ከ 1 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን 8 ሰዎችን ብቻ የሚያጠቃው አስገራሚ በሽታ

በኮቪድ በተያዙ አንዳንድ ሰዎች ላይ በሽታው ይከሰታል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በኮቪድ በተያዙ አንዳንድ ሰዎች ላይ በሽታው ይከሰታል

አንዳንድ በሽታዎች ግራ ናቸው። ለታማሚም ለአስታማሚም፤ ለአካሚም ለታካሚም።

ሐኪሞች እንዲህ ግራ የሆኑትን ደዌዎች ኢዲዮፓቲክ (idiopathic) ሲሉ ይጠሯቸዋል።

ግራ የሚባሉት ግራ ስለሚያጋቡ ነው። መንስኤያቸው ስለማይታወቅ።

ይህ ዛሬ የምንነግራችሁ በሽታ ከዚህ ይመደባል።

60 ከመቶ በምን እንደሚመጣ አይታወቅም። ሲመጣ ግን እግር ተወርች ያስራል። አስሮ ቤት ያስቀምጣል።

የአማርኛ ስም የለውም። በእንግሊዝኛ ‘ትራንስቨረስ ማያሊቲስ’ ይባላል።

በቅጽል ስሙ (TM) ይሉታል። በደምሳሳው የሕብለ ሰረሰር (የነርቭ) በሽታ ነው።

‘ከእንቅልፌ ስነሳ መራመድ አቃተኝ’

ቀደም ሲል እንዳልነው 60 ከመቶው በምን እንደሚመጣ አይታወቅም። በቃ አያድርስ ነው የሚባለው።

40 ከመቶ ግን ምንጩ ይታወቃል።

ይህን ዘርዘር አድርገው የሚያስረዱን ዶ/ር ዳዊት ክብሩ ናቸው።

ዶ/ር ዳዊት የነርቭ ሕክምና ከፍተኛ ስፔሻሊስት ናቸው።

አሁን በሰሜን አሜሪካ፣ በዊስኮንስን እና በሚቺጋን ግዛቶች በተለያዩ ሆስፒታሎች ይሠራሉ።

“በሽታው የሕብለ ሰረሰር አንዱን ክፍል በድንገት ያጠቃል” ይላሉ ዶ/ር ዳዊት።

ቀጥሎ ከተጠቃው ሕብለ ሰረሰር በታች ያለውን የነርቭ ሥርዓት ይስተጓጎላል።

ይስተጓጎላል ሲባል ምን ማለት ነው?

ለምሳሌ እጅና እግርን ማዘዝ ይቸግራል። ሽንት መቆጣጠርም ሊያስቸግር ይችላል።

“ከእንቅልፌ ስነሳ ድንገት መራመድ አቃተኝ፤ እግሬ ሰነፈብኝ” የሚሉ ታማሚዎች ያጋጥማሉ።

ማንኛውም ነገር ሲነካን ቆዳችን ንክኪን የሚረዳበትን መንገድም ይቀየራል።

ይህ የሚሆነው ከአእምሮ የሚላክ መልዕክት እየተቀየረ ለነርቭ ጫፍ ስለሚደርስ ነው።

ለምሳሌ አንሶላ ጣል ቢደረግብን አሸዋ የተደፋብን ያህል ሊሰማን ይችላል።

የሸሚዝ ቁልፍ ሲነካን በመርፌ የተወጋን ያህል ሊሰማን ይችላል።

“በሽታው ያልተለመደ የሚባል ነው’’ ይላሉ ዶ/ር ዳዊት።

ያልተለመደ ያስባለው ደግሞ ምልክቶቹ አይደሉም። ጥቂት ሰዎችን ብቻ ስለሚያጠቃ ነው።

በዓለም ከአንድ ሚሊዮን ሰው ቢበዛ 8 ሰዎችን ቢይዝ ነው።

ይህን አሃዝ ወደ እኛ አገር እንመንዝረው።

ለስሌት እንዲመቸን የኢትዮጵያን ሕዝብን 100 ሚሊዮን ነው እንበል።

በዓመት በዚህ በሽታ የሚያዙት 800 ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ እንደማለት ነው።

የአንጎል ኒዩሮን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ምን ስናደርግ ነው የምንታመመው?

ምንም ስላደረግን አይደለም የሚመጣው። ምንም ሳላላደረግንም አይደለም።

በቃ አንዳንድ ጊዜ መከላከያችን በስህተት ራሱን ያጠቃል። ይህ ከባዕድ ተህዋሲዎች ጋር የሚያያዝ ሊሆን ይችላል።

በሽታው በምን በምን ይመጣል? ስንል ዶ/ር ዳዊትን ጠየቅን።

“ብዙውን ጊዜ ያለምንም ምክንያት በድንገት ይመጣል።”

“ሌላ ጊዜ ደግሞ የአንጀት መቁሰል (ጋስትሮ ስትራይተስ) ሲያመን ሊመጣ ይችላል” ይላሉ ዶ/ር ዳዊት።

“አንዳንድ ሰዎች በአንጀት መቁሰል ከታመሙ ከ2 ሳምንት ወይም ከ3 ሳምንት በኋላ በዚህ በሽታ ይያዛሉ።”

እንደ ጉንፋን ዓይነት ወይም ኮቪድ ወይም ኤችአይቪም ይህን ድንገቴ በሽታ ሊስከትሉ ይችላል።

አንዳንድ ሰዎች አንዳች ቫይረስ ከያዛቸው ከ2 እና ከ3 ሳምንት በኋላ ይህ በሽታ ይከሰትባቸዋል።

ክሮኒክ በሽታዎች የሚባሉ በቋሚነት ሰውን የሚያጠቁ በሽታዎች አሉ።

ለምሳሌ የመገጣጠሚያ ሕመም ያለባቸው ሰዎች ይህ በሽታ አንዳንዴ ይከሰትባቸዋል።

በአመዛኙ ግን ይህ በሽታ ግራ የሚያጋባና ምክንያቱ የማይታወቅ፣ መነሻው በውል የማይለይ እና ያልተለመደ ደዌ ነው።

በሽታው እንደያዘን በምን ማወቅ እንችላለን?

ዶ/ር ዳዊት እንደሚሉት ይህ በሽታ የሚያሳያቸው ምልክቶች ውስን ናቸው።

አንዱና ዋንኛው የእግር መስነፍ ነው። የጡንቻ መልፈስፈስ ነው።

ታማሚዎች አንድ እርምጃ መራመድ ተራራ የመውጣት ያህል ሊሰማቸው ይችላል።

ይህ የሚሆነው ደግሞ በብዛት በአጭር ቀናት ውስጥ ነው። ፋታም አይሰጥም።

የእግር መስነፍ ብቻ ሳይሆን ከአንገት በታች ወይም ከወገብ በታች ያለ የሰውነት ክፍል በጠቅላላ አለመታዘዝ ይኖራል።

ሽንት እምቢኝ፣ አልወጣ ሊል ይችላል።

ቀስ ብሎ ደግሞ የሽንት እና ሰገራ ሙሉ ቁጥጥር ማጣት ይመጣል።

ምልክቶቹ በትንሹ እንኳ ሲታዩ ቶሎ ሐኪም ማየት እንጂ ሌላ መላ የለም።

“ቶሎ ከታከመ ነው ማገገም የሚቻለው። ከዘገዩ አደጋ ነው” ይላሉ ዶ/ር ዳዊት።

ራጅ

የፎቶው ባለመብት, PRAPASS PULSUB

መዳን ይቻላል?

በዚህ በሽታ ድንገተኛ (acute) እና መለስተኛ ድንገተኛ (sub-acute) የሚባሉ ደረጃዎች አሉ።

ድንገተኛ የምንለው በቀናት ውስጥ የሚመጣ ነው።

መለስተኛ ድንገተኛ የሚባለው ደግሞ በ2 ሳምንት አካባቢ የሚባባስ ነው።

ድንገተኛው በቀናት ውስጥ አጣድፎ ለሞት ሊያደርስ ይችላል። በተለይ ቶሎ ሐኪም ዘንድ ካልተሄደ አደገኛ ነው።

ከፊል ድንገቴ ከሆነ ግን ፋታ ይሰጣል።

ይህ የሚታወቀው በኤምአይአር እና በተጨማሪ ደም ምርመራዎች ነው።

ዶ/ር ዳዊት በሽታውን በቀላሉ ለማስረዳት የኤሌክትሪክ መስመርን እንደ ምሳሌ ይጠቀማሉ።

ነርቮች የእኛ የኤሌክትሪክ መስመር ሽቦዎች ናቸው።

ሕብለ ሰረሰር ውስጥ ልክ እንደ ኤሌክትሪክ መስመር ሽቦዎች የሚያልፉበት አንድ የነርቭ መስመር አለ።

እሱ የነርቭ መስመር ብግነት ሲገጥመው ነው ይህ በሽታ የሚጀምረው።

የነርቭ መስመሩ ብግነት ደረጃ ደግሞ የበሽታውን ደረጃ ይወስናል። ብግነቱን ማቆም ነው የመጀመሪያው ጥረት።

ሁለት ዓይነት ሕክምናዎች ይሰጣሉ።

የመጀሪመያው ሕክምና ስቴሮይድ ይባላል።

በደም ሥር ይሰጣል። ለተወሰኑ ቀናት። ይህም ብግነቱን ይቀንሳል።

ሌላኛው ደግሞ ‘ኢሚኖሞግሎቢን’ የሚባለው ነው።

የተቀመሙ አንቲቦዲዎች በደም ሥር ይሰጣል።

ይህ በኢትዮጵያ ውስጥ አይገኝም። ውድም ነው።

ከዚህ በኋላ ኦኮፔሽናልናል ፊዚዮቴራፒ ነው የሚቀጥለው።

ጡንቻ መሰልጠን የሚችል ነገር ነው።

አገልግሎቱን አቁሞ ከቀረ በዚያው ይሰንፋል፤ ይረሳል ይላሉ ዶ/ር ዳዊት።

ስለዚህ ሰውነታችን በፊዚካል ቴራፒ መሰልጠን አለበት።

ነርቭ

የፎቶው ባለመብት, SPL

በሽታው በኮቪድ ክትባት ይመጣል የሚባለው እውነት ነው?

ይህ በሽታ በዘር አይተላለፍም።

አንዳንድ ጊዜ ግን ክትባት ያመጣዋል። በኮቪድ በተያዙ ሰዎች ላይም አልፎ አልፎ ሊከሰት ይችላል።

ሆኖም ግን ከስንት አንዴ ነው ይህ የሚሆነው።

የኮቪድ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ተህዋስ ይህን የሕብለ ሰረሰር ብግነትን ሊያመጡ ይችላሉ።

ሰውነታችን ባክቴሪያዎቹንና ቫይረሶቹን ለማጥፋት ከሰውነታችን የሚሠራቸው አንቲቦዲ የምንላቸው ንጥረ ነገሮች አሉ።

እነርሱ በስህተት የራሳችንን መከላከያ ሲያጠቁ ይህ በሽታ ይከሰታል።

በተመሳሳይ ኮቪድም ቫይረስ ነው። ይህን በሽታ ሊያመጣ ይችላል።

እስካለፈው ዓመት መጨረሻ ድረስ በ22 አገሮች እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች ሪፖርት ተደርገዋል።

ግን ብዙ አይደሉም።

በመቶ ሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ በኮቪድ ከተያዙ ሰዎች ውስጥ ይህ የተከሰተባቸው ሰዎች ከመቶ በታች ናቸው።

“ከ140 ሚሊዮን ሰው ነው 100 ሰዎች ሪፖርት የተደረገው። የኮቪድ ክትባትም ተመሳሳይ ነው። ክትባቶች ለዚህ የሕብለ ሰረሰር በሽታ ቢያጋልጡም ቁጥራቸው ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም” ይላሉ ዶ/ር ዳዊት።

ስለዚህ የኮቪድ ክትባት ይህን ሕመም ያመጣል ወይስ አያመጣም?

ዶ/ር ዳዊት ለዚህ የሚሰጡት ምላሽ ጥንቃቄ የተሞላበት ነው።

“የኮቪድ ክትባት ይህን በሽታ ያመጣል ብሎ መናገር ትክክል አይሆንም።”

ይህ ሲባል የሕብለ ሰረሰር በሽታው ከከትባት ጋር አይያያዝም ማለት ሳይሆን፣ በዚህ የመከሰት አጋጣሚው እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው።

“እንደ ሕብረተሰብ ሦስትና አራት አጋጣሚዎች (cases) ስላሉ ክትባት በሽታውን ያመጣል ብለን መናገር ፍጹም ስህተት ነው” ይላሉ።

በኢትዮጵያ ይህ በሽታ ይታወቃል?

ዶ/ር ዳዊት እንደሚያወሱት ከሆነ ይህ በሽታ በእኛ አገር በብዛት ከቲቢ ጋር እንደሚምታታ ይናገራሉ።

ብዙ ሰው ቲቢ በአገራችን ከሳምባ ጋር ብቻ አያይዞ ነው የሚያየው።

ነገር ግን ቲቢ ሳንባን ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን ያጠቃል። ከእነዚህም መካከል ሕብለ ሰረሰር ይገኝበታል።

ይህን በሽታ ከሌሎች ተመሳሳይ በሽታዎች የሚለየው ታዲያ በቀናት ውስጥ ነገሮች መባባሳቸው ነው።

በተለይ ዶ/ር ዳዊት አገር ቤት ለሚገኙ ጠቅላላ ሐኪሞች ማስገንዘብ የሚሹት አንድ ነገር አለ።

በሽተኞቻቸው ላይ ምልክቶችን ካዩ ሳይውሉ ሳያድሩ በፍጥነት ወደ ነርቭ ሐኪም እንዲልኳቸው።

ይህም በተለይ በገጠርና ጤና ጣቢያ አካባቢ መዘግየት ሊኖር ከቻለ በሽታው ወዲያው ስለሚባባስ ነው።

ምልክቱ ለምን ያህል ጊዜ ይሰነብታል?

ከአንድ ወር እስከ ሦስት ወር ባለ ጊዜ ታማሚዎች ለውጥ ማየት ይጀምራሉ።

ይሁንና ነገሮች በአንድ እና በሁለት ቀን ውስጥ ከተከሰቱ የማገገም ዕድሉም እየጠበበ ይመጣል።

ረዘም ያለ ቀን የታመመ ሰው የማገገም ዕድሉ ከፍ ይላል።

በዚህ ሕመም የ 1/3ኛ ሕግ የሚባል ነገር አለ ይላሉ ዶ/ር ዳዊት።

ከታማሚዎቹ ውስጥ አንድ እጁ ሙሉ በሙሉ ይድናሉ። ይህም እስከ ሦስት ወራት ሊወስድ ይችላል።

አንድ ሦስተኛዎቹ ደግሞ አዝጋሚ ለውጥ ያያሉ። ይህ ለውጥ ዓመታት ሊወስድም ይችላል።

ቀሪዎቹ አንድ ሦስተኞቹ ደግሞ ቋሚ ችግር ይኖርባቸዋል ማለት ነው።

እንደ ዶ/ር ዳዊት መረዳት ከሆነ ከዚህ በሽታ ለማገገም ጊዜ ይወስዳል። የማገገም ዕድሎችን የሚጨምሩ ሌሎች ነገሮች ግን አሉ።

ለምሳሌ በአፋጣኝ ሕክምና ማግኘት፤ ለምሳሌ አጋዥ ሕክምናዎች ኦኮፔሽናል እና ፊዚካል ቴራፒን ቶሎ መጀመር።

በተለይ በሽተኞቹ ወጣት ከሆኑ ደግሞ የማገገም ዕድላቸው በዚያው ደረጃ ይጨምራል።

ወደ ነርቭ መልዕክቶችን የሚያሰደርሱት ሞተር ኒውሮንስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ወደ ነርቭ መልዕክቶችን የሚያሰደርሱት ሞተር ኒውሮንስ

እግራችን አልታዘዝ የሚለን ለምንድን ነው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዶ/ር ዳዊት የነርቭን ተግባር በቀላል ቋንቋ ለማስረዳት የኤሌክትሪክ መስመርን ማሰብ ይበጃል እንዳሉ ከላይ ገልጠናል።

በቤት ውስጥ የኤሌክትሪክ ሽቦዎችን የሚሸፍን ኮንዲት አለ። በሰውነት ደግሞ ነርቮችን የሚሸፍን ነገር አለ፤ ማይሊን ይባላል።

ብዙ ጊዜ ብግነቱ ይህን ሽፋኑን ነው የሚያጠቃው። ብግነቱ ከፍተኛ ሲሆን ግን ወደ ነርቭም ይገባል።

በዚህ ጊዜ ነርቮች መልዕክት ለማስተላለፍ ይቸገራሉ።

መልዕክት የሚተላለፈው በኬሚካል መስተጋብር ነው።

ለምሳሌ ጭንቅላታችን “ተራመድ!” ብሎ ሲያዝ እኛ አናውቀውም እንጂ በነርቭ በኩል በሕብለ ሰረሰር አልፎ ወደ እግር ይሄዳል።

ሕብለ ሰርሰር ላይ ብግነት ሲኖር መልዕክቱ በትክክል አይተላለፍም። በዚህን ጊዜ የነርቭ ሥራ ተስተጓጎለ እንላለን።

በዚህ በሽታ ሦስት ዓይነት ምልክቶች አሉ ይላሉ ዶ/ር ዳዊት።

አንደኛ ‘ሞተር’ የምንለው የእንቅስቃሴ መስተጓጎል ነው።

በቅጽበት ሰውነት ድንዝዝ ይላል። ስንፍ ይላል።

እግር ታጥፎ አለመዘርጋት፣ ተዘርግቶ አለመታጠፍ ወይም ግትር የማለት ፀባይ ያሳያል።

ሁለተኛ ‘ሴንሰሪ’ የምንለው ነው።

ይህም የውሸት ምልክቶች እና ስሜቶች ማየት ስንጀምር ነው።

እግሬ ትልቅ የሆነ ይመስለኛል። እግሬ በረዶ ውስጥ የገባ ይመስለኛል፤ የምንለው ለዚህ ነው። በሕክምና ዲስቴዥያ እንለዋለን።

የተሳሳተ መልዕክት ሲተላለፈ እንደማለት ነው።

ሦስተኛው ደግሞ ‘ኦቶኖሚክ ዲስፈንክሽን’ የሚባለው ነው።

ይህም ማለት የእኛ ቁጥጥር ሳይኖረው አእምሯችን ካለማወቅ በራሱ የሚሠራቸው ነገሮች አሉ።

ለምሳሌ ሽንታችን እንደመጣ የምናውቀው መሽናት እንዳለብን አስበንበት አብሰልስለን ሳይሆን ሰውነታችን ስለሚነግረን ነው።

የ‘ሰብ ኮንሽየስ’ አእምሮ ክፍል “ሽንት ወጥሮሃል ሂድና ሽና” ይለናል።

ይህ በሽታ እሱን መልዕክት ያዛባውና ሽንት እንደመጣብን አይነግረንም።

ከዚያ ፊኛችን ተጠራቅሞ ተጠራቅሞ በራሱ ጊዜ ይወጣል። እኛ ሳናውቀው።

ይህን ክስተት ‘ኦቶኖሚክ ዲስፈንክሽን’ እንለዋለን ይላሉ ዶ/ር ዳዊት።

አንዳንድ ሰዎች ደግሞ በዚህ በሽታ ስንፈተ ወሲብ ይገጥማቸዋል።

ከዚህ ጠንቅ እንዴት እንጠንቀቅ?

ዶ/ር ዳዊት ይህን በሽታ በተለየ ሁኔታ መከላከል እንደማይቻል ይጠቁማሉ።

ይልቅ ደጋግመው የሚያሰምሩበት ምልክት በታየ ፍጥነት ቶሎ ሐኪም ማየትን ነው።

ለታመሙ ሰዎች የሚሰጡት ምክር ሁለት ነው።

አንዳንድ ታማሚዎች ካገገሙ በኋላ በተራዘመ ጊዜ የኩላሊት ኢንፌክሽን ሊገጥማቸው ይችላል።

ይህን መከታተል ይኖርባቸዋል።

ሌሎች ታማሚዎች ደግሞ መንቀሳቀስ ስለሚያቅታቸው አልጋ ላይ ይውላሉ።

ይህንን ተከትሎ መቀመጫና ጀርባ አካባቢ ቁስል ይከሰታል። ይህ ሌላ ኢንፌክሽን ሊመጣ ይችላል።

በዚህ ሁኔታ በሽተኛውን በየሁለት ሰዓቱ ማገላበጥ ያስፈልጋል ይላሉ።

ከዚህ ሁሉ በላይ የሚያሰምሩበት ግን አንድ ነገር ነው።

ሰዎች ምልክት ካዩ ሐኪም ለማየት መዘግየት እንደሌለባቸው።

በዚህ በሽታ መዘግየት ማለት ሞት ነው።