እስራኤል በጋዛ በሚገኝ ትምህርት ቤት በፈጸመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 16 ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ በሚገኝ ትምህርት ቤት ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 16 ሰዎች መገደላቸውን የፍልስጤም ባለስልጣናት ገለጹ። በርካቶች ደግሞ ቆስለዋል።
ትምህርት ቤቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮችን አስጠልሎ እንደነበር በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል በበኩሉ በአል-ጃኡኒ ትምህርት ቤት አካባቢ የሚንቀሳቀሱ በርካታ አሸባሪዎችን ዒላማ ማድረጉን ተናግሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በካምፑ ውስጥ በሚገኝ መኖሪያ ቤት ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት 10 ሰዎች መሞታቸውን መረጃዎች ጠቁመዋል።
ጥቃት ከደረሰበት የኑሴይራት ትምህርት ቤት የተገኘ ቪዲዮ በጭስ በተሞላ መንገድ፣ በአቧራ እና በፍርስራሽ በተሸፈነ ጎዳና ላይ ቁስለኞች ይታያሉ።
የዓይን እማኞች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ጥቃቱ ያነጣጠረው በትምህርት ቤቱ የላይኛው ፎቅ ላይ ነው።
ቢቢሲ እስከ 7 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ህንጻውን እንደ መጠለያ ይጠቀሙበት እንደነበር ተረድቷል።
አንዲት ሴት ህንጻው በተመታ ጊዜ ቁርዓን ሲቀሩ የነበሩ ህጻናት መገደላቸውን ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግራለች።
"ያለ ማስጠንቀቂያ ትምህርት ቤቱን ዒላማ ሲያደርጉ ይህ ለአራተኛ ጊዜ ነው" ስትል ተናግራለች።
ዒላማ የተደረገው የሐማስ ፖሊስ ይጠቀምበት ነበር የተባለ ክፍል መሆኑን የአከባቢው ምንጭ ተናግሯል። ቢቢሲ ግን ይህን ጉዳይ ማረጋገጥ አልቻለም።
በእስራኤል ጥቃት ከተገደሉት መካከል አምስት የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች ይገኙበታል ብሏል ሐማስ። ቤተሰቦቻቸውም ኢላማ ተደርገዋል ተብሏል።
ከመስከረም 26 ጥቃት በኋላ በጋዛ ከ100 በላይ ጋዜጠኞች ሕይወታቸውን አጥተዋል ሲል ድንበር የለሹ የጋዜጠኖች ቡድን አስታውቋል።
የእስራኤል ጦር ኤክስ ላይ ባሰፈረው መግለጫ የትምህርት ቤቱን ህንጻዎች መምታቱን አረጋግጦ “በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ብዙ እርምጃ ተወስዷል” ብሏል።
የሐማስ ታጣቂዎች በጦራችን ላይ ጥቃት ለመፈጸም ቦታውን እንደ “መደበቂያ” ይጠቀሙበት ነበር ሲልም አክሏል።

ሐማስ በእስራኤል ላይ ለሚያደርሰው የሽብር ጥቃት የሲቪል ተቋማትን እንደ መሸሸጊያ በመጠቀም ዓለም አቀፍ ህግን ስልታዊ በሆነ መንገድ መጣሱን ቀጥሏል ሲልም ጨምሮ ገልጿል።
ሐማስ በበኩሉ ጥቃቱን “መከላከል በማይችሉ ተፈናቃዮች ላይ የተፈጸመ የጅምላ ጭፍጨፋ” ሲል ገልጾታል።
ከሞቱት እና ከቆሰሉት መካከል አብዛኛዎቹ ሴቶች፣ ህጻናት እና አዛውንቶች መሆናቸውን ቡድኑ በእንግሊዝኛ የቴሌግራም ቻናሉ አስፍሯል።
በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የሚደረገው ስምምነት ከወራት በኋላ ይሳካል የሚል አዲስ ተስፋ እየጨመረ ነው።
እስራኤል ታጋቾች በሚለቀቁበት ሁኔታ ላይ ለመነጋገር በሚቀጥለው ሳምንት የተደራዳሪ ቡድን እንደምትልክ አስታወቃለች።
ይህ የሆነው አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን ሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነትን በተመለከተ ባለው አቋም ላይ “በጣም ጉልህ የሆነ ማስተካከያ” ለማድረግ መስማማቱን ከገለጹ በኋላ ነው።
ለስምንት ወራት ያህል በዘለቀው ጦርነት ቤታቸውን ጥለው ለተፈናቀሉ 1.7 ሚሊዮን ሰዎች ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማት እንደ መጠለያ ጣብያነት እያገለገሉ ነው።












