ትራምፕ ወንጀለኞችን "ለማጽዳት" በባልቲሞር ወታደሮችን ለማሰማራት ዛቱ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዲሞክራቶች በከተማዋ "የደህንነት ጉዞ" ሲሉ በጠሩት ጉዞ ላይ እንዲገኙ ከጋበዟቸው በኋላ ከሜሪላንድ ገዢው ዌስ ሞር ጋር ያላቸው አለመግባባት ተካርሮ ወታደሮቻቸውን ወደ ባልቲሞር እንደሚያሰማሩ ዛቱ።
ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ "ዌስ ሞር፣ ልክ ጋቪን ኒውስከም በኤልኤ እንዳደረገው እርዳታ የሚያስፈልገው ከሆነ በአቅራቢያው በዲሲ ውስጥ እንደሆነው 'ወታደሮችን' በመላክ ወንጀልን በፍጥነት አጸዳለሁ" ሲሉ ጽፈዋል።
ፕሬዚዳንቱ ይህንን አስተያየት የሰጡት ወንጀልን ለማጥፋት በሚል የብሔራዊ ጥበቃ ዘብ ወታደሮችን በዲሞክራቶች በሚመሩ ከተሞች ለማሰማራት ጥረት እያደረጉ ባለበት ወቅት ነው።
ወታደሮችን ለአገር ውስጥ ሕግ ማስከበር መጠቀማቸው ከዲሞክራቶች ከፍተኛ ተቃውሞ አስከትሏል።
አንድ ፖለቲከኛ ድርጊቱን "ሥልጣን አላግባብ መጠቀም" ሲሉ ገልጸውታል።
በሚቀጥሉት ሳምንታት 1,700 ወታደሮች በ19 ግዛቶች ይሰማራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የፕሬዚዳንቱን እርምጃዎች በተደጋጋሚ በመተቸት የሚታወቁት ሙር፣ ትራምፕ ወንጀልን ስለመዋጋት የሰጡት አስተያየት "አላዋቂ እና ደንታቢስ መሆናቸውን ያሳየ ነው" ብለዋል።
ሙር አክለውም "በመንገዳችን ስላልሄዱ ነው" ካሉ በኋላ "በእኛ ማኅበረሰቦች ውስጥ አልነበሩም፣ እና እኛ እነዚህን ተደጋጋሚ ውንጀላዎች በማቅረባቸው በጣም ደስተኞች ናቸው።"
ትራምፕ እሁድ ዕለት በትሩዝ የማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ሙር የላኩላቸውን የግብዣ ደብዳቤ በሚመለከት በሰጡት ቀጥተኛ ምላሽ "አስቀያሚ" እና "ቀስቃሽ" ብለውታል።
ትራምፕ "እንደ ፕሬዝዳንትነቴ፣ ወደዚያ ለእግር ጉዞ ከመሄዴ በፊት ይህንን የወንጀል ቀውስ ቢያጸዳው እመርጣለሁ" ሲሉ ጽፈዋል።
ትራምፕ ቀደም ሲል ወደ 2,000 የሚጠጉ ወታደሮችን በዋሽንግተን ዲሲ አሰማርተዋል።
ይህ ዘመቻ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መታሰራቸውን ዋይት ሐውስ ገልጿል።
ትራምፕ አርብ ዕለት በዋይት ሐውስ ኦቫል ኦፊስ ንግግር ሲያደርጉ ተልዕኮው ዋሽንግተን ውስጥ አጠቃላይ ደህንነትን አምጥቷል ብለዋል።
"ዲሲ ገሃነም ነበረች" ያሉት ትራምፕ፤ "አሁን ግን ደህንነቷ የተጠበቀ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።
አርብ ዕለት ፔንታጎን ከዚህ ቀደም በዩናይትድ ስቴትስ ዋና ከተማ መሳሪያ ሳይታጠቁ የተሰማሩ ወታደሮች የጦር መሳሪያ መያዝ ይጀምራሉ ብሏል።
ወደ ዋሽንግተን ዲሲ የተላኩት ወታደሮች እስካሁን ድረስ በሕግ ማስከበር ስራዎች ላይ አልተሳተፉም። ይልቁንም በአንዳንድ ሕዝበ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ተመድበዋል።
በዋሽንግተን ዲሲ ሜትሮፖሊታን ፖሊስ ይፋ የሆኑ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በከተማዋ በ2023 ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረ አመጽ የተቀላቀለበት ወንጀል በ2024 በ30 ዓመታት ውስጥ ዝቅተኛው ነው በተባለ ሁኔታ ቀንሷል።
እስካሁን ያለው የ2025 ሪፖርት እንደሚያሳየው በከተማዋ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ቁጥር እየቀነሱ ነው።
በ2024 ከተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር በዚህ ዓመት ጥቃት የሚፈጸምባቸው ወንጀሎች በ26 በመቶ እንዲሁም ዝርፊያ በ28 በመቶ ቀንሰዋል።
ትራምፕ በኒውዮርክ እና ቺካጎ ወታደሮችን እንደሚያሰማሩ ተናግረዋል።















