ፈረንሳይ ከኦሊምፒክ መክፈቻ በፊት የባቡር መስመሮቿ በእሳት መቃጠላቸው አሻጥር ነው አለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በፈረንሳይ ዛሬ፣ ሐምሌ 19/ 2016 ዓ.ም. ማለዳ በፈጣን ባቡር መስመሮች ላይ የእሳት ቃጠሎ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ባለሥልጣናት ተናገሩ።
በዛሬው ዕለት ከሰዓታት በኋላ በይፋ ከሚከፈተው የፓሪስ ኦሊምፒክ ውድድር ቀደም ብሎ ይህ መፈጸሙ “በፈረንሳይ ላይ የተቃጣ ጥቃት” እና ወደ መክፈቻው የሚደረጉ ጉዞዎችን ለማስተጓጎል የተፈጸመ አሻጥር ነው ሲሉ አውግዘውታል።
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር “አሻጥር” ሲሉ በጠሩት በዚህ የባቡር መስመር ቃጠሎም 250 ሺህ መንገደኞች ሊስተጓጎሉ እንደሚችሉ የፈረንሳይ የባቡር ኩባንያ ኤስኤንሲኤፍ ገልጿል።
የፓሪስ ኦሊምፒክ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ሊካሄድ ሰዓታት በቀረበትም ወቅት ነው ማለዳ ላይ ተከታታይ የእሳት ቃጠሎዎች ተፈጽመው በእንቅስቃሴ ላይ መስተጓጎል የገጠመው።
ከመዲናዋ ፓሪስ በተለያዩ አቅጣጫ የሚገኙ ከፍተኛ ፍጥነት ያላቸው ቲጂቪ የተሰኙት በርካታ ፈጣን የባቡር መስመሮች የተጠቁ ሲሆን፣ የጉዞ ኩባንያዎችም ደንበኞች መጉላላት እና የጉዞ መሰረዝም እንደሚገጥማቸው አስጠንቅቀዋል።
ለእነዚህ ቃጠሎዎች ኃላፊነቱን የወሰደ አካል እስካሁን ባይኖርም ጠቅላይ ሚኒስትር አታል የፀጥታ ኃይሎች ጥቃቱን የፈጸሙትን አካላት እየፈለጉ እንደሆነ ተናግረዋል። የአገሪቱ የሕዝብ ዐቃቤ ሕግም ምርመራ ከፍቷል ተብሏል።
“ዛሬ ማለዳ ላይ በፈረንሳይ የባቡር መስመሮች ላይ በታቀደ እና በተቀናጀ መልኩ የአሻጥር ድርጊቶች ተፈጽመዋል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
የባቡር ኩባንያው ኤስኤንሲኤፍ የእሳት ቃጠሎውን ከበድ ያለ ጥቃት እንደሆነ ጠቅሶ ሆን ብሎ ለማውደም ተፈጽሟል ብሏል። በዚህ ጥቃት የተበላሹትን መስመሮች “አንድ በአንድ” እየተለዩ በእጅ እያስተካከሉም እንደሆነ ነው ኩባንያው የገለጸው።
በዚህ ቃጠሎ በሳምንቱ መጨረሻ እስከ 800 ሺህ የሚደርሱ ነዋሪዎች ጉዟቸው ሊስተጓጎል እንደሚችል ኩባንያው አክሏል።
የአገሪቱ ትራንስፖርት ሚኒስትር ፓትሪስ ቨርግሪቴ ስለጥቃቱ የተገኙ ሁሉም መረጃዎች “እነዚህ ሆን ብለው የተፈጸሙ የእሳት ቃጠሎዎች መሆናቸውን ያመለክታሉ” ብለዋል።
“የወንጀል ድርጊቱ” በአንድ ጊዜ የተፈጸመ ሲሆን፣ በተለይም በደቡብ ምሥራቅ አካባቢ ሰዎች ሸሽተው ትተዋቸው የሄዱ መኪኖች እና ተቀጣጣይ ቁሶች መገኘታቸውን አክለዋል።
ፓሪስን በሰሜን ከሊሊ፣ በምዕራብ ቦርዶ፣ በምሥራቅ ከስትራስፖርግ የሚያገናኙት ሦስቱ ዋነኛ የቲጂቪ የባቡር መስመሮች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።
ፓሪስን ከማርሴይ የሚያገናኛት አራተኛው መስመር ላይ ሊፈጸም የነበረ የጥቃት ሙከራን እንዳከሸፉ ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።
የአገሪቱ የስፖርት ሚኒስትር ኤሚሊያ ኦውዴያ ካስቴራ ጥቃቶቹን “በጣም አሰቃቂ” ሲሉ ገልጸውታል።
ጥቃቱ በሕዝቡ እና በኦሊምፒክ አትሌቶች ላይ ያደረሰው ተጽእኖ እንዲሁም በሳምንቱ መጨረሻ ቡድኖችን ወደ ውድድር ቦታዎች በማጓጓዝ ላይ ሊኖረው የሚችለው መስተጓገጓል እየተገመገመ መሆኑን አክለዋል።
በዛሬው ዕለት በይፋ በሚከፈተው የፓሪስ ኦሊምፒክ ከ300 ሺህ በላይ ሰዎች ደማቁን ሥነ ሥርዓት እንደሚታደሙ ይጠበቃል።












