እንግሊዝ እና ኔዘርላንድስ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቀሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትላንት ምሽት በተካሄዱ የአውሮፓ ዋንጫ ሁለት የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች እንግሊዝ እና ኔዘርላንድስ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቀሉ።
መጀመሪያ ላይ የተገናኙት እንግሊዝ እና ስዊትዘርላንድ ነበሩ።
ጨዋታው ያለምንም ጎል ሊጠናቀቅ ነው ሲባል ነበር ብሪል ኤምቦሎ ስዊዘርላንድን ቀዳሚ ያደረገች ጎል በ75ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው።
ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ የአርሰናሉ ቡካዮ ሳካ በግል ጥረቱ ባስቆጠራት ጎል አንግሊዝ አቻ አደረገ።
ጨዋታው በዚህ ውጤት የተጠናቀቀ ሲሆን በተጨማሪ ሰዓትም ሁለቱ ቡድኖች ኳስ እና መረብ ለማገናኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።
ሁለቱ ቡድኖች ወደ መለያ ምት ባመሩበት ሰዓት የእንግሊዙ ግብ ጠባቂ ጆርዳን ፒክፎርድ የስዊትዘርላንዱ ማኑዌል አካንጂ የመታውን የመጀመሪያውን ኳስ ለማዳን ቻለ።
ቀሪዎቹ መለያ ምቶች እንግሊዝ ማስቆጠሯን ተከትሎ ወደ ግማሽ ፍጻሜው መቀላቀሏን አረጋግጣለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሁለተኛው የምሽቱ ጨዋታ ደግሞ ኔዘርላንድስ እና ቱርክ ተገናኝተዋል።
በጨዋተው ኔዘርላንድስ ከመመራት ተነስታ ባስቆጠረቻቸው ሁለት ጎሎች ግማሽ ፍጻሜውን መቀላቀል ችላለች።
ቱርክ በመጀመሪያው አጋማሽ በተከላካዩ ሳሜት አካይዲን ቀዳሚ ለመሆን ችላ ነበር።
በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ያልነበሩት ኔዘርላንዶች በሁለተኛው አጋማሽ ስቴፋን ደ ቨርጅ ብርቱካናዎቹን አቻ ለማድረግ ቻለ።
ጫናቸውን ያበረቱት ብርቱካናማዎች ሜርት ሙለዱር በራሱ ጎል ላይ ባስቆጠራት ጎል ጨዋታውን 2 ለ 1 ለመምራት ቻሉ።
በጨዋታው መገባደጃ ላይ አቻ ለመሆን ሲጥሩ የነበሩት ቱርኮች ተደጋጋሚ ጥሩ ዕድሎች ቢፈጥሩም ሊሳካላቸው አልቻለም።
እንግሊዝ እና ኔዘርላንድስ በግማሽ ፍጻሜው ረቡዕ ዕለት ዶርትሙንድ ላይ የሚጫወቱ ይሆናል።
በሌላኛው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ፈረንሳይ እና ስፔን ይገናኛሉ።












