አሜሪካ ከሩሲያ ጋር አሁንም ምሥጢራዊ የግንኙነት መስመር እንዳላት አመነች

አሜሪካ አሁንም ድረስ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ ከሩሲያ ጋር ትገናኛለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አሜሪካ አሁንም ድረስ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ ከሩሲያ ጋር ትገናኛለች

የአሜሪካ የብሔራዊ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ከፍተኛ አማካሪ ጄክ ሰለቨን አገራቸው ከክሬምሊን ጋር ንግግርና ምክክር የምታደርግባት የግንኙነት መስመር እንዳልዘጋች ተናግረዋል።

ዋሺንግተንና ሞስኮ የመረጃ ልውውጣቸው በዩክሬን ጦርነት ሳቢያ እንዳልተስተጓጎለ ሚስተር ሰለቨን አረጋግጠዋል።

ሚስተር ሰለቨን በዚህ ጉዳይ ላይ ሲናገሩ ይህ የግንኙነት መስመሩ እንዲቀጥል ማድረግ 'ከአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት ጋር የሚስማማ' ነው ብለዋል።

የጄክ ሰለቨን ንግግር የመጣው ዋይት ሐውስ ከሩሲያ ጋር ኒውክሌርን በተመለከተ ውስጥ ውስጡን ይነጋገራል የሚል መረጃዎችን አለማስተባበሉን ተከትሎ ነው።

ይህን የውስጥ ለውስጥ ንግግር የሚመሩት ደግሞ ጄክ ሰለቨን ናቸው ተብሎ ሲዘገብ ነበር።

በተለይ የዎል ስትሪት ጆርናል ዘገባ ሚስተር ሰለቨን ከሩሲያ አቻቸው ጋር ሚስጥራዊ ንግግር ያደርጋሉ ሲል ዘግቦ ነበር።

በእርግጥም ጋዜጣው እንደዘገበው ጄክ ሰለቨን ከሩሲያው አቻቸው ኒኮላይ ፓትሮሼቭ ጋር እንዲሁም ከክሬምሊን ከፍተኛ የውጭ ጉዳዮች ረዳት ከሆኑነት ዩሪ ኡሻኮቭ ጋር ባለፉት ሰባት ወራት ንግግር ሲያደርጉ ቆይተዋል።

እንደ ዎልስትሪት ዘገባ ከሆነ እነዚህ የሁለቱ አገራት ከፍተኛ የደኅንነት ኃላፊዎች በዋናነት ውይይታቸው ያጠነጠነው የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ዙርያ የተደቀነውን አደጋና ፍጥጫ በማስቀረት ዙርያ ነው።

ይሁንና ጄክ ሰለቨን ከዚህ ጉዳይ ውጭ ጦርነቱን በማቆም ጉዳይ ላይ ከክሬምሊን አቻቸው ጋር እንዳልተናጋገሩ ጠቁመዋል።

ባለፈው ወር ሚስተር ሰለቨን በአንድ መድረክ ላይ ሲናገሩ ሩሲያ ኒውክሌር ለመጠቀም ከሞከረች አደገኛና የከፋ ጣጣ ይዞባት ይመጣል ብለው ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዚህን ጋዜጣ ዘገባ ተከትሎ የክሬምሊን ቃል አቀባይ 'የምዕራብ ሚዲያ ወትሮም እንቶፈንቶ መዘገብ ልማዱ ነው' ሲሉ ሪፖርቱን አጣጥለውት ነበር።

ይሁንና ጄክ ሰለቨን አሜሪካ ከሩሲያ ጋር የንግግር መስመሩን ክፍት አድርጋ መቆየትን እንደምትመርጥ ተናግረዋል።

የጆ ባይደን ሁነኛ አማካሪ ናቸው የሚባሉት ጄክ ሰለቨን አሁንም ድረስ ከሞስኮ ጋር መነጋገሩ ለአሜሪካም ሆነ በዩክሬን ጦርነት በአንድም በሌላም ሁኔታ ተጽእኖ ላይ ለወደቁ አገራት ሁሉ አስፈላጊ ነው ብለው ያምናሉ።

ባለፈው ሳምንት ዋሺንግተን ፖስት አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው ኪየቭ ከሩሲያ ጋር በመነጋገሩ ረገድ ግልጽ ልትሆን ይገባል ማለታቸውን አውስቶ ነበር።

በአመዛኙ አሜሪካና ሩሲያ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ ውስጥ ውስጡን ግንኙነት እንደሚያደርጉ አይጠበቅም ነበር።

የሚስተር ሰለቨን ጉዳይም ዜና የሆነው አሜሪካ ይህን የግንኙነት መስመር ጠብቃ መቆየቷን በማመናቸው ነው።

ጆ ባይደንና ፑቲን ከጦርነቱ ወዲህ በመደበኛ ሁኔታ ቁጭ ብለው ተነጋግረው አያውቁም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሩሲያ የኒውክሌር ጦር መሣሪያን ልትጠቀም ትችላለች የሚል ከፍተኛ ስጋት በዓለም ዙርያ ረብቦ ነበር።

ይህም በቅርቡ የጠቀለለቻቸውን አራት የዩክሬን ሰፋፊ ግዛቶች ለማስጠበቅ እና እየደረሰባት ያለውን ሽንፈት ለማካካስ ሊሆን እንደሚችል ሲዘገብ ነበር።

ይህ በእንዲህ ሳለ ዩክሬን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በመጠቀም በሩሲያው ቢሊዮነር ንብረትነት ተይዘው የነበሩ ኩባንያዎችን መውረሷን ገልጻለች።

እነዚህ የተወረሱት ኩባንያዎች የተሽከርካሪ ሞተር፣ የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመርና ሌሎች ተሽከርካሪዎችን የሚያመርቱ ነበሩ።

ንብረትነታቸው ደግሞ ለክሬምሊን ቅርብ ናቸው የሚባሉት ቢያቼዚልቫ ቦሁስላቭ ነበሩ።

ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ እነዚህ ኩባንያዎች የዩክሬን መከላከያን ያግዛሉ ብለዋል።

ዩክሬን አሁንም በደቡብና በምሥራቅ የአገሪቱ ክፍሎች የመልሶ ማጥቃት ዘመቻን እያደረገች ነው።