“መንግሥት ኢትዮጵያን ሊያፈርስ ነው መባሉ የዓመቱ ቀልድ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

የፎቶው ባለመብት, HOPR
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ኢትዮጵያን ሊያፈርስ እየሰራ ነው መባሉ እንደ ቀልድ እንደሚመለከቱት ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት መጋቢት 19/2015 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥትን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ነው።
በዛሬው 11ኛ የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ “መንግሥት አገርን ሊያፈርስ ነው በማለት በርካቶች ላይ ጥርጣሬ ተፈጥሯል” በማለት የጠየቁት የምክር ቤቱ አባል አቶ ጀምበር አያልነህ ናቸው።
“መንግሥት አገርን ሊያፈርስ እየሠራ ነው። መንግሥት ኢትዮጵያን አንድ ማድረግ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያን ሊያፈርስ ነው የሚሰራው የሚል ጥያቄ የተነሳው፤ በጥያቄ ደረጃ የተከበረ ጥያቄ ነው። ግን የዓመቱ ምርጥ ቀልድ አድርጌ ነው የምወስደው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
አቶ ጀምበር “ብልጽግና መራሹ መንግሥት ውስጥ ያሉ አካላት አገርን አንድ ከማድረግ ይልቅ፤ ለመበተን አቅደው እየሰሩ እንዳሉ እና ብልጽግና አገርን እና ሕዝብን ክዷል ሲሉ በተደጋጋሚ ይደመጣሉ” ብለዋል።
የኢትዮጵያ የመፍረስ ስጋት ቆሟል፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚችል ኃይል እንደሌለም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት።
ለዚህም ያነሱት ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ የነበሩ ውግዘቶችን በመጥቀስ የዓለም ኃይሎች ኢትዮጵያ ላይ በተነሱበት ወቅት በጽናት ተቋቁመናል ብለዋል።
ጦርነቱ ደብረ ብርሃን በደረሰበትም ወቅት መውጫ መንገድ እናበጅላችሁ እንደተባሉና “የለም አልለመድንም ብለን ዘምተናል” ብለዋል።
ፖሊስ፣ መከላከያ እና ሌሎች የፀጥታ ተቋማትን በቴክኖሎጂ በመታገዝ አፍሪካውያን የሚቀኑበት ግንባታ የተካሄደው መንግሥታቸው አገር ለማጽናት እንደሆነም ጠቅሰዋል።
በቅርቡ የነበረውንም የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤንም ጠቅሰው ኢትዮጵያ በኮሮና እና በጦርነት ውስጥ ሆና የሚታዩትን ግንባታዎች መገንባት ቻለች በርካቶች እንዳሏቸው ጠቅሰው፤ የምክር ቤቱ አባላት ይህንን እንዴት ሊገነዘቡ አልቻሉም? ሲሉም ጠይቀዋል።
“ኢትዮጵያ ልትፈርስ ነው? እየፈረሰች ነው ባሉ ሰዎች ጭንቅላት ውስጥ ኢትዮጵያ እኔ ካልመራኋት ፈርሳለች ለሚል ኃይል ኢትዮጵያ ፈርሳለች” ብለዋል።
አክለውም ኢትዮጵያ የምትገነጣጠልበት ወቅትም እንዲሁም የምትፈርስበት ወቅት አልፏል “አብረን ችግር ብንፈታ እና አማራጮች ብናይ። ኢትዮጵያ ለኢትዮያውያን ከበቂ በላይ ናት” ሲሉም ተደምጠዋል።
በዛሬው የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ በርካታ ጥያቄዎች ተነስተው የነበረ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታይቶ የነበረው መከፋፈል፣ ጦርነቱ ያስከተለው ዳፋ፣ በግጭቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን ዕጣ ፈንታ፣ ከአማራ ክልል የሚመጡ መንገደኞች ላይ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ የተጣለው ዕግድ፣ እየቀጠለ ያለው የዋጋ ግሽበትና ንረት፣ ማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት፣ የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት መጣስ ተነስቷል።
በተጨማሪም የሱዳን ታጣቂዎች ወደ ደቡብ ምዕራብ ክልል ዘልቆ ገብቷል መባሉ፣ የፀጥታ ኃይሎች ሰላማዊ ዜጎች የሚደርሰው ጥቃት እና ግድያ፣ እንዲሁም በቀጥታ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ያነጣጠረ “ የመፍትሄው አካል ለመሆን ሥልጣንዎትን አይለቁም ወይ?” የሚል ጥያቄንም አስተናግደው ምላሽ ሰጥተዋል።
የአገሪቱ ወቅታዊ ሰላምን በተመለከተ
ለሁለት ዓመት የዘለቀው ጦርነትን በዘላቂነት ለመቋጨት ከተደረሰው ስምምነት በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የዛሬ ስድስት ወር ከነበረው፣ ከስምንት ወራት በፊት ከነበረው በተሻለ ሁኔታ ላይ ናት ብለዋል።
ለመቶ ሺዎች ሕይወት መጥፋት የሆነው ጦርነት መቋጨት እንድ እርምጃ ነው ብለዋል። ሆኖም ሰላም አንጻራዊ ነው፣ ወደ ተሟላ የሰላም ሁኔታ ለመሄድ በርካታ ተግባራት እንደሚጠይቅ ጠቁመው እንደ ሕዝብ እና አገር ተሰናስለን ልንሰራ ይገባል።
“ተኩስ ሲቆም ወዲያውኑ የሰላም አየር ይነፍሳል ማለት አይደለም” በማለት በድኅረ ጦርነቱ የሚታዩ ዳፋዎች ቀላል አይደለም ብለዋል።
ቁስሉ ወዲያውኑ የሚሽር እንዳልሆነም አስታውሰዋል።
በተጨማሪም የጦርነት ነጋሪን አብዝተው የሚጎስሙ በርካቶች ያሉበት ስለሆነ የሰላም አየር እንዳለ መረዳት ከባድ እንደሆነም ነው የጠቀሱት።
“እነዚህ ኃይሎች ጦርነት የሚዋጊም ሆነ በቅርብ የሚዋጉም አይደለም። እነዚህ ኃይሎች ግጭት ይፈበርካሉ፣ ቀድመው ያቅዳሉ፣ ግጭት ይፈጽማሉ፣ አዛብተው በስፋት ይዘግባሉ፣ ገለው ሞትን ይላሉ፡፡ በዚህ ምክንያት የሰላም አየር በተሟላ መንገድ ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስፈን የራሱ የሆነ ፈተና ሲሆን ቆይቷል” ብለዋል።
በአገሪቱ ውስጥ ለአስርት ዓመታት የዘለቀው የመተላለፍ፣ የሴራ እና የጉልበት ፖለቲካ መስፈን በአገሪቷም ዘላቂ ሰላም እንዳይመጣ እንቅፋት ሆኗል ብለዋል።
“ገዳዩ ሰይፍ አያስፈልገንም፤ አሁንም የሚያስፈልገን እርቅ እና ሰላም ነው” በማለትም አስተዳደራቸው ለሰላም ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ መሆኑንም ።
“የረጋ ሰላም ሥራ ያስፈልገዋል። አዎንታዊ ሰላም በኃይል ብቻ የሚመጣ አይደለም” በማለት ለሰላም የሚከፈል ዋጋ እልህ አስጨራሹን ሂደትና ከእኛ ይቅር በሚል የሚመጣ ሂደት ነው ብለዋል።
ምንጊዜም ሰላም ሲባል የአንድ ሰው ሕይወት ማትረፍም ነው። “እየተጓዝን ያለነው የተሟላ ሰላም ለማምጣት ነው” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, hopr
ሚዲያዎችን በተመለከተ
የሚዲያዎች መብዛት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ የሚታይ ሁኔታ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አድማጩ ሊመርጥ ይገባል ብለዋል።
ሰላም በማይፈልጉ ኃይሎች ድጋፍ የሚሰጣቸው ሚዲያዎች መኖራቸው መዘንጋት የለበትም ያለት ጠ/ሚኒስትሩ፣ አንዳንዶቹ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ግጭት ይፈጥራሉ፣ ይገላሉ፣ ይሾማሉ፣ ይሽራሉ፣ ግጭት ያባዛሉ፣ ያልሞተ ሰው ይዘግባሉ ሲሉም ወቅሰዋቸዋል።
“ግጭት መፍጠር ብቻ ሳሆን ግጭት ያባዛሉ፡፡ አንድ ሰው ከሞተ 50 ይላሉ፤ 50 ለሞተ ሺህ ይላሉ። ግጭት ያበራክታሉ፣ ግጭት ደግሞ ካጡ ታሪክ ይመዛ። አሁን የሚታይ ግጭት ከሌለ ወደ ኋላ ይመለሳሉ።
“እነዚህ ሚዲያዎች ከአንገት ላይ ሀብል ለመውሰድ፤ አንገት የሚቆርጡ ሚዲያዎች ናቸው። ሀብሉን መቁረጥ ወይም መፍታት ሳይሆን፤ አንገት ቆርጦ ሀብል መውሰድ የሚሹ ሚዲያዎች ናቸው” ብለዋቸዋል።
ከሚዲያ ነጻነት ጋር ኃላፊነትን መሸከም አስፈላጊ እንደሆነም ጠቅሰው እነዚህ ሚዲያዎች በስፋት ራሳቸውን መፈተሽ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
“ዝም ብሎ ነጻ የሚባል ነገር የለም። የእኛ ሚዲያዎች ከዚህ አንጻር በስፋት ራሳቸውን መፈተሽ ይኖርባቸዋል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሆኖም ከዚሁ ጋር በተያያዘ የብሮድካስት ባለሥልጣኑም የተጠናከረ የሕግ ማስከበር ሥራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
ወደ አዲስ አበባ መግባት አለመቻል
ዜጎች ከተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች ወደ አዲስ አበባ ለመግባት አልቻሉም፤ የመዘዋወር ነጻነታቸው ታግዷል የሚል ጥያቄ በዛሬው ዕለት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተነስቷል።
ማንም ሰው ሕጋዊ በሆነ መንገድ ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት አለው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆኖም በዚህ ዓመት ያለው ፍልሰት አምስት፣ ስድስት ዓመታት ከነበረው ይበልጣል ብለዋል።
“ተዘጋ ሲባል እንቅስቃሴ የቆመ እንዳይመስላችሁ። በቅርቡ ጥናት አጥንተን ነበር። አዲስ አበባ አካባቢ አብዛኛው ላስቲክ አንጥፈው ሕገወጥ በሆነ መንገድ የሚኖሩ ሰዎች 96 በመቶው የአዲስ አበባ ነዋሪ አይደሉም።”
አዲስ አበባ ለመግባት የታገዱ መንገደኞችን በተመለከተም “አዲስ አበባን የብጥብጥ ማዕከል ማድረግ አለብን። አዲስ አበባ ውስጥ ሁከት ካላስነሳን በቀር በቀላሉ መንግሥትን መነቅነቅ እና ሥልጣን መያዝ አንችልምʼ የሚሉ በአገር ውስጥ እና በውጭ ያሉ ኃይሎች በተቀናጀ መንገድ በርካታ ሙከራዎች ሲያካሄዱ ቆይተዋል። ያን ለመከላከል ሰፊ ሥራ ሰርተናል። ውጤትም አምጥተናል” ብለዋል።
ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስጋት እና በአፈጻጸም ውስጥ የንጹሃን መጉላላት መፈጠር እና የሚበላሹ ጉዳዮች አሉ ሲሉ ጠቅሰዋል።
“ነገር ግን ምንም መረጃ ሳይኖረን የሠራናቸው ሥራዎች አይደሉም። በስፋት መረጃዎችን እናገኛለን። ከዚያም ተነስተን ግጭት ለማስቀረት በሚደረጉ ሥራዎች ስጋት እንገታለን። መጉላላት የማይገባቸው ንጹህ ዜጎች ደግሞ የሚጉላሉባቸው አጋጣሚዎች እና ሁኔታዎች አሉ። እነሱ መታረም አለባቸው” ብለዋል።
የሕዝብ በዓላትን አነጣጥረው የሚገቡ ኃይሎች አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምሳሌም የጠቀሱት “በአንድ ቀን፤ በአንድ ቀበሌ፤ በአንድ ሰው ፊርማ አንድ ሙሉ ባስ በወረቀት ልኮ ይዘን እናውቃለን” ሲሉም አስረድተዋል።
ቀድሞም መረጃ ስለተገኘ መሳሪያ፣ ፈንጂ እና ገንዘብ ይዘው ሲንቀሳቀሱ እንደተያዙ እንዲሁም የሰዎችን ሕይወት መታደግ መቻሉንም አመልክተዋል።
አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ደግሞ አንድ አካባቢ ይሰበሰባሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ሊቀናጁ ይገባል ብለዋል።
“ለጥፋት ከከተማ ወደ ከተማ ሳይሆን ከአንድ ክፍልም ወደ ሌላ ክፍልም የሚደረግ እንቅስቃሴ ይታገዳል” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ፍተሻ፣ ጥፋተኞችን መቆጣጠር ይጠናከራል ሲሉ ገልጸዋል።
“አዲስ አበባ ውስጥ ብጥብጥ ሲነሳ፤ ከወለጋም ይምጣ ከጎጃም፤ ብጥብጥ በሚያስነሳው ሰውዬ የአንድ ምስኪን እናት ልጅ ወይ ይቆስላል፤ ወይ ይሞታል።”

የፎቶው ባለመብት, hopr
የሚታገቱ ሰዎችን በተመለከተ
በየአገሪቱ ሕገወጥ ታጣቂዎች ተንሰራፍተው እንዳሉ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግድያ፣ ዘረፋ እና እገታ አለ ብለዋል።
አልፎ አልፎ ራሳቸውን የሚያግቱ ሰዎች እንዳሉ ሆኖ በአብዛኛው ግን እነዚህ የታጠቁ ኃይሎች እገታ እንደሚያደርጉም ጠቅሰዋል።
የመከላከያ ኃይል በአንድ ቦታ ላይ ተሰብስቦ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግን ኮንትሮባንድን፣ ሕገ ወጥ ትጥቅን፣ በየቦታው ሰው መግደል መዝረፍን መከላከል በሚያስችል አሰፋፈር የአገር መከላከያ እና ፌደራል ፖሊስ የሚሰማሩበት መንገድ ላይ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ይህም በሚቀጥሉት ወራት በበለጠ እንደሚጠናከር ተስፋ እንዳላቸው ጠቅሰው በአንድ አካባቢ የነበረው ኃይል በየስፍራው ሲሰማራ በኢትዮጵያ እየታዩ ያሉ እንቅስቃሴዎች ለማስተካከል ዕድል ይሰጣል ብለዋል።
ሱዳን እና ደቡብ ሱዳንን በተመለከተ
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ተከትሎ የአልፋሽቃ ግዛትን የተቆጣጠረችው ሱዳን ጋር መለስ ቀለስ ያሉ ግጭቶችን በተመለከተ የቅኝ ግዛትን ተከትሎ ድንበር የማካለል ሥራ ባለመሠራቱ ለረጅም ጊዜ ሲንከባለል የቆየ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በሁለቱም በኩል ያሉ ሕዝቦች እንዳይስተጓጎሉ በሁለቱም መንግሥታት የተቋቋመው የጋራ ኮሚቴ ሥራ እየሰራ ቢሆንም፣ ግጭቶች መፈጠራቸው አልቀረም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ሆኖም መንግሥታቸው ከሱዳን ጋር በመሆን የድንበር ማካለሉን ሥራ ለማከናወን ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ነው የጠቀሱት።
የደቡብ ሱዳን ኃይል በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ውስጥ ዘልቀው ገብተው የማዕድን ስፍራ መቆጣጠራቸው እና በርካቶችንም ማፈናቀላቸው መዘገቡን በተመለከተ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።
ደቡብ ሱዳን የሰው አገር የመውረር አቅሙም ሆነ ፍላጎቱ እንደሌላት ጠቅሰው፣ ያሉት ሁኔታዎች በአርብቶ አደሮች መካከል የሚፈጠሩ ችግሮች ናቸው ብለዋል። ይህንንም ለመፍታት ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር እየተነጋገሩም እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ከታጣቂ ኃይሎች ጋር ሰላም ስለማውረድ
ከመንግሥት ላይሎች ጋር ላለፉት ዓመታት ግጭት ውስጥ ከቆየው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር ሰላም ስለማውረድ እየተደረጉ ስላሉ ጥረቶች ከምክር ቤት አባላት ጥያቄ ተነስቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥታቸው ለበርካቶች መፈናቀል እና ሞት ምክንያት የሆነው ጦርነት በሰላም እንዲቋጭ ከፍተኛ ፍላጎት አለው ብለዋል።
በብልጽግና ምክትል ፕሬዝዳንት የሚመራ የሰላም ኮሚቴ መቋቋሙን እና ሥራዎችም እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት አስር ያህል ጥረቶች መደረጋቸውን ጠቁመው ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ወይም መንግሥት ሸኔ ከሚለው ኃይል ጋር ተያይዞ አንድ የተዋቀረ ኃይል ባለመኖሩ ከተለያዩ ኃይሎች የተለያዩ ሃሳቦች በመቅረባቸው ሂደቱ መጓተቱን ገልጸዋል።
ከቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ከጋምቤላ፣ ከቅማንት እና ከአገው ሸንጎ ታጣቂዎችም ጋር መንግሥት ግጭቶችን በሰላም ለመቋጨት ጥሩ እየሰራ ነው ብለዋል።
ለሁሉም የታጠቁ ኃይሎችም የሰላም መንገድ እንምረጥ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
የክልልነት ጥያቄ
የአዳዲስ ክልልነት ጥያቄን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የፖለቲካ ሰዎች ክልል እንሁን የሚል ጥያቄ ሲነሳ፣ የሕዝቡ መንገድ የመንገድ ፍላጎት መልስ እንደዲያገኝ፣ ልማት እንደሚመጣ ብለው ሰዉ ይቀሰቅሳሉ፡፡ ከቀሰቀሱ በኋላ ክልል ይፈጠራል፡፡ ክልል ሲፈጠር ወዲያው ዞን፣ ወረዳ እየተባለ ይስፋፋል” በማለት ሁኔታው የተለየ መሆኑን አመልክተዋል።
ተያይዞ ስለሚነሳው ችግርም ሲናገሩ “ባጠናነው ጥናት፤ ቢያንስ ስድስት ሚሊዮን ሕዝብ በአንድ ክልል ውስጥ ከሌለ፤ ያ ክልል ገቢውን አሳድጎ አሁን ባለው ሁኔታ ደመወዝ ለመክፈል ይቸገራል፡፡ ለዚህ ነው ክልል ከተሆነ በኋላ ደስታው እና ጩኸቱ ሳምንት አይቆይም፡፡ ወዲያው የደመወዝ ጥያቄ ይከተላል” ብለዋል።
ደርግ ወድቆ ኢህአዴግ ሥልጣን ሲቆጣጠር የመንግሥት ሠራተኛ 230 ሺህ ገደማ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን 2.6 ሚሊዮን መድረሱን አመልክተዋል።
“ሰው መዋቅር እየፈጠረ በዚያው ውስጥ ካልተሾመ በስተቀር፤ የሕዝቡ መብት አልተከበረም፣ የአካባቢ መብት አልተከበረም፡፡ መብት እንዲከበር እርሱ መሾም አለበት፡፡ ይህንን በሁለት ሦስት ዓመት ጭምር በተደጋጋሚ ስናገር የነበረው ጉዳይ ነው” ብለዋል።
“ሥልጣን ይልቀቁ”
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የምክር ቤት አባል ከሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ በአገሪቱ ላለው ችግር የመፍትሄ አካል ለመሆን ሥልጣን እንዲለቁ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።
እሳቸውም በምላሹ የተነሳው ጥያቄ “ሥልጣን ብንለቅ” በሚል ቢቀርብ የሚል አስተያየት የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስተሩ “ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚም ሆነ ተርጓሚም መንግሥት ነው። በጋራ ብንለቅ የሚል ቢሆን በበለጠ ትርጉም ይሰጣል። ኃላፊነትንም ከወሰድን በጋራ ቢሆን ጥሩ ነው” ብለዋል።
አክለውም የሥልጣን ባለቤት ሕዝብ እንደሆነና ሰጪውም ነሺውም ሕዝብ መሆኑን አስታውሰው ሰጪው ጋር የተሻለ ሃሳብ ይዞ መቅረብ ተገቢ ነው ብለዋል።
“ሥልጣን በኮሮጆ እና በመናጆ አይሆንም። ምርጫው ከሦስት ዓመታት በኋላ ነው የሚካሄደው ሕዝብ በምርጫ ከጣለን ሥልጣን በደስታ እናስረክባለን” ብለዋል።
“አየር ጨብጦ ልቀቁ አይቻልም፤ የተሻለ ሃሳብ ሲመጣ ነው መንግሥትን ሥልጣን ማስለቀቅ የሚቻለው” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል።












