በዓለም ላይ እጅግ ሀብታም በሆነችው አሜሪካ ቤት የሌላቸው ሰዎች ቁጥር ለምን ጨመረ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዋሺንግተን ዲሲ የሚታዩ ወንጀሎችን ለመከላከል ቃል ገብተው በከተማዋ የሚገኙ ቤት የሌላቸው ሰዎች "በአስቸኳይ ለቅቀው መውጣት አለባቸው" ብለዋል።
ብሔራዊ ዘብን በከተማዋ ከማሰማራታቸው እና የከተማዋን ፖሊስ በስሩ እንዲሆን ከማድረጋቸው በፊት አንድ ቀን ቀደም ብሎ "የሚቆዩበት ቦታ እንሰጣቸዋለን፤ ነገር ግን ከዋና ከተማው የራቀ ስፍራ ነው። ወንጀለኞች የትም መሄድ የለባቸውም።ወደ ሚገባቸው ቦታ፣እስር ቤት እናስገባቸዋለን" ሲሉ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ገጻቸው ላይ ለጥፈዋል።
የፕሬዚዳንቱ ዕቅድ ኤፍቢአይ በምሽት ቅኝት እንዲያደርግ ያስቀመጠ ሲሆን፣ ከተማዋን "ሕግ አልባ" ሲሉ ከገለፁት የመኖሪያ ቤት እጦት እና ወንጀል "ነጻ ማውጣት" እንዲሁም "ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አስተማማኝ እና ውብ" ለማድረግ አልሟል።
የከተማዋ ከንቲባ የሆኑት ሙሪየል ቦውሰር የፕሬዚዳንቱን ውሳኔ ተከትሎ በከተማዋ የወንጀል መጠን እየቀነሰ መሄዱን ተናግረው "ያልተቀናጀ እና አስፈላጊ ያልሆነ" ሲሉ ገልጸውታል።
የዋሽንግተን ዲሲ ፖሊስ ቢሮ ባወጣው መረጃ መሠረት እአአ በ2023 በከተማዋ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሶ የነበረው አመጽ የተቀላቀለበት ወንጀል፣ በ2024 የቀነሰ ሲሆን ይህም በ2025 ይቀጥላል ተብሎ ተገምቷል።
ትራምፕ ሰኞ ዕለት ይፋ ያደረጉት ይህ እርምጃ በሐምሌ ወር የፈረሙትን ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዝ ተከትሎ የመጣ ነው።
ይህም በጎዳና ላይ የሚኖሩትን በቁጥጥር ስር ለማዋል ቀላል የሚያደርግ ሲሆን፣ እንደ አንዳንድ የመብት ተሟጋቾች ገለጻ ከሆነ ስለ ጉዳዩ "ጥልቀት የሌለው እና የተዛባ" ምስልን ይፈጥራል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በከተማዋ ያለው ቤት አልባነት እና ወንጀል ልክ እንደ ሎስ አንጀለስ ካውንቲ ሁሉ ከተወሰኑ ጊዜያቶች በስተቀር በየዓመቱ እየተባባሰ እና ቁጥሩ እየጨመረ የሚሄድ ችግር ነው ።
እአአ በ 2024 በከተማዋ ቤት የሌላቸው ሰዎች ቁጥር ከ 770,000 በላይ ከፍ ያለ ሲሆን፣ ይህም በአግባቡ ሰነድ መያዝ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሲሰላ ከፍተኛው ቁጥር መሆኑን የፌደራል መንግሥቱ መረጃ ያሳያል።
በሌላ መንገድ ለማስቀመጥ በታህሳስ ወር መጨረሻ ላይ ከ10,000 ሰዎች ውስጥ 23ቱ ቤት አልባ ነበሩ።
በየጊዜው እየተቃለለ ከመሄድ ይልቅ እየጨመረ ለሄደው ለዚህ ውስብስብ ችግር ዋናው ምክንያት ምንድን ነው?
በዓለም ባንክ መረጃ መሠረት አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) ወደ 30 ትሪሊዮን ዶላር በሚጠጋባት ሀብታም አገር ውስጥ ለምን መፍትሄ አልተገኘም?
አሁን በትራምፕ አስተዳደር እየተወሰደ ካለው እርምጃ ምን ውጤት ይጠበቃል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቁጥሮች ምን ይነግሩናል?
እንደ አውሮፓውያን ኦቆጣጠር ከ 2007 ጀምሮ ለፕሬዚዳንቱ በቀጥታ ሪፖርት የሚያቀርበው የፌደራል መስሪያ ቤት የቤቶች እና የከተማ ልማት ቢሮ፣ ቤት አልባ የሆኑ ሰዎችን ቆጠራ አካሂዷል።
ቢሮው በዓመት ለአንድ ሌሊት ቆጠራ የሚያካሂድ ሲሆን በጥር ወር 2024 ባደረገው ቆጠራ 771,480 መኖሪያ ቤት የሌላቸውን ሰዎች መዝግቧል።
ይህም ከ2023 ጋር ሲነጻጸር የ18 በመቶ ጭማሪ መኖሩን ያሳያል። ከ2022 ጋር ደግሞ ሲወዳደር የ12 በመቶ ጭማሪን አሳይቷል።
ይህ በታህሳስ ወር በታተመው የኤጀንሲው ዓመታዊ ሪፖርት ላይ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ጭማሪው የታየው በሁሉም የነዋሪዎች ቡድን መካከል መሆኑን እና ልጅ ባላቸው ቤተሰቦች ዘንድ 40 በመቶ ጭማሪ መመዝገቡ ጠቅሷል።
ቆጠራው በተደረገበት ምሽት ወደ 150,000 የሚጠጉ ሕጻናት ቤት አልባ መሆናቸው ተመዝግቧል።
በጎዳና ተዳዳሪዎቹ ዘንድ መቀነስ የታየው በቀድሞ ወታደሮች ዘንድ ብቻ ነው።
ስለዚህ እአአ በ2024 ቤት የሌላቸው የቀድሞ ወታደሮች ቁጥር በ 8 በመቶ ቀንሶ 32,882 ደርሷል።
ይህ ቁጥር ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ በሚቆዩት ዘንድም ቀንሶ የታየ ሲሆን 11 በመቶ ወይም 13,851 ብቻ በእነዚህ መጠለያዎች ውስጥ አንደሚገኙ ተመዝግበዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሪፖርቱ በዋነኛነት ከፍተኛ ቁጥር ላለው ብሔራዊ የቤት ቀውስ ተጠያቂ ያደረገው በፌደራል መንግሥቱ ተቀምጠው የነበሩት ከቤት የማስወጣት እገዳዎች እና የኪራይ ዕርዳታ ፕሮግራሞች ማብቃታቸውን ነው።
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ጥገኝነት ጠያቂዎች እና መጠለያ ፈላጊዎች ወደ አሜሪካ ከተሞች በመምጣታቸውም የተፈጠረ የስነ ሕዝብ ጫና መሆኑንም አመልክቷል።
ቢቢሲ ሙንዶ በ2024 መጀመሪያ ላይ በሎስ አንጀለስ መሀል ከተማ ውስጥ የመኖሪያ ቤት የሌላቸው ሰዎች በሚበዙበት ስኪድ ሮው አካባቢ ባደረገው ጉብኝት፣ ከቬንዙዌላ፣ ኢኳዶር እና ሌሎች የላቲን አሜሪካ አገራት የመጡ ቤተሰቦች መደበኛውን ቤት አልባ ሕዝብ መቀላቀላቸውን አረጋግጧል።
የ40 ዓመቷ ቬንዙዋላዊ ዶሪስ ከልጇ እና ከልጅ ልጇ ጋር በምትኖርበት የጎዳና ላይ ድንኳን እዚህ አካባቢ ለ10 ቀናት እንደቆየች ተናግራለች።
"መጀመሪያ በመጠለያ ውስጥ እንቆያለን ብለን እናስብ ነበር። ከዚያ እዚህም እዚያም ተሯሩጠን ስራዎች ሰርተን ተረጋግተን የቤት ኪራይ ልንከፍል እንችላለን ብለን ገምተን ነበር። ግን በሚያሳዝን ሁኔታ ስደተኛ ሲሆኑ እና የስራ ፍቃድ ከሌለ ቀላል አይደለም" ስትል አብራርታለች።
በትራምፕ አስተዳደር ፀረ ስደተኛ ፖሊሲዎች እና በሜክሲኮ ድንበር አካባቢ ያለው ቁጥጥር ማጠናከሩን ተከትሎ የስደተኞች ቁጥር ባለበት ቢቆምም የጎዳና ላይ ነዋሪዎች በጅምላ ከአገር እንዲወጡ በሚወሰደው እርምጃ ቀጥተኛ ተጠቂ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መዋቅራዊ ምክንያቶች
ነገር ግን ከቁጥሮቹ ባሻገር፣ ከእነዚህ ማኅበረሰቦች ጋር የሚሰሩ ድርጅቶች የቤት እጦት ቀውስ ውስብስብ፣ ረጅም ጊዜ የቆየ፣መዋቅራዊ እና ዘርፈ ብዙ መሆኑን አጽንኦት ይሰጡታል።
ናሽናል አሊያንስ ቱ ኢንድ ሆምለስነስ የተሰኘ ድርጅት ተመጣጣኝ የመኖሪያ ቤት እጥረት፣ በገቢ እና በኪራይ ወጪዎች መካከል ያለው ክፍተት መስፋፋት፣ የጤና አጠባበቅ እና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶች ተደራሽነት ውሱን መሆን፣ ዘረኝነት እና ስርአታዊ መገለል ለቤት እጦት ምክንያቶች መሆናቸውን ይጠቁማል።
እአአ ከ1987 ጀምሮ የሕዝብ መኖሪያ ቤት ፖሊሲዎች ላይ መረጃዎችን እና ጥናቶችን ሲያቀርብ የቆየው ይህ ድርጅት "ረዥም ጊዜ የቆዩ እና አሁንም ያሉ አድሎአዊ ፖሊሲዎች ማን ሀብትና ዕድሎች እንደሚያገኝ እየወሰኑ ነው" ብሏል።
"የመኖሪያ ቤት የማግኘት ችግርን መረዳት እነዚህ እርስ በርስ የተያያዙ አድሏዊ ሥርዓቶች እንዴት ኅብረተሰቡን ቤት ለማግኘት አስፈላጊ የሆኑ ሀብቶችን እና እድሎች በመከልከል እንደሚሰሩ እውቅና መስጠትን ይጠይቃል" ሲል አጠቃሏል።
ድርጅቱ ባጠናቀረው መረጃ መሠረት ባለፉት አስርት ዓመታት በአገሪቱ ከገቢያቸው ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ለኪራይ የሚያወጡ ቤተሰቦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አንድ ቤተሰብ ከገቢው ከ30 በመቶ በታች የሚሆነውን ከመኖሪያ ቤት ጋር በተያያዙ ወጪዎች ላይ የሚያውል ከሆነ የመኖሪያ ቤት በተመጣጣኝ ዋጋ ነው ሲል ያስባል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ያንን መቶኛ እንደ ማጣቀሻ በመጠቀም ናሽናል ሎው ኢንካም ሀውሲንግ ኮአሊሽን (NLIHC) የተባለ መያድ ድርጅት በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ አነስተኛ ደሞዝ የሚያገኝ ሠራተኛ ባለ አንድ መኝታ ቤት "በተመጣጣኝ" ዋጋ ለመከራየት በሳምንት 104 ሰዓት መሥራት አለበት ሲል ይደመድማል።
እአአ በ1974 የተመሰረተው እና ዋና መስሪያ ቤቱን በዋሽንግተን ያደረገው ድርጅቱ በተጨማሪም እጅግ በጣም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ተከራዮች የሚሆኑ 7.1 ሚሊዮን ተመጣጣኝ የኪራይ ቤቶች እጥረት እንዳለ አስታውቋል።
ይህም ማለት ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው 100 አባወራዎች 35 ቤቶች ብቻ ዝግጁ ናቸው ማለት ነው።
በካሊፎርኒያ ሳን ፍራንሲስኮ የቤኒኦፍ ሆምለስነስ ኤንድ ሀውሲንግ ኢኒሼቲቭ ዳይሬክተር ማርጎት ኩሼል "አሁን ያለው ቀውስ መነሻው ከፍተኛ የሆነ የመኖሪያ ቤት እጥረት ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ሙንዶ ተናግረዋል።
ነገር ግን የሕክምና ፕሮፌሰር የሆኑት ኩሼል ለቤት እጦት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሌሎች ምክንያቶችንም ዘርዝረዋል።
"ዜጎች የማኅበራዊ እና የጤና አጠባበቅ አገልግሎቶችን መጠቀም ወይም ማግኘት በማይችሉበት ጊዜ ይህ ጤናቸውን ብቻ ሳይሆን ገንዘባቸውም ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል" ብለዋል።
አሜሪካ ሁሉን አቀፍ የሕዝብ የጤና ስርዓት የላትም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጤና ላይ አተኩሮ የሚሰራው ኬኤፍኤፍ የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በ2024 ያወጣው የዳሰሳ ጥናት ሪፖርት እንደሚያሳየው ከሆነ ከአራት ጎልማሶች ውስጥ ሦስቱ ያልተጠበቁ የሕክምና ወጪዎችን እንዲሁም ለራሳቸው እና ለቤተሰባቸው የጤና እንክብካቤ ወጪን መሸፈን አልችልም ሲሉ ይሰጋሉ።
የግል የጤና መድህን ከሌላቸው ጎልማሶች መካከል 61 በመቶው በወጪ ምክንያት አገልግሎቱን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፋቸውን ጥናቱ ያረጋገጠ ሲሆን፣ 21 በመቶ የሚሆኑ ኢንሹራንስ ካላቸው መካከል ደግሞ ፖሊሲያቸው ሙሉ በሙሉ ስለማይሸፍን እና ለመክፈል አቅም ስለሌላቸው የሚያስፈልጋቸውን የሕክምና አገልግሎት እያገኙ እንዳልሆነ ጥናቱ አረጋግጧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኩሽል የሚመሩት የምርምር ቡድን ቤት የሌላቸውን አረጋውያንን ለበርካታ ዓመታት ሲያጠና የቆየ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ እድሜያቸው ከ50 በላይ በሆናቸው ወቅት ቤት አልባ እንደሆኑ ይናገራሉ።
በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የፕሬዚዳንት ትራምፕ ትዕዛዝ እና በጉዳዩ ላይ የሰጡት መግለጫ ጉዳዩን "ከልክ በላይ አቅልሎ እና አዛብቶ" ማቅረቡን ባለሙያው ይጠቁማሉ።
"ከልክ በላይ ቀልሎ የቀረበው ጉዳይ"
እአአ ሐምሌ 24 የተላለፈው የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ "የተለመደ ማፈናቀል፣ ስርዓት አልበኝነት፣ ድንገተኛ ግጭቶች እና የኃይል ጥቃቶች" የአሜሪካ ከተሞችን "የበለጠ ደህንነታቸው ያልተጠበቀ" አድርጓቸዋል ይላል።
የመኖሪያ ቤት እጦት ቁጥር መጨመሩን በመጥቀስ፣ "ከእነዚህ ግለሰቦች እጅግ የሚበልጡት አብዛኞቹ የዕፅ ሱሰኞች ወይም የአእምሮ ጤና ችግር ያለባቸው ወይም ሁለቱም (...) ናቸው" ሲል አክሏል።
እናም ከዚህ ቀደም የነበሩት የፌደራል እና የክልል መንግሥታት "ውጤታማ ባልሆኑ ፕሮግራሞች ላይ በአስር ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ቢያወጡም ችግሩን መፍታት ባለመቻላቸው ሌሎች ዜጎችን ለሕዝብ ደኅንነት አስጊ ለሆኑ አደጋዎች አጋልጠዋል" ሲል ይደመድማል።
ከዚህ በመነሳት የክልል እና የአካባቢ መንግሥታት በጎዳና ላይ እና በመጠለያ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን ወደ ሕክምና ማዕከላት እንዲሄዱ ለማድረግ ያላቸውን አቅም የሚገድቡ የፍርድ ቤት ቅድመ ሁኔታዎችን እና "ስምምነቶች" የሚባሉትን ለመቀልበስ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስዱ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ፓም ቦንዲን አዝዘዋል።
ፕሬዚዳንቱ በዚሁ ውሳኔያቸው ላይ ሌሎች ላይ አደጋ ይጥላሉ ተብለው የሚታሰቡ የአእምሮ ታማሚዎች ወይም ቤት የሌላቸው እና ራሳቸውን መንከባከብ ለማይችሉ ግለሰቦች ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ ለጠቅላይ አቃቤ ሕግ መመሪያ ሰጥተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትዕዛዙ "ቤት የሌላቸውን ሰዎች ወደ ረጅም ጊዜ ወደሚቆዩበት ተቋማት ማዘዋወሩ . . .ሕዝባዊ ሰላምን ወደነበረበት ይመልሳል" ብሏል።
የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ በተጨማሪም የፍትህ፣ የጤና እና የሰብአዊ አገልግሎት፣ የመኖሪያ ቤት እና የትራንስፖርት ቢሮዎች የፌዴራል እርዳታዎችን "በግልጽ ሕገ ወጥ የአደንዛዥ ዕፅ አጠቃቀምን፣ ከተማ ውስጥ ድንኳን ጥለው መቀመጥን እና ማቆሸሽን" ለሚከላከሉ ክልሎች እና ከተሞች ቅድሚያ እንዲሰጡ ያዝዛል።
እንዲሁም ቤት በሌላቸው እና በአእምሮ ጤና እና አካል ጉዳተኞች ላይ ሰፊ መረጃ እንዲሰበስብ ያዛል።
የአሜሪካ ሲቪል ነጻነቶች ህብረት (ACLU) ይህ ክትትል ማድረግን፣ ግላዊ መረጃን መውሰድ እና ". . .የበለጠ ወንጀለኛ ተብሎ ለመፈረጅ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል" ሲል ያለውን ስጋት በመግለጫው ላይ ገልጿል።
ኩሽል በበኩላቸው "ቤት አልባ በመሆናቸው ወይም በአእምሮ ጤና ወይም በአደገኛ ዕፅ ሱሰኝነት የሚሰቃዩ ሰዎችን መወንጀል ደህንነቱ የተጠበቀ ማኅበረሰብን አይፈጥርም፤ ሁሉንም ሰው ደህንነታቸው እንዳይሰማው ያደርጋል። እና የቤት እጦትን ችግር ለመፍታት ምንም የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የለም" ሲሉ ተናግረዋል።















