ጆ ባይደን የአሜሪካንን ምርጥ የጦር ጄቶች ለዩክሬን አልሰጥም አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እጅግ ዘመናዊ ናቸው የሚባሉትን አሜሪካ ሰራሽ ኤፍ-16 የጦር ጄቶችን ለዩክሬን አሳልፈው እንደማይሰጡ ገለጹ።
ጆ ባይደን ትናንት ሰኞ ከጋዜጠኛ “ኤፍ-16 ጄቶች ለዩክሬን ይሰጣሉ ወይ?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ “በፍጹም” የሚል አጭር መልስ ሰጥተዋል።
ጆ ባይደን ይህን ከማለታቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ጀርመንም በተመሳሳይ ተዋጊ ጄቶቿን ለዩክሬን አሳልፋ እንደማትሰጥ ይፋ አድርጋ ነበር።
ዩክሬን በበኩሏ የአየር ክልሏ በሩሲያ በተደጋጋሚ እየተጣሰ ስለሆነ ያን ለመቋቋም የግድ ዘመናዊ ተዋጊ ጄቶች ያስፈልጉኛል እያለች ነው።
“ኤፍ-16” ተዋጊ ጄቶች በዓለም ላይ አስተማማኝ ከሚባሉ የአየር ላይ ውጊያ ጄቶች የሚመደቡ ሲሆን፣ እነዚህኑ ጄቶች ከአሜሪካ ባሻገር ቤልጂየም እና ፓኪስታን ታጥቀዋቸዋል።
ዩክሬን አሁን እየተጠቀመችባቸው ያሉት ብዙዎቹ የጦር ጄቶች በሶቭየት ኅብረት ጊዜ የተመረቱ ናቸው።
እነዚህ ያረጁ ያፈጁ ጄቶች አገልግሎት ላይ ይውሉ የነበረው ዩክሬን ነጻነቷን ከማወጇ በፊት ነው።
በዚህም የተነሳ ዩክሬን ሩሲያን በአየር ልትቋቋማት ተስኗታል።
ዩክሬን ምዕራባውያን ዘመናዊ ጄቶችን ሊሰጡኝ ይገባል ስትል ቀን ተሌት ብትወተውትም ጆ ባይደን ይህን ልመና ጆሮ ዳባ ልበስ ብለውታል።
ፕሬዝዳንቱ ከጄቶች በሻገር ግን በሌሎች ወታደራዊ ዘርፎች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለዩክሬን እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።
አሜሪካ ባለፈው ሳምንት ለዩክሬን ‘ኤብራምስ’ የሚባሉ እጅግ ዘመናዊ 31 የጦር ታንኮችን እንደምትሰጥ ቃል ገብታ እንደነበረ ይታወሳል።
ይሁንና እነዚህ ታንኮች ዩክሬን ጦር ሰፈር ለመድረስ ቢያንስ አንድ ዓመት ይወስድባቸዋል።
የአሜሪካንን እርዳታ ተከትሎ ጀርመን እና ዩናይትድ ኪንደግምም ተመሳሳይ ወታደራዊ ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።
ጀርመን ለዩክሬን እሰጥሻለሁ ያለቻት ‘ሊዮፓርድ-2’ የሚባሉትን ዘመናዊ ታንኮች ነው።
የጀርመን መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ለአንድ የአገሬው ጋዜጣ እንዳሉት “ከሊዮፓርድ ታንኮች በተጨማሪየ አየር ጄቶችን ወደ ዩክሬን የመላኩ ነገር የማይመስል ነው።”
ሾልዝ ጨምረው እንዳስረዱት ተዋጊ ጄቶችን ለዩክሬን መስጠት ሁኔታዎችን ይበልጥ ማባባስ ይሆናል።
ሞስኮ ምዕራባውያን ዩክሬንን በመጠቀም የራሳቸውን ጦርነት ከሩሲያ ጋር እያደረጉ ነው ስትል ትከሳለች።
የፈረንሳዩ ኢማኑኤል ማክሮን ለዩክሬን በምንሰጠው ድጋፍ “ይህን አናደርግም የምንልበት ሁኔታ አይኖርም” ብለዋል።
ይሁንና ለዩክሬን በሚደረጉ ድጋፎች ውስጥ ጦርነቱን ማቀጣጠል እንዳይኖር ጥንቃቄን ይሻል፤ ዩክሬን ራሷን የመከላከል አቅምንም ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል ብለዋል።
ሌሎች እንደ ኔዘርላንድስ ያሉ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ተዋጊ ጄቶችን ወደ ኪዬቭ ለመላክ ገና ውሳኔ ላይ አልደረሱም።












