ዩክሬን ወደ ሩሲያ ዘልቃ ጥቃት በመፈጸሟ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ

በጥቃት የወደመ መኖሪያ ቤት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የዩክሬን ወታደሮች ባልተለመደ መልኩ እያደረሱ ያሉት ድንበር ዘለል ጥቃት በመቀጠሉ ሩሲያ በኩርስክ ግዛት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀች።

የክልልሉ አስተዳዳሪ አሌክሲ ስሚርኖቭ እርምጃው "በክልሉ ውስጥ የጠላት ኃይሎች የሚያስከትሉትን ጥፋት ለማስወገድ" አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የሩስያ ባለስልጣናት ወረራው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በትንሹ አምስት ንጹሀን ዜጎች መገደላቸውን እና 31 መቁሰላቸውን (ስድስቱ ህፃናት) አስታውቀዋል።

ዩክሬን በይፋ አስተያየት ያልሰጠች ሲሆን የወረራው ጥልቀትም ግልጽ አይደለም።

ማክሰኞ ማለዳ ላይ እስከ አንድ ሺህ የሚደርሱ የዩክሬን ወታደሮች፣ 11 ታንኮች እና ከ20 በላይ የታጠቁ የጦር መኪኖች በሱድዛ ከተማ አቅራቢያ ወደ ሩሲያ ግዛት መግባታቸውን ሞስኮ አስታውቃለች።

ውጊያው እስከ ማክሰኞ ድረስ በበርካታ መንደሮች ውስጥ መካሄዱ የተዘገበ ሲሆን የአካባቢው ባለስልጣናት ነዋሪዎች እንቅስቃሴያቸውን እንዲገድቡ ሲጠይቁ ሁሉም ህዝባዊ ዝግጅቶች ተሰርዘዋል።

በኩርስክ በርካታ የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያዎች ተሰጥተዋል። ቢቢሲ ያረጋገጣቸው እና በበይነ መረብ የተለጠፉት ምስሎች ተዋጊ ጄቶች በአካባቢው ዝቅ ብለው ሲበሩ ያሳዩ ሲሆን በአካባቢዎቹ መሬት ላይ ጭሱ እየጨመረ ነው።

በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከድንበር አከባቢዎች ተፈናቅለዋል። ሐኪሞች ከሌሎች ከተሞች እንዲገቡ እየተደረገ ነው ሲሉ ስሚርኖቭ ተናግረዋል።

ሩሲያ ዩክሬንን ከወረራች በሏላ ኪዬቭ ድንበር ተሻግራ ጥቃት ስትፈጽም ብዙም አልታየም።

ረቡዕ አመሻሽ ላይ የዩክሬን የፓርላማ አባል ኦሌክሲ ሆንቻሬንኮ እንደተናገሩት የዩክሬን ጦር የሱድዛ ጋዝ ማዕከልን መቆጣጠር ችሏል። ይህም በጦርነቱ ወቅት ጭምር ከሩሲያ ወደ ዩክሬን በሚተላለፈው የተፈጥሮ ጋዝ ዋና ማዕከል በመሆን የሚያገለግል ነው።

የሩስያ ጋዝ ወደ አውሮፓ ህብረት የሚገባበት ብቸኛው መንገድም ነው።

ጉዳዩ በቢቢሲ ያልተረጋገጠ ቢሆንም ሆንቻሬንኮ የሰጡት አስተያየት ወደ ሩሲያ ግዛት ስለመገባቱ በዩክሬን ባለስልጣን የተሰጠ የመጀመሪያው ማረጋገጫ ነው።

ሆንቻሬንኮ በፌስቡክ ላይ እንዳስታወቁት ከወረራው ጀርባ ያለው "እቅድ" ምን እንደሆነ ባያውቁም፤ "አውሮፓውያን እና አሜሪካውያን... ሩሲያ ልትጠቃ እንደምትችል እና እንደሚያስፈልጋት" ያሳያል ብለዋል።

ከቢቢሲ ኒውስሃወር ጋር ባደረጉት ቆይታ ደግሞ “ከወታደራዊ እይታ አንጻር የጦርነቱን ቦታ ለመቀየር እየሞከርን ነው" ሲሉ አክለዋል።

“ጥቃቱ ወደ ሩሲያ ድንበር ቢዘልቅ የፑቲን ምላሽ መፈራት እንደሌለበት ለዓለም እያሳየን ነው። ምንም ምላሽ የለም” ብለዋል።

"ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያለው የሩሲያ ግዛት ተይዟል። ፑቲን ፊቱን ወደ ኑክሌር ጦር አላዞረም።”

ወረራው ሩሲያ ወታደሮቿን ወደ ቀጣናው እንድታንቀሳቅስ እንደሚያስገድዳት እና በምስራቃዊ ዩክሬን የምታደርገውን ጥቃት እንደሚቀንስ ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።

የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ዩናይትድ ስቴትስ ስለ ጥቃቱ ቀደም ብላ እውቀት እንደሌላት እና "ስለ ዓላማቸው የበለጠ ለማወቅ" የዩክሬን ጦርን ለማነጋገር ማቀዷን ተናግረዋል።

‘ከባዱ' የሱድዛ ውጊያ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ረቡዕ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር በቴሌቭዥን ባካሄዱት ስብሰባ ዩክሬንን እርምጃ “ቀስቃሽ" ሲሉ"ያለ ልዩነት በሲቪል ህንጻዎች እና መኖሪያ ቤቶች ላይ የምታደርሰውን ጥቃት” ወቅሰዋል።

የሩስያ ጦር ኢታማዦር ሹም ቫለሪ ገራሲሞቭ በበኩላቸው ወደ ኩርስክ ክልል የሚደረገው "ግስጋሴ" ቆሟል፤ የሩሲያ ኃይሎች "ከሩሲያ-ዩክሬን ድንበር ጋር በቀጥታ በተያያዙ አካባቢዎች ጠላትን ማጥፋት ቀጥለዋል" ብለዋል።

ጌራሲሞቭ አክለውም የዩክሬን ጦር በሱድዛ ከተማ ዙሪያ ያለውን አካባቢ ለመቆጣጠር ቢያልምም ሩሲያ 100 ሰዎችን ገድላ ሌሎች 215 አቁስላለች ብለዋል።

ሆኖም አንዳንድ ታዋቂ እና ጥሩ መረጃ ያላቸው የጦርነቱ ደጋፊ የቴሌግራም ቻናሎች ክሬምሊን እንደገለጸው ሳይሆን በመሬት ላይ ያለው ሁኔታ የተረጋጋ እንዳልሆነ ጠቁመዋል።

ጦማሪው ዩሪ ኮቴኖክ በሱድዛ እና በአቅራቢያው በኮሬኔቮ የሚካሄዱትን ጦርነቶች “ከባድ” ሲል ገልጿል።

ሬይባር የተባለው ቻናል በበኩሉ በሱድዛ አካባቢ ያለው ሁኔታ “እየተባባሰ መሄዱን” እና የዩክሬን ጦር ወደ ከተማዋ እየገሰገሱ መሆኑን ገልጿል። ቢቢሲ እነዚህን ጉዳዮች ማረጋገጥ አልቻለም።

ከሱድዛ ሰሜናዊ ምስራቅ 70 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘውን የኩርስክ የኒውክሌር ሃይል ማመንጫ ጥበቃን አጠናክሮ መቀጠሉን የሩስያ ብሔራዊ ጥበቃ አስታውቋል።

የኩርስክ ጎረቤት የሆነችው የቤልጎሮድ ክልል ገዥ ቭያቼስላቭ ግላድኮቭ እስከ ማክሰኞ ድረስ የሚሳኤል ጥቃት ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን እና በዩክሬን የአየር ጥቃት ብዙ ሰዎች መቁሰላቸውን ተናግረዋል።

ረቡዕ ዕለት የዩክሬን የሱሚ ክልል መሪ ቮሎዲሚር አርቱክ ነዋሪዎች ከኩርስክ ጋር የሚዋሰኑ አካባቢዎችን ለቀው እንዲወጡ አዘዘ።

በዩክሬን ጦር ኮሎኔል የሆኑት ቭላዲላቭ ሴሌዝኒዮቭ ለታዋቂው ኔክስታ ቻናል ጥቃቱ “የመከላከያ ዘዴ” እንደሆነ ተናግረው በግምት ወደ 75 ሺህ የሚጠጉ የሩሲያ ወታደሮች ድንበሩ አቅራቢያ መሰባሰባቸውን ቀጥለዋል ብለዋል።

በግንቦት ወር ሩሲያ ወደ ሰሜናዊ ምስራቅ ካርኪቭ ክልል ትልቅ ድንበር ተሻጋሪ ወረራ ካደረገች በኋላ ሞስኮ ይህንን ሙከራ በሱሚ አቅጣጫ ታደርጋለች የሚል ስጋት ነበረ።

የዩክሬን ጦርን ቀድሞውንም ከመጠን በላይ በመለጠጡ አንዳንድ ወታደራዊ ተንታኞች እንደዚህ አይነት ድንበር ተሻጋሪ ወረራዎችን ስኬት ይጠራጠራሉ።

መቀመጫቸውን በዩክሬን ያደረጉ ተዋጊዎች ወደ ሩሲያ ሲገቡ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

አንዳንድ የፀረ-ክሬምሊን ሩሲያውያን ቡድኖች ባለፈው ዓመት ወረራ ቢጀምሩም ተመትተው ተመልሰዋል።

ኃይሎቹ በመጋቢት ወር እንደገና ወደ ቤልጎሮድ እና ኩርስክ ክልሎች ተሻግረው ከሩሲያ የጸጥታ ሃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ ገብተዋል።