ናይጄሪያዊያኖቹ ቲክቶከሮች በባለስልጣን በመሳለቃቸው በጅራፍ እንዲገረፉ ተፈረደባቸው

 የቲክቶክ አርማ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በቲክ ቶክ ማህበራዊ ድረገፅ ዝና ያተረፉ ሁለት ናይጄሪያውያን የመንግሥት ባለስልጣን ላይ ተሳልቀዋል በሚል በጅራፍ እንዲገረፉ ፍርድ ቤቱ ወሰነ።

በተጨማሪም የገንዘብ ቅጣትና ፍርድ ቤቱንም እንዲያጸዱ ብያኔ ተላልፏል።

ሙባረክ ኢሳ መሀመድ እና መሃመድ ቡላ የተባሉት ግለሰቦች ቲክቶክን በመጠቀም የሰሜን የካኖ ግዛት አስተዳዳሪ አብዱላሂ ጋንዲን ስም በማጠልሸት ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።

የግለሰቦቹ ጠበቃ ለውሳኔው ይግባኝ እንደማይሉ አስታውቀዋል።

ናይጄሪያ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾችን በመጠቀም ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ትችቶችን በቀልድ ባዋዛ መልኩ የሚያቀርቡ ግለሰቦች ቁጥር እየተበራከተ መጥቷል።

ሙባረክ ኢሳ መሀመድ እና መሀመድ ባላ አስተደዳሪው በመሬት ወረራ፣ በሙስና እና በስራቸው ላይ ይተኛሉ በሚል በቲክቶክ እና ፌስቡክ ላይ በለጠፉት ቪዲዮ ተሳልቀዋል።

አቃቤ ህግ ዋዳ አህመድ ዋዳ ግለሰቦቹ የአስተዳሪውን ስም አጥፍተዋል እንዲሁም ድርጊታቸው የህዝብን ሰላም ሊያደፈርስ የሚችል ነው ብለዋል።

ግለሰቦቹ ጥፋተኝነታቸውን አምነው ምህረት እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል ነገር ግን ዳኛው እያንዳንዳቸው በ20 ግርፋት እንዲቀጡ፣ 20 ፓውንድ እንዲከፍሉና የፍርድ ቤቱን ግቢም ለ30 ቀናት እንዲያጸዱ አዘዋል።

በተጨማሪም አስተዳዳሪውን በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቁም ታዘዋል።

ጠበቃቸው ባሽር ዩሱፍ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የተወሰነው ብያኔ እንደማይቃወሙትና ደንበኞቻቸው እንደማይታሰሩ ተናግረዋል።

በናይጄሪያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቲክቶክ በወጣቶች ዘንድ መካከል ፈጣን እድገትን ያሳየ የማህበራዊ ድረ ገፅ ነው።

እነዚህ የቲክቶክ ተጠቃሚዎች አብዛኛውን ጊዜ ታዋቂ ሰዎችን ወይም የመንግሥት ባለስልጣናትን ጨምሮ ምስሎቻቸውንና ቪዲዮዎችን በመቁረጥ ሲሳለቁ ይሰማሉ።

በሰሜን ናይጄሪያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የእስልምና እምነት ተከታይ በአብላጫ ያለበት የካኖ ግዛት ከሃገሩ ህግ ጎን ለጎን የሸሪአ ህግን ከሚፈጸምባቸው ወደ አስር ከሚጠጉ ግዛቶች አንዱ ነው።

በነዚህ የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች የሚዳኙት የእስልምና እምነት ተከታዮች ብቻ ናቸው።