ጠቅላይ ሚኒስትሩ በድርድሩ መንግሥታቸው ያቀረበው ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት አግኝቷል አሉ

የፎቶው ባለመብት, Abiy Ahmed Ali/twitter
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥታቸው ከህወሓት ጋር በነበረው የሰላም ድርድር ያቀረበው ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት እንዳገኘ ተናገሩ።
ደቡብ አፍሪካ በነበረው ድርድር “ኢትዮጵያ ያቀረበችው ሃሳብ መቶ በመቶ ተቀባይነትን አግኝቷል” ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ በአርባ ምንጭ ከተማ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ላይ ነው።
ትናንት፣ ረቡዕ ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ፣ በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መሪዎች መካከል ሲካሄድ የነበረው ድርድር ተጠናቅቆ ሰላም ለማውረድ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ለአስር ቀናት ያህል ሲካሄድ በቆየው ድርድር ማብቂያ ላይ የተፈረመው ባለ 12 ነጥብ ስምምነት በዋናነት ዘላቂነት ግጭት ማቆም፣ የህወሓት ታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታት እና የሰብዓዊ እርዳታ ያለገደብ ማድረስ ይገኙበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአርባ ምንጭ ከተማ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ “ጀግንነት ማለት ማሸነፍ ብቻ አይደለም። ጀግንነት ማለት ከድል በኋላ ይቅር ማለት ነው” ያሉ ሲሆን መንግሥታቸው ያገኘውን የሰላም ዕድል እንደሚቀበል ተናግረዋል።
“በሙሉ ልብ ይቅርብ ብለን የኢትዮጵያን አንድነት እና ሰላም መመለስ እንፈልጋለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ትግራይን እና የትግራይ ሕዝብን “በሙሉ ልብ መልሶ ለመገንባት ወደ ቀደም የአገሩ ስሜት እንዲመለስ አብረን እንድንቆም በታላቅ ትህትና እጠይቃለሁ” ሲሉ ለዜጎች መልዕክት አስተላልፈዋል።
“ጀግንነታችን የሚረጋገጠው ካለን አካፍለን በትግራይ የተጎዱ ወገኖቻችንን ማጉረስ ስንችል ነው“ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስር ዐቢይ፤ ለትግራይ ሕዝብም መልዕክት አስተላልፈዋል።
“ለመላው የትግራይ ሕዝብ ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት አላስፈላጊ ጦርነት፣ አላስፈላጊ ጉዳት፣ አላስፈላጊ ኢትዮጵያን አሳልፎ መስጠት በዚህ ይብቃ” ብለዋል።
በፕሪቶሪያው ስምምነት በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲሁም በአንድ አገር ውስጥ ከአንድ በላይ ሠራዊት ሊኖር አይችልም በሚለው ጉዳይ ከስምምነት መደረሱን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ በትግራይ “ሕጋዊ ምርጫ” ለማካሄደ ከስምምነት ተደርሷል ብለዋል።
የይገባኛል ጥያቄ በሚነሱባቸው እና አከራካሪ ቦታዎች በሰላም የአገሪቱን ሕግ መሠረት በማድረግ ብቻ ምላሽ እንዲያገኙ በሁለቱ ወገኖች ከስምምነት ተደርሷል ብሏል።
ሁለት ዓመት የደረፈነው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ተዛትመቶ እንደነበረ ይታወሳል።
በጦርነቱ ከባድ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት የደረሰ ሲሆን፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል።












