"ተጫዋቾቼን የምጠይቀው ጎል እንዲያስቆጥሩ ብቻ ነው" - አርሰናል አጥቂ ማስፈረም ይኖርበታል?

የአርሰናሉ አጥቂ ጋብርኤል እየሱስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቅዳሜ አመሻሹን በሜዳው ኤሜሬትስ ኤቨርተንን ያስተናገደው አርሰናል ጎል ሳይስቆጥር፤ ሳይቆጠርበት ጨዋታው ተጠናቋል።

የጨዋታው መጠናቀቂያ ፊሽካ ሲነፋ ደጋፊዎች የጉርምርምታ ድምፃቸውን አሰምተዋል።

አርሰናል በቅዳሜው ጨዋታ ሁለት ነጥብ በመጣሉ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫ ፍልሚያ ትልቅ ዕድል እንዳመለጠው ደጋፊዎች የገባቸው ይመስላል።

የሊጉ ዋንጫ ወደ ከሁለት አስርታት በኋላ ወደ ሰሜን ለንደን ማምራት ካለበት አርሰናል እንዲህ ነጥብ መጣል የለበትም የሚሉ በርካቶች ናቸው።

አርሰናል ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመኖች ከማን ሲቲ ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ ቢያጠናቅቅም በዘንድሮው የደረጃ ሰንጠረዥ ግን እስካሁን ሊቨርፑልን ሊደርስበት አልቻለም።

የሊጉ መሪ ሊቨርፑል በመጀመሪያው አጋማሽ የግራ መስመሩ አንዲ ሮበርትሰን በቀይ ካርድ ቢሰናበትበትም በሜዳው ከፉልሀም ጋር ያደረገውን ጨዋታ 2-2 አጠናቋል።

ኤቨርተንን ያስተናገዱት መድፈኞቹ በኳስ ቁጥጥር 76 በመቶ የበላይነት አሳይተዋል። 13 ጊዜ ወደ ተቃራኒ ጎል ኳስ ሞክረዋል። ነገር ግን የኤቨርተንን ተከላካይ መስመር መስበር አልቻሉም።

"ይህንን ጨዋታ ባለማሸነፋችን በጣም ተበሳጭቻለሁ" ሲል አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ከግጥሚያው በኋላ አስተያየቱን ሰጥቷል።

"በሁሉም ረገድ የበላይነት ነበረን። ዕድሎችንም ፈጥረናል። ነገር ግን ማስቆጠር አልቻልንም። ተጫዋቾቼን የምጠይቀው ጎል እንዲያስቆጥሩ ብቻ ነው" ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሊጉ ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል በ16 ጨዋታዎች 30 ነጥቦች ሰብስቧል። ባጠቃላይ በፕሪሚዬር ሊጉ ካደረጋቸው ጨዋታዎች ግማሹን ማሸነፍ አልቻለም። ይህ ካለፉት ሁለት የውድድር ዘመኖች ጋር ሲነፃፀር ደካማ አቋም ነው።

ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት 36 ነጥቦች ይዘው ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው ነበር። ከዚያ ቀደም በነበረው የውድድር ዘመን ደግሞ 40 ነጥቦች ሰብስበው ሊጉን ሲመሩ እንደነበር ይታወሳል።

መድፈኞቹ እስካሁን ባደረጓቸው ጨዋታዎች 2 ጊዜ ብቻ ነው የተሸነፉት። ነገር ግን 6 ጊዜ አቻ ወጥተዋል። ይህ ደግሞ ዋጋ እያስከፈላቸው ይመስላል።

አርሰናል ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ አቻ ወጥቷል። ከጥር 2023 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሜዳው ጎል ሳይስቆጥር ወጥቷል።

ምናልባት አርሰናል ጨራሽ አጥቂ ያስፈልገው ይሆን?

የሰሜን ለንደኑ ክለብ በያዝነው የውድድር ዘመን 29 ጎሎች አስቆጥሯል። ባለፈው የውድድር ዘመን በተመሳሳይ ወቅት 11 ተጨማሪ ጎሎች አስጥሮ ነበር።

ከ29 ጎሎች ሁለቱ ፍፁም ቅጣት ምት ናቸው። 9 ጎሎች ከቆሙ ኳስ የተገኙ መሆናቸውን ቁጥሮች ያሳያሉ። በለተይ ከማዕዘን ምት ብዙ ጎሎች እያስቆጠሩ ነው።

እኒህ ቁጥሮች አርሰናል ጨራሽ አጥቂ እንደሚያስፈልገው ያሳያሉ። መድፈኞቹ በሚመጣው የጥር የዝውውር መስኮት አጥቂ ያስፈርሙ ይሆን?

የኒውካስሉ አሌክሳንደር ኢሳክ እና የጁቬንቱሱ ዱሳን ቭላሆቪች ከአርሰናል ጋር ተያይዞ ስማቸው እየተነሳ ነው።

የቀድሞው የመድፈኞቹ ተከላካይ ማርቲን ኬውን አርሰናል "ከምንም ተነስቶ ጎል መፍጠር የሚችል" አጥቂ ያስፈልገዋል ሲል ይከራከራል።

ካለፈው የውድድር ዘመን ጀምሮ ቡካዮ ሳካ እና ካይ ሀቨርትዝ አርሰናል ካስቆጠራቸው ጎሎች ግማሹን በስማቸው አስመዝግበዋል። ነገር ግን ቅዳሜ በነበረው ጨዋታ ካይ ሀቨርትዝ ያባከነው ኳስ ጀርመናዊው ተጫዋች ጨራሽ አጥቂ ላለመሆኑ ማሳያ ነው።

በሌሎች የቅዳሜ ምሽት ጨዋታዎች ሊቨርፑል አቻ ሲለያይ፤ ኒውካስል ሌስተርን 4-0፤ ኢፕስዊች ዎልቭስን 2-1፤ ኖቲንግሀም ቢላን 2-1 ረትተዋል።