በአዲስ አበባ የቤት ግብር ማሻሻያ ተግባራዊ እንዳይሆን በፍርድ ቤት ያሳገደው ክስ ምን ይዟል?

ተቃዋሚው እናት ፓርቲ የቤት ግብር ማሻሻያን በተመለከተ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ ላይ የመሠረተውን ክስ መርታቱን ተከትሎ ውሳኔውን ለማስፈጸም መዝገብ እንደሚከፍት አስታወቀ።
ጉዳዩን ሲመለከተው የነበረው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የፌደራል አስተዳደር ሥነ ሥርዓት ፍትሐ ብሔር ችሎት "መመሪያው ተፈጻሚነት ሊኖረው አይገባም" ተብሎ መመሪያው እንዲሻር በሙሉ ድምጽ ውሳኔ ያስተላለፈው ጥር 9/2017 ዓ.ም. ነበር።
በዚሁ ዕለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሌሊሴ ደሳለኝ የዕግድ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ለ15 ቀናት የቆው የፕሬዝዳንቷ የዕግድ ትዕዛዝ፤ "ውሳኔው ከመፈጸም እና ውሳኔው ላይ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ እንዳይሰጥ" የከለከለ ነበር።
ይህ የ15 ቀናት ዕግድ መጠናቀቁን ተከትሎ እናት ፓርቲ ሰኞ፣ ጥር 26/2017 ዓ.ም. መግለጫ ሰጥቷል። ፓርቲው በመግለጫው የፍርድ ቤት ውሳኔውን ለማስፈጸም የአፈጻጸም መዝገብ እንደሚከፍት አስታውቋል።
እናት ፓርቲ በክርክር የረታበትን አቤቱታ ለፍርድ ቤት ያቀረበው ከአንድ ዓመት ከሰባት ወራት በፊት ሐምሌ 2015 ዓ.ም. ነው።
ጉዳዩ የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰጠው ብይን መሠረት አቤቱታውን አሻሽሎ ባለፈው ዓመት ጥቅምት 2016 ዓ.ም ለችሎቱ አቅርቧል።
ፓርቲው ያቀረበው አቤቱታ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ ያወጣው እና "ከሕግ ውጭ ሥራ ላይ የዋለ መመሪያ" እንዲሰረዝ የሚጠይቅ ነው።
አቤቱታው "ወቅቱን ግምት ውስጥ ያስገባ የንብረት ግብር ለማስከፈል" በሚል በቢሮው "የወጣው መመሪያ የሕግ መሠረት የሌለው" መሆኑን ጠቅሷል። ከዚህ በተጨማሪም ቢሮው "እንዲህ ዓይነት መመሪያ እንዲያወጣ በሕግ ሥልጣን ሳይሰጠው ያወጣው መመሪያ" መሆኑን የጠቀሰው ፓርቲው ይህ መመሪያ እንዲሰረዝ ክሱ ጠይቋል።
ለእናት ፓርቲ አቤቱታ ምክንያት የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስ ቢሮ ከሁለት ዓመታት ገደማ በፊት ያቋቋመው የንብረት ግብር ማስተባበሪያ ጊዜያዊ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ያዘጋጀው ጥናት ነው።
ቢሮው ጽህፈት ቤቱን ያቋቋመው በንጉሡ ጊዜ የወጣውን የከተማ ቦታ ኪራይ እና የከተማ ቤት ግብር አዋጅ መሠረት በማድረግ መሆኑን በወቅቱ ገልጾ ነበር።
የከተማዋ ፋይናንስ ቢሮ የፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ የጥናት ውጤት ለሌሎች የከተማ አስተዳደሩ መዋቅሮች በሚያዝያ 5/2015 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ አስተላልፏል። ቢሮው በዚህ ደብዳቤ የቤት ግብር ማሻሻያ ተግባራዊ እንዲደረግም ጠይቋል።
እናት ፓርቲ በአቤቱታው ቢሮው መመሪያውን ያስተላለፈው "የመመሪያ አወጣጥ ሥርዓትን ተከትሎ የወጣ አለመሆኑን" ጠቅሷል።
እናት ፓርቲ በአቤቱታው ያቀረበው የመጀመሪያ ፍሬ ነገር ቢሮው ያወጣው መመሪያ "የሕግ መሠረት የለውም" የሚል ነው።
ማንኛውም ተቋም መመሪያ ለማውጣት "በሕግ የተሰጠ ሥልጣን" ሊኖረው እንደሚገባ የጠቆመው የእናት ፓርቲ አቤቱታ ቢሮው መመሪያውን ለማውጣት የጠቀሰው አዋጅ "ስለ ንብረት ግብር የወጣ አይደለም" ብሏል።
ፓርቲው "በኢትዮጵያ የንብረት ግብር ለማስከፈል የወጣ ሕግ በሌለበት ሁኔታ "የንብረት ግብር ማስተባበሪያ ጊዜያዊ ፕሮጀክት ጽ/ቤት የሚባል የሕግ መሠረት አካል አቋቁሞ በማስጠናት የንብረት ግብር እንዲከፈል መመሪያ ማውጣት ፍፁም የሆነ የሕግ ጥሰት ነው" ሲል አቤቱታውን አቅርቧል።
ሁለተኛው የእናት ፓርቲ አቤቱታ ፍሬ ነገር መመሪያ ከማውጣት ሥልጣን ጋር የተያያዘ ነው። አቤቱታው በ1968 የወጣውን አዋጅ ለማስፈጸም የወጣው ደንብ "ማንኛውም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንቡን ለማስፈጸም መመሪያ ማውጣት እንደሚችል አንድም ሥልጣን አልሰጠም" ሲል ፍሬ ነገሩን አስረድቷል።

የፎቶው ባለመብት, ENAT PARTY/FB
ፓርቲው በአቤቱታው "ደንቡ ሥልጣን ባልሰጠበት ሁኔታ ለዚያውም የንብረት ግብር እንዲከፈል የሚፈቅድ ሕግ በሌለበት ሁኔታ የንብረት ግብር ለማስከፈል መመሪያ ማውጣት የሕግ መሠረት ስለሌለው መመሪያው እንዲሰረዝ" ሲል ዳኝነት ጠይቋል።
ሦስተኛው የፓርቲው መከራከሪያ ቢሮው ያወጣው መመሪያ በ2012 ዓ.ም. የወጣውን የፌደራል የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ ተከትሎ ያልወጣ መሆኑን በመጥቀስ የቀረበ ነው።
አዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስ ቢሮ በበኩሉ በፓርቲው ለቀረቡ አቤቱታዎች መልስ ሰጥቷል። ቢሮው በሰጠው መልስ የግብር መጠንን ከ47 ዓመት በኋላ ባለበት አግባብ ማስቀጠል "አሁናዊ እና ነባራዊ አገር አቀፍ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች የማይፈቅዱ" መሆኑን ጠቅሷል።
ይህን ተከትሎም የእናት ፓርቲ አቤቱታ "የሕግም ሆነ የማስረጃ ድጋፍ የሌለው ከመሆኑን ባሻገር ተገቢነት ያለው አይደለም። ስለዚህ አቤቱታው ውድቅ ይደረግልን" ሲል ዳኝነት ጠይቋል።
ቢሮው አክሎም አመልካች "እንዲከለስላቸው የሚጠይቁትን መመሪያ ቁጥሩን ጠቅሰው ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት መመሪያ የሌለ መሆኑን" ጠቅሷል።
"በተጠሪ [ፋይናንስ ቢሮ] የወጣ እና ሥራ ላይ የሚገኝ መመሪያ የለም" ያለው ቢሮው፤ "መመሪያው ሊሰረዝ ወይም ሊከለስ ይገባል በማለት የቀረበው ክስ የሕግ መሠረት የሌለው ስለሆነ ውድቅ ይደረግልን" ብሏል።
ግራ ቀኙ የቃል ክርክር ባደረጉበት ወቅትም ቢሮው ይህን መከራከሪያ በአጽንኦት አሰምቷል።
በቃል ክርክሩ ወቅት "ማዘጋጃ ቤታዊ ታሪክ ማሻሻያ የማድረግ ሥልጣን በተሰጠው መሠረት ፋይናንስ ቢሮ ጥናቱን መሠረት አድረጎ [የታሪፍ] ማሻሻያ አደረገ እንጂ አዲስ መመሪያ ወይም የንብረት ግብርን በተመለከተ የሚከፈልበት ታክስ በሌለበት በእኛ በኩል የወጣ መመሪያ የለም" ሲል ተሟግቷል።
የግራ ቀኙን ክርክር የተመለከተው ፍርድ ቤቱም ሦስት ጭብጦችን ይዞ ውሳኔ ሰጥቷል።
የመጀመሪያው ጭብጥ የንብረት ግብር ማስተባበሪያ ጊዜያዊ ፕሮጀክት ጽ/ቤት የወጣው ሰነድ መመሪያ ነው? አይደለም? የሚለው ነው።
ፍርድ ቤቱ ይህን ጭብጥ በተመለከተ የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጁን በመጥቀስ በአስተዳደር ተቋም የሚወጣ እና በሰዎች መብት ወይም ጥቅም ላይ ውጤት የሚያስከትል የሕግ ሰነድ መመሪያ መሆኑን ገልጿል።
ይህን ተከትሎ የጥናት ሰነዱ "ግብር ከፋዮች ግብር እና ታክስ እንዲከፍሉ ግዴታ የጣለ" መሆኑ እንዲሁም "ግብር እና ታክስ ሲከፈል የነበረ" መሆኑን በመጥቀስ፤ "የጥናት ሰነዱ እንደ መመሪያ ካልተቆጠረ በስተቀር ሌላ ትርጉም መስጠት አይቻልም" ሲል ሰነዱ መመሪያ ነው በማለት ደምድሟል።
ሁለተኛው ጭብጥ መመሪያው የመመሪያ አወጣጥ መርሆዎችን ተከትሎ መውጣቱን የተመለከተበት ነው።
ችሎቱ መመሪያው "የሕግ አስተያየት ሳይታከልበት የወጣ ስለሆነ በአጠቃላይ ያልተፈተነ እና የመመሪያ አወጣጥ ሥርዓቱን እና ሕጋዊነቱ ተመርምሮ ያልተመዘገበ ስለሆነ ሕጋዊነቱ እና ተፈጻሚነቱ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው" ብሏል።
ሦስተኛው እና የመጨረሻው ጭብጥ የፋይናንስ ቢሮው መመሪያ የማውጣት ሥልጣን ላይ ያተኮረ ነው። ችሎቱ ይህን ጭብጥ በተመለከተ "ተጠሪ [የፋይናንስ ቢሮ] መመሪያ በማውጣት ሥራ ላይ እንዲውል ማድረጉ ከሥልጣን ገደቡ ውጪ እና ያለ ሕግ መሠረት የወጣ መመሪያ መሆኑን መገንዘብ ይችላል" ብሏል።
ይህን ተከትሎ በሦስት ዳኞች የተሰየመው ችሎት "በፋይናንስ ቢሮ በኩል ወደ ተግባር እንዲለወጥ የተጻፈው የንብረት ግብር ማሻሻያ ጥናት ሰነዱ በፍርድ ቤቱ መመሪያ መሆኑ" መረጋገጡን አስታውሷል።
በመሆኑም "መመሪያው ተፈጻሚነት ሊኖረው አይገባም" ተብሎ መመሪያው እንዲሻር በሙሉ ድምጽ ውሳኔ ሰጥቷል።












