በዓለም የመጀመሪያ የሆነው ሰው ሰራሽ ደም በሰዎች ላይ መሞከር ተጀመረ

በቤተ ሙከራ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, NHSBT

በቤተ ሙከራ ውስጥ የዳበረ ሰው ሰራሽ ደም ለመጀመሪያ ጊዜ በሚደረግ ክሊኒካዊ ሙከራ ለሰዎች መሰጠቱን የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ተመራማሪዎች አስታወቁ።

አሁን ለሙከራ ለሰዎች የተሰጠው ሰው ሰራሽ ደም መጠኑ ትንሽ ሲሆን፣ የተወሰነ የሻይ ማንኪያ መጠን እንደሆነ ተገልጿል። በዚህም ደሙ በሰው አካል ውስጥ ገብቶ ምን ውጤት እንደሚኖረው ለማወቅ ሙከራ ይደረጋል።

አስካሁን በዓለም ዙሪያ ደም ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ከሌሎች በልገሳ የተገኘ ደምን በመስጠት ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል። ይህ በቤተ ሙከራ የተሰራው ደም ስኬታማ ከሆነ፣ በተለይ ለማግኘት አስቸጋሪ የሆኑ የተለዩ የደም አይነቶችን በማምረት ላይ ትኩረት ይደረጋል።

በተለይ የደም ካንሰር እና ሲክል ሴል አኒሚያ ላለባቸው እንዲሁም መደበኛ የደም ለውጥ ለሚያስፈልጋቸው ህሙማን ይህ አዲሱ ሰው ሰራሽ ደም ስኬታማ ከሆነ ችግራቸውን ያቀላል ተብሏል።

በደም ልገሳ ወቅት ተቀባዩ ግለሰብ በትክክል ተመሳሳይ የደም አይነት የማያገኝ ከሆነ ሰውነቱ ሊቆጣና ህክምናው ሊሰናከል ይችላል።

ይህም የደም አይነት ተመሳሳይነት በስፋት ከሚታወቁት የደም አይነት ከሆኑት ኤ፣ ቢ፣ ኤቢ እና ኦ ባሻገር ዝርዝር ልዩነቶችን መለየትን የሚጠይቅ ነው።

በሰውነት ውስጥ ኦክሰጂንና ካርቦን ዳይኦክሳይድን የሚያመላልሰው በቤተ ሙከራ ውስጥ የዳበረው ቀይ የደም ህዋስ

የፎቶው ባለመብት, NHSBT

የምስሉ መግለጫ, በሰውነት ውስጥ ኦክሰጂንና ካርቦን ዳይኦክሳይድን የሚያመላልሰው በቤተ ሙከራ ውስጥ የዳበረው ቀይ የደም ህዋስ

አንዳንድ የደም አይነቶች ከተጠቀሱት በተለየ “በጣም፣ በጣም የተለዩ ከመሆናቸው ባሻገር፤ በአንድ አገር ውስጥ የዚያ አይነት ደም ያላቸው ሰዎች 10 ሰዎች ብቻ ሊሆኑ ይችላሉ” ይላሉ የብሪስቶል ዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰር አሽሊ ቶዬ።

ሰው ሰራሹን ደም ለማዳበር የብሪስቶል፣ የኬምብሪጅ፣ የለንደን እና የዩኬ ብሔራዊ የጤና አግልግሎት የምርምር አባላት እየተሳተፉ ነው። የፕሮጀክቱ ትኩረት ከሳንባ ወደ ቀሪው የሰውነት ክፍል ኦክስጂን በሚወስደው ቀይ የደም ህዋስ ላይ ነው።

ሰው ሰራሽ ደሙን ለመሞከር ቢያንስ 10 ጤናማ በጎ ፈቃደኞች የሚያስፍልጉ ሲሆን፣ አሁን የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሰዎች በሙከራው ላይ እየተሳተፉ ነው።

በዚህም ሙከራው የሚደረግባቸው ሰዎች በአራት ወራት ልዩነት ውስጥ ከ5 አስከ 10 ሚሊ ሊትር የሚሆን ደም በመጀመሪያ ትክክለኛ ደም፣ ቀጥሎ ደግሞ በቤተ ሙከራ የዳበረ ደም ይሰጣቸዋል ተብሏል።

ይህ በቤተሙከራ የዳበረው ደም ስኬታማ ከሆነ በወጪ ረገድ አሳሳቢ እንደሚሆን ባለሙያዎቹ የተናገሩ ሲሆን፣ ከለጋሾች ተፈጥሯዊ ደምን ለማግኘት የሚወጣው ወጪ፣ ሰው ሰራሽ ደሙን ለማምረት ከሚያስፈልገው ያነሰ ነው።

በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ብሔራዊው የጤና አገልግሎት እንደሚለው ተፈጥሯዊው የደም ልገሳ በአማካይ 130 ፓወንድ ያክል ያስወጣል። ምርምሩን የሚያካሂደው ቡድን ባይገልጸውም በቤተ ሙከራ ውስጥ ሰው ሰራሽ ደም ማዳበር ከፍተኛ ወጪን ይጠይቃል ተብሏል።

በተጨማሪም በቤተሙከራ ውስጥ የስቴም ህዋሳትን ለማዳበር በሚከናወነው ሂደት ውስጥ ሌሎች ተግዳሮቶች ስለሚኖሩ በምርቱ ወቅት የተለያዩ ችግሮች መግጠማቸው እንደማይቀር ተገልጿል።

ነገር ግን ይህ በቤተ ሙከራ የሚዳብረው ደም መደበኛ የደም ዝውውር ለሚፈልጉ እና እጅግ ለየት ያለ የደም አይነት ላላቸው ሰዎች የሚሆን ደም በማምረት በኩል ትልቅ መፍትሔ እንደሚሆን ባለሙያዎች ይናገራሉ።