ሐማስ በኦሊምፒክ ላይ ጥቃት እንደሚያደርስ የሚሠራጨው ወሬ ምን ያህል እውነት ነው?

የፎቶው ባለመብት, Telegram channel 'Golos Mordora'
የሐማስ ታጣቂዎች ነን የሚሉ ግሰለቦች በፓሪስ በሚካሄደው የኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ ጥቃት ለማድረስ ሲዝቱ የሚያሳይ ቪድዮ ማኅበራዊ ሚድያ ላይ ተሠራጭቷል።
ነገር ግን ቢቢሲ ያደረገው የመረጃ ማጣራት ቪድዮው በሩሲያውያን የተሠራጨ ሊሆን እንደሚችል ያሳያል።
ፈረንሳይ የምታዘጋጀው የኦሊምፒክ ጨዋታ አርብ ሐምሌ 20/2016 ዓ.ም. በዋና ከተማዋ ፓሪስ በይፋ ተጀምሯል። ይህ ከመሆኑ ከጥቂት ቀናት በፊት ነው ቪድዮው በማኅበራዊ ሚድያዎች ላይ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች የታየው።
ፊቱ የተሸፈነው እና የሐማስ ታጣቂ ነኝ የሚለው ግለሰብ ፈረንሳይ ለእስራኤል ባሳየችው ድጋፍ ምክንያት “በፓሪስ ጎዳናዎች የደም ወንዝ ይፈሳል” ሲል በአረብኛ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል።
በቪድዮው መጨረሻ ላይ ሰውዬው በደም የተነከረ የፈረንሳይ ሪፐብሊክ መለያ የሆነችውን ማሪያን ጭንቅላት ይዞ ይታያል።
እርግጥ ነው ጭንቅላቱ “ፌክ” ይመስላል። ቪድዮውም እንደዚያው።
የቋንቋ እና የዘይቤ አለመመሳሰል
ቪድዮው ምንም እንኳ ከሐማስ የተለቀቀ መሆኑን ባይጠቁምም በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ላይ በስፋት ያጋሩት ሰዎች ከቡድኑ ጋር ያገናኙታል። የሐማስ ፖለቲካዊ አመራሮች ደግሞ ቪድዮው ትክክለኛ አይደለም ይላሉ።
ቢቢሲ ይህንን ቪድዮ ከመረመረ በኋላ በቋንቋ እና አቀራረብ ላይ በርካታ ክፍተቶች የተመለከተ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ሐማስ ከሚለቃቸው ቪድዮዎች ጋር ያለው ተመሳሳይነትም አጠራጣሪ መሆኑን ታዝቧል።
ሐማስ በጋዛ ያለውን ጦርነት በተለመከተ ቴሌግራም ላይ ባሉት የተለያዩ ገፆች መግለጫዎች እና ቪዲዮዎችን ይለቃል።
በዚህ ቪድዮ ላይ የሚናገረው ግለሰብ የአነጋገር ዘይቤው ፍልስጤማዊ አይመስልም። መሠረታዊ የሚባሉ ቃላትን ሲያወጣ የአረብኛ ቋንቋ ተናጋሪ እንዳልሆነ ያስታውቃል። ሐማስ ደግሞ በዚህ አይታማም።
ሰውዬው ያደረገው ሙሉ ጥቁር የሆነ ልብስ የሐማስ ታጣቂ ክንፍ አል-ቃሳም ብርጌድ ቃል አቀባይ ለወትሮው ከሚያደርገው ወታደራዊ መለዮ የተለየ ነው።
አልፎም የፍልስጤም ባንዲራ የተለጠፈበት ጃኬት ከሌላው ጊዜ ለየት ያለ ነው። የሐማስ ታጣቂዎች ቃል አቀባይ የፍልስጤምን ባንዲራ የሚያርገው እጅጌው ላይ ከፍ ብሎ ሲሆን ቪድዮው ያለው ግለሰብ ግን ደረቱ ላይ አድርጎት ታይቷል።
ሌላ “የሐማስ” ቪድዮ
የፓሪስ ኦሊምፒክን ለመበጥበጥ የሚዝተው ይህ ቪድዮ ከዚህ ቀደም በሐሰት ከሐማስ ጋር ተያይዞ ከወጣ አንድ ቪድዮ ጋር ተመሳሳይነት አለው።
ባለፈው ጥቅምት ማኅበራዊ ሚድያ ላይ ሲሠራጭ የነበረው የቀድሞው ተንቀሳቃሽ ምሥል እንዲሁ የሐማስ አባላት ናቸው የተባሉ ሰዎችን የያዘ ሲሆን፣ ምሥሉ ላይ የሚታዩት ግለሰቦች የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪን “ለተደረገልን የጦር መሣሪያ እርዳታ” ሲያመስግኑ ታይተዋል። ይህ ዩክሬን ላይ የቀረበ ሐሰተኛ ወቀሳ ነው።
ቪድዮው ትክክለኛ አይደለም የሚሉት የክሌምሰን ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ቡድን አባላት፤ እንደዚህ ዓይነት የተሳሳቱ መረጃዎች ማሠራጭ የክሬምሊን ዘመቻ አካል ነው ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Telegram channel "Russia MyVmeste!"
ቢቢሲ ባደረገው ምርመራ መሠረት “የሐማስ” ናቸው ተብለው የተለቀቁት ሁለቱ ቪድዮዎች ድምፅ፣ የደንብ ልብስ እና የቀረፃ ቦታ ተመሳሳይ እንደሆኑ ያስታውቃል።
ሁለቱም ቪድዮዎች ተመሳሳይ ግራጫ ቀለም ያለው ግድግዳ እና ጥራታቸው ዝቅ ያሉ ናቸው። በተነፃፃሪው ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተለቀቁ የሐማስ ይፋዊ መግለጫዎች ጥራታቸው ከፍ ያለ እና ጀርባቸው ጥቁር አሊያም “አርማ/ብራንድ” ያለባቸው ናቸው።
ቪድዮውን ማን አሠራጨው?
አንዳንድ የማኅበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች “የሐማስ” የተባለው ቪድዮ የተሠራው በእስራኤል ነው ቢሉም ማስረጃ አላቀረቡም።
ነገር ግን ቪድዮውን ለማሠራጨት ጥቅም ላይ የዋለውን ዘዴ የተመለከቱ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ጣታቸውን ክሬምሊን ላይ ይጠቁማሉ።
ፀረ-ፈረንሳይ የሆነው ቪድዮ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለጠፈው በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 21 ሲሆን @endzionism24 የተባለ “የሐማስ ተዋጊ” የሚል መለያ ያለው ገፅ ነው የለጠፈው።
ይህ ገፅ ከዚህ ቀደም በሰው ሠራሽ አስተውሎት [ኤአይ] የተሠሩ ምሥሎችን የሚያጋራ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ይህ ገፅ ተዘግቷል።
ከዚያ በኋላ ደግሞ ይህ ቪድዮ በአብዛኛው የተለጠፈው የክሬምሊን ወዳጆች በሆኑ የምዕራብ የአረብኛ እና የፈረንሳይኛ ቋንቋ የዜና ጣቢያዎች ነው። ቪድዮው ቴሌግራም ላይ መለጠፉን የክሌምሰን ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ዳረን ሊንቪል ይናገራሉ።
ቪድዮውን በቴሌግራም ገፃቸው ካጋሩት ገፆች መካከል መቀመጫውን ሲድኒ ያደረገው የሩሲያ ፕሮፖጋንዳ አቀንቃኝ የሆነው “ኦሲ ኮሳክ” የተባለ 80 ሺህ ተከታዮች ያሉት ገፅ አንዱ ነው። ሌላኛው ደግሞ 170 ሺህ ተከታዮች ያሉት ለክሬምሊን የሚያደላ “ጎሎስ ሞርዶራ” የተባለ የቴሌግራም ቻነል ነው።
በጥቂት ሰዓታት ውስጥ በሩሲያ ቋንቋ የየተረጎሙ ፅሑፎች እንዲሁም ፎቶዎች በተለያዩ በርካታ ሺህ ተከታዮች ባሏቸው ገፆች ተሰራጨቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፈረንሳይ ባለሥልጣናት ላለፉት ወራት፤ ሩሲያ የፓሪስ ኦሊምፒክን ለመጉዳት የተሳሳተ መረጃ የማሠራጨት ዘመቻ ጀምራለች በማለት ሲያስጠነቀቁ ነበር።
ባለፈው ሚያዝያ የፈረንዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን፤ ሞስኮ ፈረንሳይ ኦሊምፒክ ለማዘጋጀት ብቁ አይደለችም የሚል ትርክት ስታሠራጭ ነበር ማለታቸው አይዘነጋም። ክሬምሊን ይህን ወቀሳ “ተቀባይነት የሌለው” ነው ትላለች።
ዩክሬን ውስጥ ባለው ጦርነት ምክንያት ሩሲያ እና ቤላሩስ በፓሪስ ኦሊምፒክ ከመሳተፍ የታገዱ ሲሆን፣ ከእነዚህ አገራት የመጡ ጥቂት አትሌቶች ብቻ ማንንም በማይወክል ባንዲራ መሳተፍ ይችላሉ።
“ፍራቻ መንዛት”

የፎቶው ባለመብት, Telegram channel "Olympics Has Fallen 2"
የማይክሮሶፍት ትሬት አናሊሲስ ሴንተር ቪድዮውን ካጣራ በኋላ “ስቶርም-1516” የተባለው የሩሲያ ቡድን ያሠራጨው ነው ብሏል።
የማይክሮሶፍት አጥኚዎች እንደሚሉት ይህ ቡድን ከቀድሞው የቫግነር ቡድን መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን ጋር ግንኙነት ያለው ነው።
በፈረንሳይ የጂኦፖለቲክስ ተቋም የሩሲያ ጥናቶች ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ኬቪን ሊሞኒዬር እንደሚሉት የኦሊምፒክ ጨዋታዎችን መረበሽ ማለት ለዩክሬን ዲፕሎማሲያዊ እና ወታደራዊ ድጋፍ የምታደርገው ፈረንሳይ ላይ ጫና መፍጠር ነው።
ሩሲያውያን የፓሪስ ኦሊምፒክን በተለመከተ የተሳሳተ መረጃ ሲያሠራጩ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።
ከዚህ ቀደም “ኦሊምፒክ ወደቋል” የሚል ርዕስ ያለው የአክተሩ ቶም ክሩዝን ሐሰተኛ ድምፅ ተጠቅሞ የተለቀቀው ቪድዮ የመጀመሪያው ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ የኢላን መስክን ምስል ተጣቅሞ የተሠራጨ ነው።












