“ወሳኝ ቀዳሚ እርምጃ” የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማብቃት “ወሳኝ ቀዳሚ እርምጃ” ነው ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አወደሱ።
አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በቃል አቀባያቸው በኩል ባወጡት መግለጫ በአፍሪካ ኅብረት በኩል የተደረሰው ስምምነት የበርካቶችን ሕይወትና ኑሮን ያወደመውን ጦርነት ለማስቆም ተስፋ ሰጪ ጅምር ነው ብለዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ “ኢትዮጵያውያን እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት የወሰዱትን ቆራጥ እርምጃ” እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።
አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሁለቱም ወገኖች ተኩስ አቁመው አገሪቱን ወደ ሰላምና መረጋጋት ለመመለስ “በቀሩ ጉዳዮች ላይ ዘላቂ ፖለቲካዊ ስምምነት ላይ ለመድረስ በእርቅ መንፈስ ድርድራቸውን እንዲቀጥሉ” ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ድርድሩን በማስተባበርና በመምራት የተሳተፉትን ሁሉንም ወገኖች ያመሰገኑት ጉቴሬዝ፣ ሁሉም ወገኖች ተኩስ አቁሙ የፈጠረውን እድል በመጠቀም “የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲቀላጠፍ እና በጽኑ የሚፈለጉት መሠረታዊ አገልግሎቶች ሥራ እንዲጀመሩ” ጠይቀዋል።
“የተባበሩት መንግሥታት በአፍሪካ ኅብረት የሚመራውን ቀጣይ ሂደት ለመደገፍና እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው በማቅረብ በኩል ሥራውን ይቀጥላል” ብሏል የወጣው መግለጫ።














