በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዙ ወታደራዊ መሪዎች “የሳህል አገራት ኮንፌዴሬሸን” መሠረቱ

የፎቶው ባለመብት, Burkina Faso Presidency
በምዕራብ አፍሪካ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ላይ የወጡት የቡርኪና ፋሶ፣ የማሊ እና የኒጀር ወታደራዊ መሪዎች “የሳህል አገራት ኮንፌዴሬሽን” የተባለ ጥምረት መሠረቱ።
የወታደራዊ ሁነታ መሪዎቹ ውሳኔ ሦስቱን አገራት ከምዕራብ አፍሪካ አገራት የኢኮኖሚ ማኅብረሰብ (ኤኮዋስ) ስብስብ ውጪ የሚያደርግ ነው።
የኒጀር መሪ ጄኔራል አብዱራሃማኔ ቺያኒ፣ የማሊው ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ እና የቡርኪና ፋሶው መፊ ሻምበል ኢብራሂም ትራኦሬ የመሠረቱተ ጥምረት “በውጪ ኃይል ቁጥጥር ስር አይወድቅም” ብለዋል።
የሦስቱ አገራት ወታደራዊ መሪዎች ትናንት ቅዳሜ ሰኔ 29/2016 ዓ.ም. በኒጀር መዲና ኒያሚን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ኮንፌዴሬሽን ማቋቋማቸው እንደ ባንክ ያሉ የጋራ ተቋማትን ዜጎቻቸው በጋራ እንዲጠቀሙ ያስችላል ብለዋል።
ኒጀር፣ ማሊ እና ቡርኪና ፋሶ ጥምረቱን መመሠረታቸው የሳህል አገራት ዜጎች በአገራቱ መካከል በነጻነት እንዲዘዋወሩ እና መሠረታዊ አገልግሎቶችን ከተመሳሳይ ተቋማት ለማግኘት ያስችላቸዋል ብለዋል።
የኒጀሩ መሪ ከኤኮዋስ ይልቅ “ከውጭ ኃይሎች ነጻ የሆነ እና በአፍሪካ ዕሴቶች ላይ የተመሠረተ ሰላም እና አብሮነት ያለበት” ኅብረት መመሥረት አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል ብለዋል።
የቡርኪና ፋሶ ወታደራዊ መሪ ደግሞ በኤክስ ገጻቸው ላይ በሳህል አገራት ኮንፌዴሬሽን ስር “በጋራ እውነተኛ ነጻነታችንን እንመሠርታለን” ብለዋል።
ሻምበል ትራኦሬ “ይህች አህጉር በኢምፔሪያሊስቶች የሚደርስባት ስቃይ እንደቀጠለ ነው” ብለዋል።
ሦስቱ አገራት በቅኝ ገዢዋ ፈረንሳይ ቁጥጥር ስር ይገኛል ካሉት የመዕራብ አፈሪካ አገራት የምጣኔ ሀብት ትብብር ማኅበረሰብ - ኤኮዋስ ከስድስት ወራት በፊት መውጣታቸው ይታወሳል።
የኒጀሩ መሪ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሦስቱ አገራት ኤኮዋስን መልሶ የመቀላቀል ፍላጎት ጨርሶ እንደሌላቸው ተናግረዋል።
በመፈንቅለ መንግሥት የየአገራቸውን የመንግሥት ሥልጣን የጨበጡት የኒጀር፣ የቡርኪና ፋሶ እና የማሊ መሪዎች የጽንፈኛ እስላማዊ ቡድን እንቅስቃሴ ስጋት ውስጥ ይገኛሉ።
የወታደራዊ ሁንታ መሪዎቹ የጽንፈኛ ቡድኖችን እንቅስቃሴ ለመዋጋት እርዳታ ፍለጋ ፊታቸውን ወደ ሩሲያ አዙረዋል።
ሦስቱም አገራት በቀጠናው ጂሃዲስቶችን ሲዋጋ የነበረውን የፈረንሳይ ጦር ከግዛታቸው ማስወጣታቸው ይታወሳል።












