ሶማሊያ ታጣቂው ቡድን “አል ሻባብ” በሚለው ስያሜ እንዳይጠራ አገደች

የፎቶው ባለመብት, AFP
የሶማሊያ መንግሥት የሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስቴር በአገሪቱ የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ አስላማዊ ቡድን “አል ሻባብ” በሚለው ስሙ እንዳይጠራው ክልከላ ጣለ።
የታጣቂው ቡድን መጠሪያ “አል ሻባብ” የአረብኛ ስያሜ ሲሆን ትርጉሙም “ወጣቶቹ” የሚል ነው። መነሻውን የሶማሊያ አድርጎ በጎረቤት አገራት ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ቡድኑ በአሸባሪነት የተፈረጀ ነው።
የሶማሊያ መንግሥት ቡድኑን ለማዳከም ከፍተኛ ዘመቻ እያካሄደ ሲሆን፣ የቡድኑን ተቀባይነት ለመቀመስም የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው።
የአገሪቱ የሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስቴር ታጣቂው ቡድን አል ሻባብ አስካሁን ሲጠቀምበት የነበረውን ስያሜ ከማገዱ በተጨማሪ፣ ሕዝቡ ቡድኑን “ካህዋሪጅ” ብሎ እንዲጠራው ጠይቋል። ይህ ስያሜ ከእስልምና ያፈነገጠ ቡድን መጠሪያ ሲሆን፣ በበርካታ ሙስሊሞች ዘንድ ተቀባይነት የሚያሳጣ ነው።
በተጨማሪም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ ላይ ምንኛውም የሃይማኖት መሪዎች ከአልሻባብ ጋር ግንኙነት ካላቸው ታጣቂዎች ጋር ስምምነትም ሆነ ግንኙነት እንዳያደርጉ ክልከላ ጥሏል።
የሶማሊያ መንግሥት እንዳለው አዲስ በወጣው መመሪያ አል ሻባብ “ካህዋሪጅ” በሚል መጠሪያ የተሰየመው በቡድኑ ላይ በከፈተው ዘመቻ አማካይነት ነው።
ይህ በሶማሊያ መንግሥት አማካይነት ለታጣቂው የአል ሻባብ ቡድን አዲስ አይነት ስያሜ ሲሰጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ከሰባት ዓመት በፊት ቡድኑን ከሕዝቡ ለመነጠል አዲስ ስያሜ ተሰጥቶት ነበር።
በአውሮፓውያኑ 2015 የሶማሊያ መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን አል ሻባብን “ኡጉስ” በሚል ምህጻረ ቃል እንዲጠሩት ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር። መጠሪያው “የሶማሊያን ሕዝብ የሚጨፈጭፍ ቡድን” ከሚሉት ቃላት የተወሰደ አህጽሮተ ቃል ነው።
ይህንንም ተከትሎ ታጣቂው ቡድን ጋዜጠኞችን ጨምሮ ማንም ሰው የመንግሥትን ትዕዛዝ ተከትሎ ቡድኑን በተባለው ስያሜ የሚጠራ ከሆነ እርምጃ እንደሚውስድ አስጠንቅቆ ነበር።
የሶማሊያ መንግሥት በአል ሻባብ ላይ እየወሰዳቸው ካሉት እርምጃዎች መካከል በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ማንኛውም የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን የቡድኑን እንቅስቃሴ በሚመለከት ምንም አይንት ዘገባ እንዳይሰሩ እገዳ መጣሉ ይታወሳል።
አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ፣ በታጣቂው ቡድን ላይ ሲካሄድ የነበረውን ዘመቻ የመንግሥት ኃይሎች ከጎሳ ሚሊሻዎች ጋር በመተባበር አጠናክረው ቀጥለዋል።
ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገረው አልሻባብ ከሶማሊያ ባሻገር በምሥራቅ አፍሪካ አገራት ውስጥ በሚፈጽማቸው የሽብር ጥቃቶች ይታወቃል።












