ዐይናችንን ሊጎዱ እና ዕይታችንን ሊያጨልሙ የሚችሉ አራት ምክንያቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የህመም አለመኖር ጤንነትን አያረጋግጥም ይባላል።
ፍጹም ጤነኛ እንደሆኑ እያሰቡ ድንገት በአንዱ የሰውነት ክፍልዎ ላይ ስር የሰደደ በሽታ እንዳለ ማወቅ ሌላ ህመም ነው።
ከ23 ዓመታት በፊት ሥራ የጀመሩት የዐይን ህክምና ስፔሻሊሰቱ ዶክተር ዮናስ ጥላሁን እንዲህ አይነት አጋጣሚዎችን ተመልክተዋል።
“አንዳንድ ታካሚዎች ‘ድንገት ጠዋት ተነስቼ አንዱ ዐይኔን ሳሸው ጠፋ’ ይላሉ” በማለት አልፎ አልፎ ስለሚያጋጥማቸው ነገር ይናገራሉ።
ዐይን በድንገት ሊጠፋ ይችላል?
መልሱን እንመለሰበታለን! ከዚያ በፊት ዐይናችንን ስለሚጎዱ እና የዕይታ መጠናችንን ስለሚቀንሱ ምክንያቶች እናውራ!
ዐይንን የሚጎዱ በርካታ ምክንያቶች አሉ። እኛ ግን ዶክተር ዮናስ ጥላሁን የነገሩን አራት ምክንያቶች ብቻ እንመልከት።
ጤና
ዶክተር ዮናስ ዐይን በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ ባሉ የጤና ችግሮች ምክንያት ሊጎዳ የሚችልበት አጋጣሚዎች እንዳሉ ያስረዳሉ።
እንደ ስኳር እና ደም ግፊት ያሉ በሽታዎች በቀጥታ የዐይን ጤንነት ላይ ጉዳት በማድረስ እስከ ዐይነ ስውርነት ሊደርሱ ይችላሉ።
የአሜሪካ በሽታ መቆጣጠር እና መካለከል ማዕከል ወይም ሲዲሲ እንደሚለው የስኳር በሽታ ከዐይን ጋር የተሳሰሩ የደም ቧንቧዎች ላይ ጉዳት በማድረስ የዕይታ መጠናችን እጅግ እንዲያሽቆለቁል ወይም ሙሉ በሙሉ እንዲጠፋ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
ከዚህም ባሻገር በክትባት በቀላሉ ሊወገዱ በሚችሉ ችግሮች ምክንያት ዐይን በከፋ ሁኔታ ሊጎዳ እንደሚችልም ነው ዶክተር ዮናስ የሚናገሩት።
“እንደ ኩፍኝ ያሉ በሽታዎች ክትባት ካልተወሰደ ጠበሳ በማምጣት ዐይንን እስከማጥፋት ይደርሳሉ” የሚሉት የዐይን ስፔሻሊስቱ “በተመጣጠነ ምግብ፣ ቫይታሚን ኤ እጥረት የዐይን ብሌን መቁሰል አጋጥሟቸው ብዙ ህጻናት ዐይናቸውን ሊያጡ የሚችሉበት ሁኔታ አለ” ብለዋል።
በሌላ በኩል በህጸናት ዐይን ላይ “መንሸዋረር” የመሰሉ ችግሮችን ችላ ብሎ ማለፍ በዕይታቸው ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችልም ጠቁመዋል።
የዐይን ንጽህናንን ባለመጠበቅ ደግሞ እንደ ትራኮማ ያሉ በሽታዎች ተከስተው “ውለው አድረው” የዐይን ብርሃንን ሊያሳጡ የሚችሉ ሲሆን የዐይን በሽታ ከቤተሰብ ሊወረስበት የሚችልበት አጋጣሚም አለ።
በጤና ምክንያት የሚመጡ የዐይን ችግሮችን ምርመራ በማድረግ የከፋ ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት ሊደረስባቸው ይችላል።
ስኳርን የመሳሰሉ በሽታዎች ያሉባቸው ሰዎች እና በቤተሰብ ውስጥ የዐይን ችግር እንዳለ ከታወቀ የዐይን ምርመራን በቋሚነት ማድረግ ይመከራል።
ለህጻናት ደግሞ የተመጣጠነ ምግብ መስጠት እና ክትባቶችን እንዲወስዱ ማድረግ እንደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ሁሉ ለዐይናቸውም ጠቃሚ መሆኑን ነው ይላሉ ዶክተር ዮናስ።
ህጻናት ከተወለዱበት ጊዜ ጀምሮ ዐይናቸው ላይ “ነጭ ነገር ጣል ካለ”፣ ሳያለቅሱ እንባ ከፈሰሰ፣ የዐይን መጠን መለያየት ካለና ዐይናቸውን ደጋግመው ካሹ ወደ ህክምና ተቋማት እንዲሄዱ ዶክተር ዮናስ ይመክራሉ።
የቫይታሚን ኤ እና ኦሜጋ 3 ይዘት ያላቸው ምግቦችን ማዘውተር የዐይን ጤናን በእጅጉ ይጠብቃሉ። እንደ ፓፓያና ማንጎ ያሉ ፍራፍሬዎችን፣ እንደ ቆስጣና ጎመን ያሉ አትክልቶችን እንዲሁም አሳን ማዘውተር ለዐይን ጤና ጠቃሚ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሞባይል እና ኮምፒውተር ስክሪኖች
የዐይን ስፔሻሊስቱ “በስክሪን ላይ የሰዎች ዐይን ተተክሎ በመዋሉ የተነሳ፣ የዐይን ጤና መታወክ ደርሶ ሰዎች ወደ ሆስፒታል መመላለሳቸው መጨመሩ ይታያል” ይላሉ።
በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ ከሞባይል እና ከኮምፒውተር ጋር ያለን ቁርኝት እየጨመረ በመሄዱ የተነሳ፣ በዲጂታል ቁሶች ምክንያት የሚመጡ የዐይን ውጥረቶች (Digital Eye Strain/Computer Vision Syndrome) በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
እንደ ሐኪሙ ገለጻ በቀን በስክሪኖች ላይ ያለ ቆይታ ከ2 ሰዓታት ከዘለለ ረጀም የስክሪን ቆይታ ተብሎ የሚገለጽ ነው።
ማን ያውቃል?! ከሞባይሉ ጋር ቁርኝት ላለው ግለሰብ በቀን ለሁለት ሰዓት መጠቀም እጅግ ትንሽ ሊሆን ይችላል።
ቢቢሲ በአንድ ወቅት የተመለከተው ሪፖርት በ20 ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሰዎች ስክሪን ላይ የሚያጠፉት ጊዜ መጨመሩን ያመላክታል።
ሪፖርቱ ከ5 እስከ 16 ዓመት ያሉ ህጻናት በቀን በአማካኝ 6 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ስክሪን ላይ እንደሚያጠፉ ይጠቁማል።
ታዲያ ዐይንን ለረጅም ሰዓት ስክሪን ላይ ማንከራተት ጊዜያዊ ችግሮችን እንደሚያስከትል ነው ዶክተር ዮናስ የሚያስረዱት።
ይህም የዐይን ብዥታ፣ መወጠር፣ መቅላት፣ ማሳከክ፣ መደረቅ፣ ማቃጠል እንዲሁም ቶሎ መድከም፣ እንቅልፍ እንቅልፍ ማለትና ራስ ምታትን ያካትታል።
ሐኪሙ አንዳንድ ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ ረጅም የስክሪን ቆይታ ህጻናት ላይ የዕይታ ችግር (Short-sightedness) ሊፈጥር እንደሚችል ተናግረዋል።
መፍትሄው ምንድን ነው?
ስክሪን በምንጠቀምበት ጊዜ “የሃያ ሃያ ሕግ”ን መተግበርን ዶክተር ዮናስ ይመክራሉ።
“የሃያ ሃያ ሕግ” እንደ ኮምፒውተር፣ ሞባይል ወይም ቴሌቪዢን ያሉ ቁሶችን ለ20 ደቂቃ ከተጠቀምን በኋላ ለ20 ሰኮንድ ሥራ በማቆም 20 ጫማ ወይም 6 ሜትር ርቀት አካባቢ በመመልከት ዐይንን የማሳረፍ ሕግ ነው።
ይህም ቀላል የሚመስል ቢሆንም ለዐይን ጠቃሚ መሆኑን ነው የሚያስረዱት።
በሐኪም ያልታዘዙ መነጽሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መነጽርን ከተገኘበት ቦታ “ለስክሪን፣ ለፀሐይ አልያም ለዝነጣ” መሸመት ለዐይናችን ጤና ጠንቅ ሊሆን ይችላል።
ዶክተር ዮናስ “አንዳድ መነጽሮች ጠቃሚነታቸው የተረጋገጠ አይደለም። አንዳንዶች ደግሞ ጎጂም ሊሆኑ ይችላሉ” ያሉ ሲሆን፣ ለምሳሌ ሰማያዊ ብርሃኖችን ያጣራሉ በሚል እና ለኮምፒውተር በሚል በውድ ዋጋ የሚሸጡ መነጽሮችን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።
“እርግጥ ኮምፒውተር ለመጠቀም መነጽር አይጠቅምም እያልኩ አይደለም። በሐኪም ምርመራ ታይቶ የሚጠቅምባቸው አስፈላጊ እና የግድም የሚሆንባቸው ጊዜያት አሉ” ይላሉ።
ከዚያ ውጪ ግን አንዳንዶቹ የ‘ሳይት’ ቁጥራቸው ከተጠቃሚው ዐይን ጋር ባለመናበቡ ምክንያት ዐይን ላይ ጫና ይፈጥራሉ።
ለፀሐይ ወይም ለዝነጣ በሚል የሚሸመቱት ደግሞ “ዐይናችን እንደጨለመ ስለሚቆጥር የዐይን ብሌናችን ይሰፋል።”
የዐይን ብሌን መስፋት ደግሞ ዐይናችን ለጎጂ እና አላስፈላጊ ጨረር እንዲጋለጥ ያደርገዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዕድሜ
ዕድሜ ከሚያዳክማቸው የሰውነት ክፍሎች አንዱ ዐይን ነው። በተለይ እድሜ ከአርባ ሲሻገር ዐይን ይደክማል።
የዕይታ መጠን እየቀነሰ ይሄዳል።
ዶክተር ዮናስ የዚህን ምክንያት ሲያስረዱ ዐይን ጉልበቱን የሚያስተካክልበት፣ ቅርጽ የሚቀይርበት ጡንቻዎች እያረጁ ስለሚሄዱ ነው ይላሉ።
በወጣትነት ዘመን ብሌን ለርቀት፣ ለመካከለኛ እና ለቅርበት ዕይታ የሚሰጠው ቀላል ምላሽ ዕድሜ ሲገፋ ለመታዘዝ ይደክማል። በዚህ ጊዜ አጋዥ መነጽሮች ሊያስፈልጉ ይችላሉ።
በሌላ በኩል ዕድሜ ሲገፋ ሞራ (Cataract) የተሰኘው የዐይን ክፍል “ጉም በመያዝ” ብርሃን ለማስተላለፍ ይቸገራል።
ይህም “ጭጋግ የሆነ ዕይታ ሊያመጣ ይችላል። በተወሰነ ደረጃ በመነጽር ሊረዳ ይችላል። ግን እየገፋ ሲሄድ ደግሞ በቀዶ ህክምና ብቻ የሚስተካከል ሊሆን ይችላል” ይላሉ - የዐይን ህክምና ስፔሻሊስቱ።
በዕድሜ ምክንያት ዐይን ላይ የሚመጡ ችግሮች አንዳንዶቹ በህክምና መመለስ የሚችሉ ሲሆን፣ ሌሎቹ ደግሞ ህክምና ላይመልሳቸው ይችላል።
ዐይናችን ድንገት ሊጠፋ ይችላል?
ዶክተር ዮናስ “ሰዎች ዐይናቸው ሥራ እንዳቆመ ድንገት ሊያውቁ ይችላሉ እንጂ ዐይን ድንገት አይጠፋም” ይላሉ።
ቀደም ብሎ የነበረ እና በህክምና ያልታየ ችግር በሂደት ዐይንን እስከ ማሳወር ሊያደርስ ይችላል።
በተለይ “የዐይን ብርሃን ሌባ” ተብሎ የሚታወቀው ግላኮማ ምንም ምልክት ሳይሰጥ ለረጅም ጊዜ የዐይን ነርቭን ጎድቶ ሥራውን ሊያቆም ይችላል።
ለዚህ ነው ሰዎች ከ40 ዓመት ዕድሜ በኋላ በየዓመቱ የጤና ምርመራ ማድረግ እንዲያደርጉ የሚመከረው።












