ትራምፕ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ለሚፈጸሙ ግድያዎች የሞት ቅጣት እንዲፈረድ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ሰው በመግደል የሚከሰሱ ግለሰቦች የሞት ቅጣት እንዲወሰንባቸው ለመጠየቅ ማቀዳቸውን ተናገሩ።
ትራምፕ በዋይት ሐውስ በተካሄደ የካቢኔ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የሞት ቅጣት ይህንን ዓይነቱን ወንጀል "የሚያስቀር" እርምጃ ይሆናል ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ፤ በከተማዋ አሉ ያሉትን "ሙሉ እና አጠቃላይ ሕግ አልባነት" ለመዋጋት በመቶዎች የሚቆጠሩ የብሔራዊ ዘብ እና የፌዴራል ሕግ አስከባሪ መኮንኖች በአሜሪካ ዋና ከተማ አሰማርተዋል።
እርምጃው በቺካጎ እና በሌሎች ከተሞች ሊደገም እንደሚችልም ጠቁመዋል፥።
የዋሽንግተን ከንቲባ ሙሪየል ቦውሰር፤ ከ2023 ወዲህ በከተማዋ የሚፈጸመው የወንጀል መጠን መቀነሱን በመጥቀስ ፕሬዝዳንቱ ስለሚፈጸመው ወንጀል ያቀረቡትን ክስ ውድቅ አድርገዋል።
ትራምፕ፤ "አንድ ሰው በዋና ከተማዋ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ አንድን ሰው ቢገድል የሞት ቅጣት እንጠይቃለን" ሲሉ ለጋዜጠኞች እና ለካቢኔ አባላት ተናግረዋል። "ይህ በጣም ጠንካራ የመከላከያ [እርምጃ] ነው" በማለትም አክለዋል።
በአሰራር ደረጃ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ለሚፈጸሙ ነገር ግን በፌዴራል ሕጎች ስር ለሚወድቁ ወንጀሎች ዐቃቢያነ ሕግ የሞት ቅጣት መጠየቅ የሚችሉ ቢሆንም አብዛኛዎቹ ግድያዎች የሚዳኙት በከተማዋ ሕግ ነው።
ይህም ቢሆን ግን የሞት ቅጣት ሊፈጸም የሚችለው ከነዋሪዎች የተወጣጡ እና በፍርድ ቤት የሚቀርበውን ክርክር ተመልክተው ውሳኔ በሚያሳልፉ ግለሰቦችን የያዘው "ጁሪ" የተሰኘ ቡድን አባላት ሲስማሙበት ብቻ ነው።
በዚህም ምክንያት አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች የሞት ቅጣትን የሚቃወሙ በሆኑበት ከተማ ይህንን ፍርድ ማሰጠት ቀላል አይሆንም።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ለውጥ እንዴት ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚፈልጉ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።
ትራምፕ ጥር ላይ ወደ ስልጣን በተመለሱበት የመጀመሪያው ቀን በፈረሙት ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ የፌደራል የሞት ቅጣት በድጋሚ ተግባራዊ እንዲሆን የሚያስችል ውሳኔ አሳልፈዋል።
በቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ጊዜ የአገሪቱ ፍትህ ሚኒስቴር በፌዴራል የሞት ቅጣት አተገባበር ላይ ጊዜያዊ እገዳ ጥሎ ነበር።
ትራምፕ ጥር ላይ የፈረሙት የፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ፤ የሞት ቅጣትን "በአሜሪካ ዜጎች ላይ እጅግ አሰቃቂ ወንጀሎችን እና ገዳይ የኃይል ድርጊቶችን የሚፈፅሙት ሰዎችን ለማስቀረት እና ለመቅጣት አስፈላጊ መሳሪያ ነው" በማለት ይገልጸዋል።
"አሜሪካ ከመመስረቷ በፊት፣ በምስረታዋ ወቅት እና በኋላ ከተሞቻችን፣ ግዛቶቻችን እና አገራችን የሞት ቅጣትን እንደ የመጨረሻው መከላከያ እና ለከፋ ወንጀሎች ብቸኛው ተገቢ ቅጣት አድርገው ያለማቋረጥ ተጠቅመዋል" ሲልም አክሏል።
አሜሪካ ውስጥ አብዛኛዎቹ የሞት ቅጣቶች የሚፈፀሙት በግዛቶች ደረጃ ነው። 27 ግዛቶች፣ የአገሪቱ ሠራዊት እና የፌዴራል መንግሥት አሁንም የሞት ቅጣትን እንደ ሕጋዊ አማራጭ አድርገው ይቆጥሩታል።
በ1972 የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዋሽንግተን ዲሲ የሞት ቅጣት ሕግ ተፈጻሚ እንዳይሆን የወሰነ ሲሆን በ1981 ደግሞ በከተማዋ ምክር ቤት ሽሮታል።
ከአስርተ ዓመታት በኋላ በ2002 በሪፐብሊካኖች ቁጥጥር ሥር በነበረው የአሜሪካ ኮንግረስ በጉዳዩ ላይ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ባደርገበት ወቅት የከተማዋ ነዋሪዎች የሞት ቅጣትን በመቃወም በከፍተኛ መጠን ድምፅ ሰጥተዋል።
ትራምፕ ወደ ስልጣን ከተመለሱ ወዲህ ምንም የፌዴራል የሞት ቅጣት አልተፈጸመም።
ይሁን እንጂ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ወቅት በ2020 መጨረሻ እና በጥር 2021 በተከታታይ 13 የሞት ቅጣቶች እንዲፈጸሙ ተደርጎ ነበር።
ይህ እርምጃ ትራምፕ በአንድ ክፍለ ዘመን ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፌደራል ሞት ቅጣት ተፈጻሚ እንዲሆን ያደረጉ ፕሬዝዳንት አድርጓቸዋል።
ፕሬዝዳንታዊ ሽግግር በሚደረግበት ጊዜ የሞት ቅጣቶች እንዲቆሙ ሲደረግ የነበረውን ለ130 ዓመታት የዘለቀ ልማድንም አቋርጠውታል።
የመጨረሻው የሞት ቅጣት የተፈጸመው ጥር 2021 ሥልጣናቸውን ከማስረከባቸው አምስት ቀናት በፊት ነበር።
ፕሬዝዳንቱ ስለ ሞት ቅጣት አስተያየት የሰጡት 800 እንደሚሆኑ የተገመቱ የብሔራዊ ዘብ ወታደሮች እና በመቶዎች የሚቆጠሩ የፌዴራል መኮንኖች ወንጀል እና ቤት አልባነት ላይ ለመዝመት ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በተሰማሩበት በዚህ ወቅት ነው።
ከንቲባ ሙሪየል ቦውሰርን ጨምሮ የከተማዋ ባለሥልጣናት ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ የፌዴራል ጣልቃ ገብነት አስፈላጊነት ላይ ጥያቄ አንስተዋል።
ከንቲባዋ "የወንጀል በከፍተኛ መጠን ላይ መቀነሱን" እንዲሁም "በ30 ዓመታት ውስጥ አመጻን የቀላቀለ ወንጀል መጠን ዝቅተኛ" ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።















