የፊሊፒንስ ማረሚያ ቤቶች ሃላፊ ጋዜጠኛ በማስገደል ተጠረጠሩ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የፊሊፒንስ ፖሊስ የአገሪቱን የማረሚያ ቤቶች ሃላፊ አንድ ታዋቂ ጋዜጠኛ በማስገደል ወንጀል መጠርጠሩን ገለጸ።
የ63 ዓመቱ ጋዜጠኛ ፐርሲቫል ማባሳ ባለፈው ወር ነበር በዋና ከተማዋ ማኒላ ወደሚገኘው የራዲዮ ስቱዲዮው እየተጓዘ ባለበት በተተኮሰበት ጥይት የተገደለው።
ከመገደሉ በፊትም የአገሪቱ ማረሚያ ቤቶች ዋና ዳይሬክተርን የሚመለከት የሙስና ክሶችን የያዘ ፕሮግራም በራዲዮ ጣቢያው አስተላልፎ እንደነበርም የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ማባሳ የቀድሞው የፊሊፒንስ ፕሬዚዳንት ዱቴርቴን በተመለከተ ከፍተኛ ትችቶችን ሲያቀርብ የቆየ ጋዜጠኛም እንደነበር ተነግሯል።
የማረሚያ ቤቱ ሃላፊ በአሁን ሰአት ከስራ ገበታቸው ላይ የታገዱ ሲሆን በዚህ ወንጀል የሚከሰሱ ከሆነ በከባድ ወንጀል የተከሰሱ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣን ይሆናሉ ሲሉ የአገሪቱ የፍትህ ጉዳዮች ሃላፊ መናገራቸውን ኤኤፍፒ ተናግሯል።
ፖሊስ የግድያ ወንጀል ክሱን በአንድ የምክትል የጸጥታ ሃላፊ ላይም መስርቷል። እንዲሁም ተጠርጣሪው ነፍሰ ገዳይ ግድያው ከተፈጸመ ከቀናት በኋላ ለጸጥታ ሃይሎች እጁን ሰጥቷል። ለዚህም የዳረገው የደህንነት ካሜራዎች ፊቱን ይዘው ማስቀረታቸውን ተከትሎ ነው።
በተጨማሪም የማረሚያ ቤቱ ሃላፊ እንዲሁም ምክትል የጸጥታ ሃላፊው በአንድ ታራሚ ግድያ ጉዳይ ላይ ትዕዛዝ ሰጥተዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል። ታራሚው የጋዜጠኛውን ህይወት አጥፍቷል ተብሎ ለተጠረጠው ግለሰብ የግድያ ትዕዛዛቸውን እንዳስተላለፈም ይገመታል።
የፊሊፒንስ ብሔራዊ የምርመራ ቢሮ የማረሚያ ቤት ሃላፊው ጋዜጠኛው በተከታታይ የሙስና ተግባራቸውን የሚያጋልጥ ፕሮግራም በመስራቱ ምክንያት እንዲገደል ትዕዛዝ ሰጥተዋል ብለው እንደሚያምን ይፋ አድርጓል።
በቀድሞው ፕሬዚዳንት ዱቱርቴ የተሾሙት የማረሚያ ቤት ሃላፊው ባለፈው ወር ለአንድ መገናኛ ብዙሃን ግድያውን እንዳልፈጸሙ አስተባብለዋል።
ጋዜጠኛው ማባሳ አዲሱ ፕሬዚዳንት ስልጣን ከያዙ ወዲህ የተገደለ ሁለተኛው ጋዜጠኛ ሆኗል።
‘’ግድያው በዋና ከተማዋ ማኒላ መፈጸሙ ገዳዮቹ ምንም አይነት ፍርሃት እንደሌላቸው ያሳያል። እንዲሁም ባለስልጣናት ጋዜጠኞችንም ሆነ መደበኛ ዜጎችን ለመጠበቅ አለመቻላቸውንም ያሳያል’’ ሲል ብሔራዊ የጋዜጠኞቹ ማህበር ገልጿል።
ባለፉት 30 ዓመታት በፊሊፒንስ 187 ጋዜጠኞች መገደላቸውን የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ መረጃ ያሳያል።












