቨር ኖዋም የራሱ አስተዋጽኦ አለው።

ኮሜዲያን እሸቱ መለሰ የተማረው የትያትር ጥበብ ነው።

አዳማ ያደገው እሸቱ፣ ከልጅነቱም በቤተክርስቲያን ቴአትር ይሰራ ነበር።

ኮሜዲያን እሆናለሁ የሚል ህልምም ሆነ ቅዠት ከዚያ በፊት አልነበረውም።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከተመረቀ በኋላ ሥራ አጥቶ ጋራዥ ውስጥ ረዳት ሆኖ ሠርቷል።

በካልዲስ ኮፊ አስተናጋጅም ነበረ።

ዛሬ ግን ከኮመዲው ባሻገር በዩቲዩብ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ተከታዮች አሉ።

እሸቱ ለገዳም ውሃ ለማስገንባት፣ ገዳም እና መስጂድ ለመገንባት፣ እንዲሁም በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች በዩቲዩብ በቀጥታ ሥርጭት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ አሰባስቧል።

ለሜቄዶኒያ የአረጋውያን እና የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ደግሞ ሦስት ቀን በፈጀ የቀጥታ ስርጭት 3 ሚሊዮን ዶላር ማሰባሰብ ችሏል።

ኮሜዲያን እሸቱ በዶንኪ ቲዩብ አንቂ አንደበቶች፣ ጀግና መፍጠር፣ ድንቅ ልጆች፣ ኢትዮጵያዊ ነን እና ሌሎች ተወዳጅ ፕሮግራሞችን ያቀርባል።

በዩቲዩብ ካቀረባቸው ሥራዎች መካከል ከ5 ሚሊዮን በላይ ተመልካች ያገኘ ቪዲዮ አለው።

ከሰባት በላይ የመድረክ ሥራዎችን አቅርቦ ተመልካች በግፊያ ተመልክቶለታል።

ቢቢሲ ኮሜዲያን እሸቱን ስለሥራዎቹ እና ስለስኬቱ ጠይቆታል።

“ኮሜዲን የጀመርኩት ካረጀሁ ነው”

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኮሜዲያን እሸቱ ወደ ኮሜዲ የገባበትን ጊዜ ሲናገር “እርሱን እንኳ ካረጀሁ ካፈጀሁ በኋላ ነው። ከሸመገልኩ፣ ከጨረጨስኩ በኋላ ነው” ይላል።

እኤአ በ2013 ‘Let Me Explain’ የሚል የጥቁር አሜሪካዊው ኮሜዲያን ኬቨን ኸርት ሥራ ወጥቶ ነበር።

ይህንን ሲያይ “. . .በደስታ፣ ልቤ ላይ በጣም ስቃይ ይሰማኝ ነበር። ኮሜዲውን 17 ጊዜ ያህል ደጋግሜ አይቸዋለሁ። ያኔ ነው ውስጤ ላይ ኮሜዲ እንዳለ እና መሥራት እንዳለብኝ ያወቅኩት።”

ከዚያ በኋላ የመጀመሪያ ሥራ የሆነውን ጣዝማ ማር ጽፎ ለሕዝብ አቀረበ።

በመቀጠል ዘመነ ፍሰሃ፣ የት ነበርን፣ ነግ በኔ፣ . . .ተምታታብን፣ የተሰኙ በአጠቃላይ ሰባት የኮሜዲ ሥራዎችን ለሕዝብ አቅርቧል።

ቢቢሲ ኮሜዲያን እሸቱን አሁን በዩቲዩብ በምታቀርባቸው ዝግጅቶች ዝነኛ ሆነሃል፣ ነገር ግን አሁንም የኮሜዲ ሥራዎችን መድረክ ላይ ታቀርባለህ። ለምን? ሲል ጠይቆታል።

“መጀመርያም ኮሜዲያን የሆንኩት ውስጤ የሚያምንባቸውን እና በጣም ጠቃሚ ቁም ነገሮች ስላሉ እና ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ መሆን የሚያስችሉንን ርዕሰ ጉዳዮች ለሕዝብ ለማድረስ ነው” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

ከዚህ ባሻገር ደግሞ መጀመሪያ ወደ ሕዝብ የመጣው በኮሜዲ ሥራዎቹ በመሆኑ፣ ያንን ተመልካች በማክበር ማሳቅ ማዝናናት እንዳለበት ስለሚያምን ነው።

ኮሜዲያን እሸቱ የሥራዎቹ ዓላማ በዋናነት ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ መሆኑን ያነሳል።

“ጭቆና በጣም ያንገበግበኛል” ይላል ኮሜዲያን እሸቱ። ለዚህም የእስካሁኖቹnእ ሥራዎቹን በአስረጅነት ይጠቅሳል።

“ኮሜዲውን የምጽፈው አንዳንዴ እያለቀስኩ ነው።. . .ስጽፍ ሪሰርች አድርጌ ነው። ለምሳሌ ለጥምቀት የተገደለውን ልጅ ኮሜዲ ከመሥራቴ በፊት አባቱን ቃለ መጠይቅ አድርጌያቸው ነው።

“ማንኛውንም ሥራ ከመሥራቴ በፊት ሚዲያ ላይ በደንብ አገላብጬ፣ ሰው ቀጥሬ ጥናት አስደርጌ፣ ለሕግ ባለሙያ፣ [ለኪነ ጥበብ ] ባለሙያ አስገምግሜ ነው። ኢፍትሀዊነት ጭቆና ልቤ ውስጥ ገብቶ በጣም ሲነካኝ ሲያስለቅሰኝ ልቤ ውስጥ የገባውን ድምጽ የማወጣው በኮሜዲው ነው።”

በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ አልቀልድም የምትልበት ጉዳይ አለ? ሌላው ቢቢሲ ለእሸቱ ያቀረበው ሌላው ጥያቄ ነበር።

“አዎ፤ ርዕሰ ጉዳይ ሳይሆን አስተሳሰብ አለ። የሌሎችን ሃይማኖት የሚያንቋሽሽ፣ የሌሎችን እምነት ፍልስፍና፣ ቋንቋ፣ ባሕልን የሚያንቋሽሽ፣ በሕዝብ ውስጥ ቂም፣ ጥላቻ እና ንቀትን በሚፈጥር ሃሳብ ዙሪያ በፍፁም አልቀልድም።”

ለመሆኑ ኮሜዲያን እሸቱን የሚያስቀው ኮሜዲያን ማን ነው? እሸቱ ፍልፍሉን ያነሳል “. . . ድሮ በተለይ ገና እንደመጣ ‘አባባ አቡሽ’ የሚል ኮሜዲ ነበረው። ክበበው በጣም በጣም ያስቀኛል” ምንም ቢያደርግ የሚያስቀው ግን ኮሜዲያን ደረጀ ሀይሌ መሆኑን ይናገራል።

ከውጪስ የምትመርጠው አለ? የቢቢሲ ቀጣይ ጥያቄ ነበር።

“ድሮ አርዓያዎቼ ኬቨን ኸርት እና ትሬቨር ኖዋ ናቸው እል ነበር። አሁን አሁን ግን ሳያቸው አቋማቸው ይዋዥቅብኛል። አሁን ኬቨን ኸርት አልኮል እያስተዋወቀ ነው። . . .እንደዚያ ሲሆን የኔ አርዓያዬ መሆኑ ያቆማል። ቀልዶቹም እስካሳቀ ድረስ የማይነካው ነገር የለም። አሁን ዝም ብዬ ሥራዎቻቸውን አያለሁ እንጂ አርዓያዎቼ ናቸው አልልም።”

ኮሜዲያን እሸቱ መለሰ

የፎቶው ባለመብት, eshetu

ዝነኛ ለመሆን ማናጀር የቀጠረው ኮሜዲያን

እሸቱ በአንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ እየሰራ እያለ ነው የስታንድ አፕ ኮሜዲ በተለያዩ መድረኮች ለማቅረብ አቅዶ መሥራት የጀመረው።

ሥራዎቹን በሚያስቀምጠው የጊዜ ገደብ ግን ጽፎ ለመጨረስ ሳይችል ቀረ። ያኔ ለምን ማናጀር አልቀጥርም ሲል ወሰነ።

“. . .ሰው ማናጀር የሚቀጥረው ‘ፌመስ’ ከሆነ በኋላ ነው። እኔ ግን ማናጀር የቀጠርኩት ‘ፌመስ’ ለመሆን ነው። መስመሩ እንደሆነ፣ አስፈላጊ እንደሆነ በማወቅ” ይላል።

እውነትም የቀጠረው ማናጀር ሥራዎቹ በታቀደላቸው ጊዜ እንዲያልቁ እና ለመድረክ እንዲበቁ በማድረግ ረገድ ውጤታማ ሥራ መሥራቱን እሸቱ ዛሬ ላይ ቆሞ ይመሰክራል።

እስካሁን ድረስ ሰባት አንድ ሰዓት እና ከዚያ በላይ የሆኑ የኮሜዲ ሥራዎችን በአዲስ አበባ የተለያዩ መድረኮች አቅርቧል።

ወደ ባሕርዳር፣ አዳማ፣ ጎንደር፣ ሐዋሳ፣ ቢሾፍቱ ተጉዞ ለአድናቂዎቹ ሥራዎቹን አድርሷል።

ከአገር ውጭ ግን ያሉ አድናቂዎቹ እስካሁን ድረስ በኮሜዲ ሥራዎቹ አላገኙትም።

ለምን?

እሸቱ ብቻውን ወደ ባሕር ማዶ ተሻግሮ አድናቂዎቹን ማዝናናት ውጤታማ ነው ብሎ አያስብም።

ራሴን እንደ ፕሮፌሽናል ኮሜዲያን ነው የማየው የሚለው እሸቱ “ስታንዳፕ ኮሜዲ ስሠራ ከማናጀሬ ውጪ የትም ልሄድ አልችልም. . .” ይላል።

ከዚህ ውጪ ደግሞ “. . .ማናጀር ብቻ ሳይሆን ኮሜዲውን ሳጠና አንዳንድ በሳውንድ ኢፌክቶች የምሰራቸው ቀልዶች ስላሉ፣ ያንን የሚያጫውት ዲጄ አለኝ። ሙዚቃ የሚያጫውት ሳይሆን ሳውንድ ኢፌክት የሚያጫውት ነው።

“እና ይህንን ላይቭ ዲጄ እና ማናጀሬን ይዤ እንድመጣ ፍቀዱልኝ ስላቸው ብዙዎቹ ፈቃደኛ አይደሉም። ድሮ ማለት ነው። እነርሱ የሚያስቡት በቃ የሆነ አገር ሄደን እንደምንጠፋ ነው። ወይ ደግሞ ሆቴል እና ቲኬት ውድ እንደሚሆንባቸው ነው። እኔ ደግሞ ፕሮፌሽናል ባለሙያዎች ይዤ ለመሄድ ብቁ እስክሆን ድረስ መሄድ የለብኝም ብዬ ነው።”

እሸቱ ከኮሜዲው ባሻገር በዩቲዩብ ወደ ሁለት ሚሊዮን ተከታዮችን ማፍራት ችሏል።

በዚህም 58 ሠራተኞችን ቀጥሮ እያስተዳደረ ይገኛል።

የማናጀሬ ጥረት 57 ተጨማሪ ሰው ወለደ ይላል እሸቱ ይህንንም ሲያስረዳ።

የኮሜዲም ሆነ የዩቲዩብ ሥራ ለብቻ አልያም በጥቂት ሰው ተሰርቶ ውጤታማ መሆን እየተቻለ ለምን ይህን ያህል ሰው መቅጠር ፈለገ? ቢቢሲ ያቀረበለት ጥያቄ ነው።

“ሰው መቅጠር ምርጫ አይደለም። ግዴታ ነው። ዶንኪ ቲዩብ በአሁን ሰዓት 58 ሠራተኞች አሉት። በአንድ የቀጥታ ሥርጭት ሦስት ሚሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ ችሏል። እዚህ ድረስ ማደግ ከፈለግክ ሰው መቅጠር አለብህ” ሲል ይመልሳል።

በዩቲዩብ ላይ 'ፉገራ፣ ኮመንተሪ፣ ሪያክሽን እየሰራህ ራስህ ኤዲት እያደረግክ እየለቀክ 60 እና 70 ሺህ ሰው ያይልሀል። ገቢህም እውቅናህም በዚያው ልክ ትንሽ ነው የሚሆነው ሲል ያክላል።

እሸቱ ሰው የምቀጥረው ድርጅቴ ትልቅ እንዲሆን እንዲያድግ ከመፈለግ፣ ከማሰብ ነው ሲል ያስረዳል።

“ሰው ሳትቀጥር፣ እቃ ሳትገዛ ደግሞ ውጤታማ አትሆንም። . . . ሦስት ቀን ላይቭ ላይ ለመቆየት በቂ የሰው ኃይል ሊኖረኝ ይገባ ነበር። በቂ የሠው ኃይል ሳይኖር ላይቭ ገብቼ ይህንን ያህል ቀን እንዴት ለመቆየት ላስብ እችላለሁ?” ሲል መልሶ ራሱ ይጠይቃል።

የሰው ኃይል ባነሰ ቁጥር የሚታሰበው ሃሳብ እያነሰ፣ ፈጠራ እና እድገት እየተገደበ እንደሚሄድ በማከል፣ በተቃራኒው በማድረጉ “ሃሳብህ ቡርቅቅ ይላል። ምንም አይገድብህም። 'ዘ ስካይ ኢዝ ዘ ሊሚት' [ምንም የሚያግድህ ነገር የለም] እድገት የሚመነጨው ከዚህ ስለሆነ ነው” ሲል ይገልጻል።

ኮሜዲያን እሸቱ መለሰ

የፎቶው ባለመብት, eshetu

ሕልሙ የኢትዮጵያን ሚዲያ መቀየር የሆነው እሸቱ

እሸቱ ስታንድአፕ ኮሜዲ መሥራት ከጀመረ በኋላ በሕዝብ ዘንድ ዝናን ለማትረፍ ከአንድ ዓመት በላይ እንዳልፈጀበት ያስታውሳል።

“. . . የመጀመሪያው ሥራ ዘመነ ፍሰሃ የሚል መስከረም ላይ ተለቀቀ። በቴሌቪዥን ላይ በጣም ተወደደ። በተመልካች ጥያቄ እየተባለ ስምንት ጊዜ ተደገመ። ከዚያ 'የት ነበርን' የሚል ሰራሁ እሱም ቲቪ ላይ ታየ በጣም ተወደደ። ከዚያ ፋሲካ ላይ 'ነግ በኔ' የሚል ስደግም ተቀጣጥሎ ቁጭ አለ።. . . በዓመት ውስጥ ዝነኛ ሆኜ አንዳንድ ሥራዎች በገንዘብ ለአንድ መድረክ እስከ 100 ሺህ ብር ድረስ እየተከፈለኝ ወደ መሥራት የገባሁት በአንድ ዓመት ውስጥ ነው።”

ዶንኪ ቲዩብ ላይ በርካታ ተከታዮችንም ለማግኘት እንዲሁ ከአንድ ዓመት በላይ አልወሰደብኝም ይላል። እንዴት?

“...ድሮ ስታንድ አፕ ኮመዲውን እንጭን ነበር። ግን በሦስት ወር አንዴ ስለሚጫን ብዙም ሰው የእኔ መሆኑን አያውቀውም። ልክ የቤተሰብ ጨዋታን እየሰራሁ የኮሮና ወረርሽኝ ሲከሰት እና ከቤታችሁ ሥሩ ሲባል ዩቲብን ቤት ሆነን ጀመርን።

“በዓመት ውስጥ ለአገርሽ ያብቃሽ፣ ጀግና መፍጠር፣ የሚባሉ ፕሮግራሞች ሀሪፍ ሆነው ልክ ዓመቱ እንዳለቀ ሁለተኛው ዓመት ላይ ድንቅ ልጆችን ጀመርን። በዓመት ውስጥ ግን በሁለት እግሩ ቆሞ ደመወዝ መክፈል ችሎ የቢሮ ኪራይ መክፈል ችሎ ጥሩ ሆኖ ነበር።”

አሁን ሀብታም ሆነሃል?

አዎ። እንግዲህ ለምሳሌ ቤት የለኝም። ባንክ ተቀማጭ ካሽ ምናምን የለኝም። ዛሬ እኔ እና አንተ ስናወራ በድርጅቱ ስም 10 ሺህ ወይንም 20 ሺህ ብር ይሆናል ባንክ አካውንት ላይ ያለው። ግን ሀብቴ ምንድን ነው በቀደም እንዳየኸው. . . ተደራሽነቴ እና ተጽኖ ፈጣሪነቴ አለ። ለምሳሌ አንድ ሰው እኔን ማስታወቂያ ማሰራት ቢፈልግ የምጠይቀው ብር ቀላል አይደለም።

ዶንኪ ቲዩብ ላይ ለማስተዋወቅ ፈልገህ ብትመጣ እንዲሁ ዝም ብለህ በቀላሉ ማስተዋወቅ አትችልም።... ተጽዕኖው አድጓል። እንደ ዶንኪ ቲዩብ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችል ሚዲያ መፍጠር ችለናል። ሀብት ካልክ እርሱ ነው ሀብት እንጂ በገንዘብ ደረጃ ካሽ ንብረት ቤት የምንለው ነገር የለም። አብዛኛው ሀብት ያለው እዚያው ዶንኪ ቲዩብ ላይ ስለሆነ ማለት ነው።

እሸቱ በቀጥታ ሥርጭት ከአሜሪካ እና አውሮፓ ለሜቄዶንያ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ያዋጣው ሰው ብዛት 12 ሺህ መሆኑን ይናገራል።

ይህንንም ሲመለከት ለበጎ ዓላማ መዋል የሚችል እና በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ከአገሩ ርቆ የሚኖር ኢትዮጵያዊ መኖሩን አስተውሏል።

ይህንንም በማንሳት “እኔ እንግዲህ ሚዲያን ለአዎንታዊ ለውጥ እንጠቀም ነው የምለው” ይላል።

ዶንኪ ቲዩብ የሚመለከቱ ሁሉ ከዚህ ቀደም ዩቲዩብ ሐሰተኛ ዜና ወይም ሰበር ዜና ካልሰራህ አልያም ሰው ካልተሳደብክ በዩቲዩብ ብር አይገኝም የሚለው አመለካከታቸው ሙሉ በሙሉ መቀየሩን ይናገራል።

“እሱ ተሰብሮ አሁን አንዴት አድርጌ እንደ ዶንኪ ቲዩብ ልሁን?” የሚሉ ሰዎች መፈጠራቸውንም ይገልጻል።

እሸቱ ዩቲዩብን ለበጎ ዓላማ ተጠቅመው ለመሥራት የሚፈልጉ 110 ወጣቶችን በመሰብሰብ “የዶንኪ ቲዩብን የስኬት ምሥጢር” እያስተማረ መሆኑን ይናገራል።

እነዚህ ወጣቶች ወደ ሥራ ሲገቡ የዩቲዩቡን መልከዓ ምድር በመቀየር ረገድ በጎ ተጽዕኖ እንደሚኖራቸው ተስፋ አድርጓል።

“ስለዚህ የእኔ የመጨረሻው ሕልም የኢትዮጵያን የሚድያ ኢንዱስትሪ መቀየር ነው።”

በዩቲዩብ ባልተለመደ መልኩ ዶንኪ ቲዩብ ከትልልቅ የልማት ተቋማት፣ ባንኮች፣ ፋብሪካዎች ጋር ይሰራል።

ዶንኪ ቲዩብ ከፖለቲካ፣ ከዘረኝነት ሃይማኖትን ከሚያጎድፍ ነገር ነጻ ሆኖ ከቀጠለ ትልልቅ ተቋማት መጥተው ያስተዋውቃሉ የሚል ጠንካራ እምነት ከመጀመሪያው አንስቶ እንደነበረው ይናገራል።

በዚህም የተነሳ በዩቲዩብ የሚፈልጉትን ያህል ገንዘብ መሥራት ባልቻሉበት ጊዜ እንኳ ተጠንቅቀው መቆየታቸውን ይናገራል።

“እኛ ገና ዩቲዩብ ስንጀምር አንዱ መርኅ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ተቋማት መጥተው ዶንኪ ቲዩብ ላይ ያስተዋወቃሉ። ስፖንሰር ይሆናሉ የሚል አቋም ነበረን” ይላል።

“...ብዙ የኪሳራ ወራት አሳልፈናል። ተጠንቅቀን ገለልተኛ የሆነ ብራንድ በመገንባታችን እና ዓላማችንን በማወቃችን...እዚህ ደርሰናል” ይላል።

ዛሬ ታድያ የዶንኪ ቲዩብን በር ድርጅታቸውን ለማስተዋወቅ ከሚያንኳኩት ተቋማት መካከል የቢራ ፋብሪካዎች ይገኙበታል።

የኮሜዲያን እሸቱ መለሰ መልስ አጭር ነው።

“ማኅበረሰብ አይገነባም” የሚል።

ከአገር ውስጥ ባሻገር ከባሕር ማዶ የቁማር እና ጌሚንግ ድርጅቶች ከፍተኛ ተከታይ ባለው የዩቲዩብ ገጽ ላይ ምርታቸውን ለማስተዋወቅ ይጠይቃሉ።

“እኛ ትውልዱን ወደ አልባሌ ነገር የሚወስዱ ከሆነ በፍፁም አንሰራም፤ የዛሬ ስምንት ዓመት እንደ ጀመርን ሳንባንን የሠራናቸው ካሉም ይቅርታ እንጠይቃለን” ይላል እሸቱ።

ለተለያዩ የእምነት ተቋማት፣ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች እንዲሁም ለሜቄዶኒያ 3 ሚሊዮን ዶላር አሰባስበሃል። ከዩቲዩብ ሥራዎችህ መካከል 5 ሚሊዮን በላይ ተመልካች ያገኘ ቪዲዮ አለህ፣ ከሰባት በላይ በርካታ ሕዝብ የተመለከታቸው የመድረክ ሥራዎችን አቅርበህ። ከእነዚህ ሁሉ የበለጠ ደስታን የፈጠረልህ የቱ ነው?

(ረዥም ዝምታ)...ብቻ ከባድ ነው ለመምረጥ። በየጊዜው ስሜቱ ይለያያል። ስታንድ አፕ ኮሜዲው በጣም ያረካኛል። አንዳንዴ ደግሞ የገንዘብ ማሰባሰቡ ሥራ የማይቻል የሚመስሉ ሲቻሉ ሳይ በጣም ደስታዬ ከፍ ይላል።

ለምሳሌ 1 ሚሊዮን ዶላር ለአሜሪካው ገዳም የሰበሰብን ጊዜ፣ ደስታዬ ትልቅ ነበር። አሁን ደግሞ የሜቄዶኒያው ትልቅ ነገር ነው። አንዳንዴ በድንቅ ልጆች በጣም የምደሰትበት ጊዜ አለ። አንዳንዴ ደግሞ...ይገርማል በጣም ፈታኝ ጥያቄ ነውአ፣ እንደዚህ ለይቼ ስቤው አላውቅም።

እኔ ሁልጊዜ የሚያስደስተኝ እና የደስታ ስሜት እንዲሰማኝ የሚያደርገው ሥራው ሲፈትነኝ (ቻሌንጅ) ሲያደርገኝ ነው። አሁን ሁለት ሚሊዮን ዶላር ሰብስብ ብትለኝ የሚሰጠኝ የተለየ ደስታ ላይኖር ይችላል። ግን 20 ሚሊዮን ዶላር ሰብስብ ብትለኝ በጣም ተደስቼ በጣም ኢነርጀቲክ ሆኜ ነው የምሰራው። አዲስ ነገር መሆኑ እና ቻሌንጅ የሚያደርግ መሆኑ እና ሥራው ሲሳካ እርካታዬ ይጨምራል። እንደዚያ አይነት ስሜት ነው ያለኝ።

ኮሜዲያን እሸቱ መለሰ

የፎቶው ባለመብት, eshetu

ለኮሜዲያን እሸቱ ከባድ የሆነው ነገር

እጅግ በጣም ፈታኝ ነገር ግን ሚዲያ ላይ የማይወራ ጉዳይ ቢኖር ድርጅት ማስተዳደር ምን ያህል ከባድ ስለመሆኑ ነው ይላል እሸቱ።

የዶንኪ ቲዩብ ሠራተኞች ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ እና ሥራዎች እርሱ በሚጠብቃቸው ልክ ሳይሰሩ ሲቀሩ ከሠራተኞቹ ጋር ይጨቃጨቅ እና ይጋጭ እንደነበር ያስታውሳል።

ይህ ደግሞ “እኔ መጥፎ ሰው ነኝ ማለት ነው” የሚል አለመካከት እንዲያድርበት እና ከራሱ ጋር እንዲጋጭ አድርጎት ያውቃል።

በዚህም የተነሳ ከሰው ጋር ከሚጋጭ አልያም ሥራው ከሚበላሽ ቢሮ አድሮ መሥራትን ይመርጥ ጀመር።

ሠራተኛውም በዚያው ልክ የማያስብ ከሆነ መቆጣት እና መጨቃጨቅ ግን አልቀረለትም።

“ከሠራተኞቼ የምጠብቀውን ሳላገኝ ስቀር ይኼ ነገር ይቅርብን። ዝም ብለን አራት አምስት ሆነን ስታንድ አፕ ኮሜዲዬን እየሰራሁ የቲቪ ሾው ሆስት እያደረግኩኝ፣ ሲመቸኝ ሲመቸኝ ዩቲዩብ ላይ ቪዲዩ እየለቀቅኩኝ ለምን ዘና ብዬ አልኖርም ምን አስጨነቀኝ ብዬ አቃለሁ። ...እኔ ተቋም መምራት አልችልም ይቅርብኝ እል ነበር።”

ይኼኔ ግን ሥልጠና መውሰድ እንዳለበት ወሰነ።

“በኋላ ግን ሥልጠናዎች ስወስድ ስሜትን መግራት ምን እንደሆነ፣ የኢሞሽናል ኢንተለጀንስ ምንነት (የስሜት ብልህነት)፣ ሠራተኛውን ቀድሞ ማሰልጠን፣ ስለጉዳዩ ማስረዳት፣ እንደገባው ማረጋገጥ እና በተጨማሪም አማራጭ ዕቅድ (ፕላን ቢ) ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን” ተረዳ።

ሰው ማስተዳደር በጣም ከባድ ነገር ነው። ቀላል ነገር አይደለም የሚለው እሸቱ፣ በቀዳሚነት ሥልጠና መውሰዱ፣ በመቀጠል ደግሞ የሰው ኃይል አስተዳደር መቅጠሩ ሸክሙን እንዳቀለለለት ይናገራል።

ከስልጠናዎች ባሻገር ደግሞ “...እነዚህን አሠልጣኞች ቃለ መጠይቅ ሳደርግላቸው ለራሴ ብዬ ነው የምሰማው። ለተመልካች ወይንም ለሆነ ሰው ይጠቅመዋል ብዬ አይደለም የምሰማው። የእውነት ለራሴ ብዬ አዳምጬ በሰማሁት ነገር ተለውጬ አውቃለሁ። ስለዚህ ሥልጠናዎችን በአካል ከመውሰድ ባለፈ ሚዲያም ላይ በጣም እከታተላለሁ።”