የብልፅግና ፓርቲ መደበኛ ጉባኤ የትኞቹን የሥራ አስፈጻሚ አባላት በአዲስ ተካ?

የጉባኤው ተሳታፊዎች

የፎቶው ባለመብት, Prosperity Party

የብልፅግና ፓርቲ መደበኛ ጉባኤ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ካሉት 45 አባላት ውስጥ አስራ ስምንቱን በአዲስ ተካ። አማራ ክልል፤ በመጀመሪያው የፓርቲው መደበኛ ጉባኤ ከተወከለባቸው ስምንት የሥራ አስፈጻሚ አባላት መካከል አምስቱን በመተካት ብዛት ያላቸው አዲስ አባላት የተወከሉለት ቀዳሚው ክልል ሆኗል።

ገዢው ብልፅግና ፓርቲ ለሦስት ቀናት የቆየውን ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤውን ያጠናቀቀው እሁድ ጥር 25/2016 ዓ.ም. ነው። በአዲስ አበባ ከተማ የዓድዋ ድል መታሰቢያ አዳራሽ የተደረገው የብልፅግና መደበኛ ጉባኤ፤ የመጨረሻ ቀን ውሎውን ያሳለፈው የፓርቲው አመራሮችን ምርጫ በማድረግ ነው።

በዚህ ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በድጋሚ የፓርቲው ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል። ፓርቲውን በምክትል ፕሬዝዳንትነት ሲመሩ የነበሩት አቶ ተመስገን ጥሩነህ እና አቶ አደም ፋራህም በድጋሚ ለዚሁ የድርጅት ኃላፊነት ተመርጠዋል።

የብልፅግና መደበኛ ጉባኤ ያደረገው ሌላኛው ምርጫ፤ ከዚህ ቀደም "ማዕከላዊ ኮሚቴ" በሚል ስያሜ ለሚጠራው እና በአዲሱ የፓርቲው መተደዳደሪያ ደንብ መሠረት "ምክር ቤት" ለተባለው የፓርቲው አመራር መዋቅር አባላት ለመምረጥ የተካሄደ ነበር። በዚህ ምርጫ 225 የምክር ቤት አባላት እንደተመረጡ ፓርቲው አስታውቋል።

ከእነዚህ የፓርቲው ምክር ቤት አባላት መካከል ደግሞ 45 የፓርቲው አመራሮች በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ተመርጠዋል። ብልፅግና ፓርቲ ይፋ ያደረገው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ዝርዝር እንደሚያሳየው፤ በ2014 ዓ.ም. በተደረገው የፓርቲው የመጀመሪያ መደበኛ ጉባኤ ከተመረጡት የኮሚቴው አባላት መካከል 37.7 በመቶ የሚሆኑት በአዲስ ተተክተዋል።

ደመቀ መኮንን፣ ይልቃል ከፋለ፣ ዳግማዊት ሞገስ፣ ሰማ ጥሩነህ እና ግርማ የሺጥላ (በሕይወት የሌሉ)
የምስሉ መግለጫ, በአዲስ የተተኩት የአማራ ክልል የብልፅግና ቅርንጫፍ የቀድሞው ሥራ አስፈጻሚ አባላት ደመቀ መኮንን፣ ይልቃል ከፋለ፣ ዳግማዊት ሞገስ፣ ሰማ ጥሩነህ እና ግርማ የሺጥላ (በሕይወት የሌሉ)

አማራ ክልል

ከ2015 ዓ.ም. መጨረሻ ጀምሮ በግጭት ውስጥ ያለው የአማራ ክልል ከዚህ ቀደም በብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ውስጥ የተወከለባቸው አብዛኛዎቹ አመራሮቹ በአዲሱ የኮሚቴው የአባላት ዝርዝር ውስጥ አልተካተቱም።

የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ካሉት 45 አባላት ውስጥ ስምንቱ የሚመረጡት ከአማራ ክልል ነው። በመጀመሪያው መደበኛ ጉባኤ ከክልሉ ከተመረጡት ሥራ አስፈጻሚ አባላት መካከል የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የቀድሞው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ እና የቀድሞ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ ይገኙበታል።

ሚያዝያ 2015 ዓ.ም. የተገደሉት የቀድሞ የብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ እና የፓርቲው የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ሰማ ጥሩነህም ከክልሉ የተመረጡ የሥራ አስፈጻሚ አባላት ነበሩ።

የብልፅግና ፓርቲ መደበኛ ጉባኤ እሁድ ባደረገው ምርጫ እነዚህን አምስት የሥራ አስፈጻሚ አባላት በአዲስ ተክቷል። አማራ ክልልን በመወከል የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴውን ከተቀላቀሉ አመራሮች መካከል የወቅቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር አብዱ ሁሴን እና የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ዣንጥራር አባይ ይገኙበታል።

በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሉነሽ ደሴ እና የብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ ሌሎቹ ከክልሉ የተመረጡ አዲስ የሥራ አስፈጻሚ አባላት ናቸው።

ከአማራ ክልል ከተመረጡት ስምንት ሥራ አስፈጻሚዎች ውስጥ ሦስቱ ከዚህ ቀደምም የኮሚቴው አባል ነበሩ። በኮሚቴው አባልነታቸው የቀጠሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ እና የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ናቸው።

የብልፅግና

ጋምቤላ እና ኦሮሚያ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ርዕሰ መስተዳድር እና ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በመቀየሩ ምክንያት አዲስ የሥራ አስፈጻሚ አባላትን ያስመረጠው አማራ ክልል ብቻ አይደለም። ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ክልሉን የሚመሩ አዲስ አመራሮች የተመረጡበት ጋምቤላ፤ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ ያሉትን ሁለት ተወካዮች በአዲስ ተክቷል።

የቀድሞው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡመድ ኡጁሉ እና ምክትላቸው አቶ ቴንኩዌይ ጆክ ነሐሴ 2016 ዓ.ም. ከሥልጣን የተነሱት "በፓርቲው ተገምግመው" እንደሆነ በወቅቱ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረው ነበር። ሁለቱ የቀድሞ የክልሉ አመራሮች ጋምቤላን የወከሉ የሥራ አስፈጻሚ አባላት ነበሩ።

በአዲሱ ምርጫ መሠረት ጋምቤላን በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት የወከሉት የወቅቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ እና ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ጋልዋክ ሮን ናቸው።

በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ ባለው የተወካዮች ብዛት ቀዳሚ የሆነው የኦሮሚያ ክልልም፤ ካሉት 10 ተወካዮች ውስጥ ሁለቱን በአዲስ ተክቷል። ኦሮሚያ ክልል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለሥራ አስፈጻሚነት የተወከሉለት ክልል ነው።

በመጀመሪያው የብልፅግና መደበኛ ጉባኤ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ዶ/ር አለሙ ስሜ እና የፓርቲው የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳም ለሥራ አስፈጻሚ አባልነት ከክልሉ ተወክለው ነበር። ሁለተኛው የፓርቲው መደበኛ ጉባኤ በበኩሉ በአሁኑ ምርጫ ሁለቱን አመራሮች በአዲስ ተክቷል።

ኦሮሚያ ክልልን ወክለው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴውን የተቀላቀሉት የብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ እና የሸገር ከተማ ከንቲባ ዶ/ር ተሾመ አዱኛ ናቸው።

ብልፅግና

ደቡብ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ

ከብልፅግና ፓርቲ የመጀመሪያ መደበኛ ጉባኤ በኋላ እንደ አዲስ የተዋቀሩት የደቡብ ኢትዮጵያ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎችም በተመሳሳይ አዲስ የሥራ አስፈጻሚ አባላትን አስመርጠዋል።

በመጀመሪያው ጉባኤ የሥራ አስፈጻሚ አባላትን ሲመርጥ አሁን ማዕከላዊ ኢትዮጵያ በሚል ከተዋቀሩት አካባቢዎች ሦስት አባላት ተወክለው ነበር። የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያ ካሚል፣ የቀድሞው ደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው እንዲሁም በሚኒስትር ማዕረግ የብልፅግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ ከእነዚህ አካባቢዎች የተገኙ አባላት ነበሩ።

በአዲሱ ምርጫ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል በአባልነት ሲቀጥሉ ሁለቱ አባላት ተተክተዋል። ከክልሉ የተመረጡት አዲሶቹ የሥራ አስፈጻሚ አባላት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው እና የብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዶ/ር ዲላሞ ኦቶሬ ናቸው።

ከመጀመሪያው መደበኛ ጉባኤ በኋላ የተመሠረተው ደቡብ ኢትዮጵያ ክልልም በተመሳሳይ ሁለት አዲስ አባላትን ለሥራ አስፈጻሚ አባልነት አስመርጧል። በፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ውስጥ በአራት አባላት የሚወከለው ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤ የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደን እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ዶ/ር ተስፋዬ በልጅጌን በአባልነት ይዞ ቀጥሏል።

ከዚህ ቀደም ከክልሉ ተወክለው የነበሩት የብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ሞገስ ባልቻ እና የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙ በአንጻሩ በአዲስ አባላት ተተክተዋል። ሁለቱን አመራሮች የተኳቸው የባህል እና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የጂንካ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር አበባየሁ ታደሰ ናቸው።

ብልፅግና

ብልፅግና ፓርቲ የመንግሥት ሥልጣንን የማይቆጣጠርበት የትግራይ ክልል፤ በፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ በሁለት አባላት ይወከላል። የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዶ/ር አብርሃም በላይ እና የቀድሞዋ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ከዚህ ቀደም ክልሉን ወክለው የኮሚቴው አባል ነበሩ።

በአሁኑ ምርጫ ዶ/ር አብርሃም በአባልነታቸው ሲቀጥሉ ዶ/ር ሊያ ተተክተዋል። የቀድሞዋን የጤና ሚኒስትር የተኩት የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታዜር ገብረእግዚአብሔር ናቸው።

የአፋር፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና የሐረሪ ክልሎችም በተመሳሳይ ከዚህ ቀደም የተወከሉባቸው የሥራ አስፈጻሚ አባላት በከፊል ተክተዋል። ሶማሌ፣ ሲዳማ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ደግሞ የተወከሉባቸው የሥራ አስፈጻሚ አባላት ሳይቀይሩ የቀጠሉ ክልሎች ናቸው።