የብሪታንያዊቷ ሙዚቀኛ ቦርሳ በጨረታ በ10.1 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠ

የበርኪን ቦርሳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የብሪታንዊቷ ሙዚቀኛ ጄን በርኪን የሌዘር ቦርሳ በፋሽን ኢንዱስትሪው ከፍተኛ በሚባል በ10.1 ሚሊዮን ዶላር ጨረታ ተሸጠ።

ይህ በዋጋ ክብረ ወሰን ያስመዘገበው ጥቁር ሌዘር ቦርሳ የተሰራው በአውሮፓውያኑ 1985 ነበር።

በአንድ በረራ ላይ ቅንጡ የፋሽን ምርቶችን የሚያመርተው ሄርመስ ኃላፊ ተቀምጣ የነበረችው ሙዚቀኛዋ ይዛው የነበረው የነበረው ቦርሳ አነስተኛ ስለነበር ዕቃዎቿን መከወን አልቻለችም ነበር።

ለምንን ትልልቅ ቦርሳዎችን እንደማይሰሩ? ጥያቄ ለኃላፊው መወርወሯን ተከትሎ ኃላፊው አዲስ የቦርሳ ዲዛይን ንድፍ ማውጣት ጀመሩ። አዲሱ ቦርሳ በውበቱም እንዲሁም በአጠቃቀሙም የበለጠ ተግባራዊ እንዲሆን ነበር የተሰራው።

የሔርመስ ኃላፊ መጀመሪያ ለሙከራ የሰሩት ቦርሳ በፓሪስ ሶትሄቢስ ሐሙስ ዕለት በወጣ ጨረታ ለጃፓኑ ሰብሳቢ በ513 ሺህ ዶላር ተሸጧል። ይህ ሽያጭ ከዚህ ቀደም ከነበሩ በከፍተኛ ደረጃ የላቀ ነው።

የሙዚቀኛዋን ቦርሳ ለጨረታ ያቀረበው ሶትሄቢስ ለአስር ደቂቃ ያህል በዘጠኝ ተጫራቾች መካከል የጋለ ፉክክር እንደነበር አስታውቋል።

የጨረታ ድርጅቱ ሶትሄቢስ የዓለም አቀፍ የፋሺን ኃላፊ ቦርሳው የተሸጠበት ዋጋ " ተጫራቾች ልዩ የሆነ ዕቃን ለራሳቸው እንዲያደርጉ በማነሳሳት የአፈ ታሪክን አስደናቂ ኃይል እንዲሁም አቅምን ያሳየ ነው" ብለዋል።

"የበርኪን ቦርሳ ይህንኑ ያሳየ ነው። በዓለማችን ላይ እጅጉን ተፈላጊ፣ የዘመናዊነት ተምሳሌት የሆነውን የበርኪን ቦርሳን የሰጠን መነሻ የሆነው አስደናቂ ታሪክን የሚወክል ነው "ብለዋል።

ጄን በርኪን በአሁኑ ወቅት በ10.1 ሚሊዮን ዶላር የተሸጠውን ቦርሳ ይዛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጄን በርኪን በአሁኑ ወቅት በ10.1 ሚሊዮን ዶላር የተሸጠውን ቦርሳ ይዛ

ቦርሳው የተሸጠበት 10.1 ሚሊዮን ዶላር አጠቃላይ ኮሚሽን እና ክፍያዎችን ያካተተተ ነው። ሶትሄቢስ የጨረታ ድርጅት ቦርሳው የሚሸጥበትን የቅድመ-ጨረታ ግምት ይፋ አላደረገም።

ሄርመስ ለእንግሊዛዊቷ-ፈረንሳይ ዘፋኝ ቦርሳውን ከሰራ በኋላ ሻንጣውን ለገበያ ያቀረበ ሲሆን በፋሽን ውስጥ ስመ ጥር ከሆኑ አንዱ ለመሆን በቅቷል።

የቦርሳው አንዳንድ ዲዛይኖች በአስር ሺዎች የሚቆጠር ዶላር የሚያስወጡ ሲሆን ለዓመታትም በኩባንያው የገዥዎች ዝርዝር ውስጥ ተካትተው ለዓመታትም መጠበቅ ይኖርብዎታል።

የዓለማችን ታዋቂዎች እንደ ኬት ሞስ፣ ቪክቶሪያ ቤካም እና ጄኔፈር ሎፔዝ ይህ ቦርሳ አላቸው።

የሙዚቀኛዋ ቦርሳ የበርኪን የስሟ ፊደልን ጨምሮ ትደግፋቸው የነበሩ አቋሟቿን የሚያሳዩ ተለጣፊዎች ያሉበት ነው።

በአውሮፓውያኑ 2023፣ በ76 ዓመቷ ህይወቷ ያለፈው ሙዚቀኛዋ ቦርሳውን ለአስር ዓመታት ከያዘችው በኋላ ለኤድስ የበጎ አድራጎት ድርጅት ገንዘብ ለማሰባሰብ በሚል በአውሮፓውያኑ 1994 ለጨረታ ለግሳለች።

በፓሪስ ቅንጡ ቡቲክ ያላት ካትሪን ቤኒየር ከገዛችው በኋላ ለ25 ዓመታት በባለቤትነት ካቆየችው በኋላ ሐሙስ ዕለት ለሽያጭ አቅርባዋለች።