በአሜሪካ ነገ የሚደረገው የ‘ሚድ-ተርም’ ምርጫ አጭር ማብራሪያ

የአሜሪካዊያን ምርጫ አያልቅም።
ዋንኞቹ ግን ሁለት ናቸው።
አንዱ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ነው። በየአራት ዓመቱ ይደረጋል። ሌላኛው ደግሞ ‘ሚድ ተርም’ ምርጫ ይባላል። በየሁለት ዓመቱ ይደረጋል።
እኛ 'የአጋማሽ ዘመን ምርጫ' እንበለው።
የአጋማሽ ዘመን ምርጫ የመዳረሻ ምርጫ ነው። የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ነጩ ቤተ መንግሥት በገባ በሁለተኛ ዓመቱ ነው የሚደረገው።
አዲስ ባይሆንም ለሁለተኛ ጊዜ የቀጠለ ፕሬዝዳንትም ነጩ ቤተ መንግሥት በቆየ በ2ኛ ዓመቱ ይካሄዳል።
ይህ ምርጫ 'ሚድ ተርም’ የተባለውም ለዚሁ ነው። የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የሥልጣን ዘመን 4 ዓመት ስለሆነና በመንፈቁ ወይም በአማካይ ዓመቱ ስለሚደረግ።
ይህ ምርጫ ነገ ማክሰኞ ኖቬምበር 8 ይደረጋል። ወይም ነገ ይጠናቀቃል ብንል ይቀላል።
ምክንያቱም ላለፉት ሳምንታት መራጮች በበርካታ ግዛቶች በፖስታ ድምጽ እየሰጡ ስለነበረ ነው።
ቅድመ ምርጫ ቀን ምርጫ (early voting) የሚፈቅዱ ግዛቶችም ይህን ሲያደርጉ ነበር።
ለመሆኑ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ምንድነው?
በአሜሪካ ሁለት ምክር ቤቶች አሉ። የታችኛውና የላይኛው።
ወይም ደግሞ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔት) እና የሕግ መምሪያ ምክር ቤት።
ምርጫው በእነዚህ ምክር ቤቶች የተጓደሉ አባላትን፣ ወይም ደግሞ ዘመናቸውን የጨረሱ አባላትን ለመተካት የሚደረግ ነው።
የሁለቱ ምክር ቤቶች ሚና ለየቅል ነው።
የሕግ መመሪያ ምክር ቤት ረቂቅ ሕግ ያወጣል። ረቂቅ ሕግ ላይ ይከራከራል፤ ድምጽ ይሰጣል። ይሁንና ረቂቅ ሕጎቹ በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ውድቅ ሊደረጉ ይችላሉ።
የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ረቂቅ ሕጎችን ብቻም ሳይሆን በፕሬዝዳንቱ የሚቀርቡ እጩ ባለሥልጣናትን፤፤ አምባሳደሮችንም ያጸድቃል። አልፎ አልፎም የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ላይ ጉድፍ ሲገኝ፣ በወንጀል ሲጠረጠር ምርመራ ሊያደርግ ይችላል።
የአሜሪካ የግዛት ተወካይ እንደራሴዎች ሴናተርስ ይባላሉ።
50ዎቹ ግዛቶች እያንዳንዳቸው በሁለት እንደራሴዎች ይወከላሉ። በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የሚቆዩትም ለ6 ዓመታት ነው።
የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባላት ደግሞ የሚወክሉት ግዛቶችን ሳይሆን ወረዳዎችን (ዲስትሪክትስ) ነው።
አንድ ግዛት በሕግ መምሪያ ምክር ቤት የሚኖረው የተወካይ ቁጥር እንደ ግዛቱ የሕዝብ ብዛት የሚወሰን ነው።
በሕግ መምሪያ ምክር ቤት እንደራሴዎች የሥልጣን ዘመናቸውም ሁለት ዓመት ብቻ ነው።
ስለዚህ በዚህ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ሁሉም የታችኛው ምክር ቤት አባላት ወንበር ለውድድር ይቀርባል። ምክንያቱም ዘመኑ ሁለት ዓመት ስለሆነ።
የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት ወንበር ግን ዕድሜ ርዝማኔው 6 ዓመት ስለሆነ ለውድድር የሚቀርበው ከጠቅላላ መቀመጫው አንድ ሦስተኛው ብቻ ነው።
ይህም የሚሆነው ሁሉም 6ኛ ዓመታቸውን በአንድ ተመሳሳይ ዘመን ስለማይጨርሱ ነው።
ከዚህ ባሻገር በዚህ የመዳረሻ ምርጫ ብዙ ግዛቶች ገዢዎቻቸውን ይመርጣሉ። ከንቲባ ይመርጣሉ። የአካባቢ አስተዳዳሪዎችንም ይመርጣሉ፤ ወዘተ።

ማን ሊያሸንፍ ይችላል?
ላለፉት ሁለት ዓመታት ባይደን ሕግ ለማጸደቅ አልተቸገሩም። ይህም የሆነው የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት በአንድ ድምጽ የዲሞክራቶች አብላጫ መቀመጫ ስለነበረው ነው።
በሕግ መወሰኛ ብቻ ሳይሆን በሕግ መምሪያ ምክር ቤትም ቢሆን ዲሞክራቶች ብልጫ ነበራቸው።
ይሁንና የዲሞክራቶች በሁለቱም ምክር ቤቶች ሪፐብሊካኖቸን የሚበልጡበት ወንበር በጣም ጠባብ ነው።
ለምሳሌ በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት 50 ዲሞክራቶችና 50 ሪፐብሊካኖች ተወክለዋል።
የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ካሜላ ሐሪስ ስለሆኑ ግን ዲሞክራቶች አንድ ድምጽ ብልጫን ያገኛሉ።
በሕግ መምሪያ ምክር ቤት ደግሞ 435 መቀመጫዎች ነው ያሉት። ይህ ምክር ቤት አሁን በሪፐብሊካኖች አብላጫ እንደሚያዝ እየተጠበቀ ነው።
በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ደግሞ ከመቶ ወንበሮች 35 ወንበሮች ለውድድር ክፍት ናቸው። ሆኖም የአንዱን ፓርቲ የበላይነት የሚወስኑት አራት ግዛቶች ናቸው።
እነርሱም ኔቫዳ፣ አሪዞና፣ ጆርጂያ እና ፔንሴልቬኒያ ናቸው።
ዋና ዋናዎቹ ጉዳዮች ምንድን ናቸው
አሜሪካ በታሪኳ እንደዚህ ለሁለት ተከፍላ አታውቅም እየተባለ ነው።
የሪፐብሊካኖችና የዲሞክራቶች ጫፍና ጫፍ መርገጥ በጉልህ የታየበት ዘመን ነው።
ሪፐብሊካኖች ዋናው ጉዳይ ብለው የሚያነሱት የስደተኞች መብዛት፣ የወንጀል መበራከት፣ የኑሮ ሰማይ መንካትን ነው።
ባላንጣዎቻቸው ዲሞክራቶች ደግሞ ዲሞክራሲ አደጋ ላይ ሊወድቅ ነው ይላሉ። የጽንስ ማቋረጥ መብት በሪፐብሊካኖች ሊቀለበስ እንደሚችል ይሰጋሉ።
ምን ተጽእኖ ይኖረዋል
የአጋማሽ ዘመን ምርጫ መጪውን ዘመን በሽንቁር የሚያሳይ ነው ይባላል።
በተቀማጩ ፕሬዝዳንት ላይ የሚሰጥ የድጋፍና ተቃውሞ ድምጽ ተደርጎም ይወሰዳል።
ጆ ባይደን በዚህ ረገድ ብዙም ዕድለኛ አይመስሉም። የዩክሬን ጦርነት የነዳጅ ዋጋን አቀጣጥሎታል። ይህ ደግሞ ለብዙ አሜሪካዊያን ብስጭትን ፈጥሯል።
ጆ ባይደን በሕዝብ አስተያየት ለጊዜው ዝቅተኛ ድጋፍ ያላቸው ፕሬዝዳንት ሆነዋል።
ባይደንና ፓርቲያቸው በዚህ አጋማሽ ምርጫ ከቀናቸው የጽንስ ማቋረጥ መብትን ያረጋግጣሉ፣ የጤና መድኅን ሽፋንን ያስፋፋሉ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ለውጥ የሚያመጡ ወሳኝ እርምጃዎችን ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሪፐብሊካኖች ከቀናቸው ደግሞ የጆ ባይደንን ሕልሞች በሙሉ ማምከን ይችላሉ። ይህም በ2024 አዲስ ሪፐብሊካን ፕሬዝዳንት እንዲመረጥ መንገዱን ይጠርጋል።
ምናልባትም ዶናልድ ትራምፕ በድጋሚ ነጩን ቤተ መንግሥት ሊረግጡ ያስችላቸዋል።
የሪፐብሊካኖች ቁጥጥር በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ለዩክሬን የሚደረገው ድጋፍ ላይ፣ በኢራን፣ በአፍጋኒስታንና በሳኡዲ ግንኙነት ላይ ለውጦችን ይዞ ሊመጣ ይችላል።
ከስደተኞች ጋር በተያያዘም በርካታ ማነቆዎች ይኖራሉ።
በ2024 ምን ሊከሰት ይችላል?
ይህ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ በ2024 አሜሪካን ማን ሊመራት እንደሚችል የሚጠቁም ይሆናል።
ትራምፕ የሚደግፏቸው ሪፐብሊካን እጩዎች በለስ ካልቀናቸው ዶናልድ ትራምፕ በድጋሚ ወደ ሥልጣን የመምጣት ህልማቸው ይጨልማል።
በቴክሳስና ፍሎሪዳ የሪፐብሊካን እጩዎች የሆኑት ግሬግ አቦት እና ሮን ዴ ሳንቲስ በድጋሚ ከተመረጡ ምናልባት ከሁለት ዓመት በኋላ ፕሬዝዳንትነት ሊወዳደሩ ይችላሉ።
በተለይ የፍሎሪዳው ሮን ሳንቲስ ከወዲሁ ከትራምፕ ጋር መቃቃር ውስጥ ገብተዋል። ነገር ግን እጅግ ከፍተኛ የሪፐብሊካን ቢሊየነሮች ድጋፍ አላቸው።
ሮን ዴ ሳንቲስን ለእውቅና ያበቋቸው ትራምፕ ቢሆኑም አሁን ግን ‘እኔን በደንብ አያመሰግነኝም፤ ላደረኩለት ነገር ዋጋ አልሰጠም’ በሚል ትራምፕ ሰውየውን ገሸሽ አድርገዋቸዋል።
ይሁንና ሮን ዴ ሳንቲስ አሁን በዚህ አጋማሽ ምርጫ በድጋሚ ከተመረጡ ምናልባትም በ2024 ትራምፕን ሳይሆን ሳንቲስን ይሆናል በነጩ ቤተ መንግሥት የምናየው።
ዲሞክራቶች በበኩላቸው በ2024 የተስፋ ጭላንጭል ለማየት እንኳ ገና ከወዲሁ ሚቺጋንን፣ ዊስኮንሰንን እና ፔንስልቬኒያን መቆጣጠር ይኖርባቸዋል።
እንደ ሕዝብ አስተያየት መለኪያዎች ግምት ከሆነ ግን ዲሞክራቶች ተስፋ ቢስ ሆነዋል።












