የትራምፕ እርምጃ እንዲታወስ ያደረገው አሜሪካ ድሆች እና አካል ጉዳተኞችን ትቀጣበት የነበረው ሕግ

አካል ጉዳተኞችን የሚያገልለው ሕግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአካላዊ ውበት መመዘኛ አስቀምጠው፣ ከመስፈርቱ በታች የሆኑ ሰዎችን የሚያገል የሕግ ማዕቀፍ ተግብረዋል

"መልካም ከመሆን ቆንጆ መሆን ይሻላል" - አየርላንዳዊው ደራሲ እና ገጣሚ ኦስካር ዋይልድ ይህንን የተናገረው አሜሪካንን እያሰበ ይመስላል።

በ19ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ የአሜሪካ አንድ ግዛት እና ብዙ ከተሞች የአካላዊ ውበት መመዘኛ አስቀምጠው፣ ከመስፈርቱ በታች የሆኑ ሰዎችን የሚያገልል የሕግ ማዕቀፍ ተግብረዋል።

በወቅቱ የነበረውን የሥነ ውበት መመዘኛ አላሟሉም የተባሉ ሰዎችም በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ተካተዋል።

እነዚህ ሰዎች የገንዘብ ቅጣት እና እስራት ይፈረድባቸው ነበር። በእንግሊዝኛው "Ugly laws" የተባለው ሕግ በግርድፉ "የአስቀያሚዎች ሕግ" ተብሎ ይተረጎማል።

አወዛጋቢ ሕግ ነበር።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዋሺንግተን ዲሲ የሚገኙ ቤት አልባ ሰዎች ከከተማዋ "መውጣት አለባቸው" ማለታቸው ከዓመታት በፊት ተተግብሮ የነበረውን ሕግ እንዲታወስ እያደረገ ነው።

ምንም እንኳን የቀደመው ሕግ ገጽታ እና ውበትን መሠረት ያደረገ ቢሆንም፣ አንዳንዶች የአሁኑ መጠለያ አልባ ድሆችን ከከተማዋ የማስወጣት ውሳኔ ከዚያ ጋር የሚስተካከል ነው በማለት ይተቻሉ።

ትራምፕ በከተማዋ የሚታዩ ወንጀሎችን ለመከላከል ቃል ገብተው ነው ጎዳና ላይ የሚኖሩ ሰዎች እንዲወጡ ያሉት።

ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ "የምትቆዩበት ቦታ እንሰጣችኋለን፤ ነገር ግን ከዋና ከተማው የራቀ ነው" ብለዋል።

ዋና ከተማቸው ዋሺንግተን ዲሲን "ከዚህ በፊት ከነበረችው የበለጠ አስተማማኝ እና የበለጠ ውብ" ለማድረግ ማቀዳቸውንም ተናግረዋል።

ትራምፕ ባለፈው ወር ቤት አልባ ሰዎችን በቀላሉ በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚያስችል ትዕዛዝ የፈረሙ ሲሆን፤ ባለፈው ሳምንት የፌደራል ሕግ አስከባሪ አካላት በዋሽንግተን ዲሲ ጎዳናዎች እንዲሰማሩ አዝዘዋል።

ትራምፕ በዋሽንግተን ያለውን ወንጀል እና ጎዳና ተዳዳሪነትን ለማስወገድ የአገሪቱን ብሔራዊ ዘብን ጨምሮ ሌሎችንም የደኅንነት ተቋማትን እንደሚጠቀሙ አስታውቀዋል።

የጎዳና ላይ ተዳዳሪዎች መጠለያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ በዋሽንግተን የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለማስወገድ የፀጥታ ኃይሎች እንዲሰማሩ አዝዘዋል

'አስቀያሚዎች ይደበቁ'

በዩኒቨርስቲ ኦፍ በርክሌይ የአርትስ ኤንድ ሂውማኒቲስ ዲን የሆኑት ሱዛን ሻዊክ እንደሚሉት፣ አንዳች ዓይነት አካላዊ መዋቅር ያላቸው ሰዎች በሕዝብ አደባባይ እንዳይታዩ ሕጉ ያግዳል።

በጉዳዩ ላይ 'The Ugly Laws: Disability in Public' የተሰኘ መጽሐፍ ያሳተሙት ሱዛን እንደገለጹት፣ ሕጉ መጀመሪያ የፀደቀው በአውሮፓውያኑ 1867 በሳን ፍራንሲስኮ ነው።

የታመሙ፣ አካላቸው የጎደለ ወይም ሰውነታቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን የሚቀጣ ሕግ ነበር።

ይህ ሕግ "እስከ አስቀያሚ እና አስጸያፊ ሆነው እንዲታዩ ነበር ያደረገው" ይላሉ ተመራማሪዋ።

በጊዜ ሒደት እንደ ኔቫዳ፣ ኦሪገን፣ ኔብራስካ፣ ኦሃዮ፣ ኤልኖይስ፣ ፔንሲልቬኒያ እና ሉዊዝያና ያሉ ግዛቶች የሳን ፍራንሲስኮን ሕግ መተግበር ጀመሩ።

ቺካጎ ሕጉን ያፀደቀችው በ1916 ሲሆን፣ እንደ መከራከሪያ የቀረበው ሐሳብ "ከጎዳናዎች አስቀያሚነትን ማስወገድ አለብን" የሚለው ነበር።

"አስቀያሚ ብለው የገለጹት ነገር ዓይነ ግቡ ያልሆነ አካባቢ አይደለም። ሰዎችን ከዕይታ ማስወገድ ነበር ግባቸው። 'ማተርናል ኢንፍሉዌንስ' የተባለው ዕሳቤ ነፍሰ ጡር ሴቶች የታመመ ወይም አካሉ የጎደለ ሰው ከተመለከቱ የሚወልዱት ልጅ ሕመምተኛ ይሆናል ይላል" ይላሉ ሱዛን ሻዊክ።

አያይዘውም "የሚጥል ሕመም ያለበት ሰው ወድቆ ማየት አሰቃቂ ነበር። ሰዎች ከሚሰማቸው ድንጋጤ እና መጸየፍ ለመላቀቅ ጊዜ ይወስድባቸዋል" በማለት ያክላሉ።

ለምጽዋት የተዘረጋ እጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሱዛን እንደሚሉት፣ ከአውሮፓውያኑ 1861 – 1865 ከተካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ ይህ ሕግ የወጣው እንዲሁ በአጋጣሚ አይደለም።

"ሳን ፍራንሲስኮ በድንጋጤ ተውጣ ነበር። በተለይም ከቻይና እና ከሌሎች አገራት ዓለም አቀፍ ስደት እየተበራከተ ነበር። ስለዚህም በየመንገዱ የተቸገሩ ሰዎች ይታያሉ" በማለት ያስረዳሉ።

ከተማው ከጦር ሜዳው የራቀ ስለሆነ የቆሰሉ እና የተጎዱ ሰዎች ማየት የተለመደ አልነበረም። የከተማው ነዋሪዎች መንገድ ላይ የሚያዩዋቸው አካል ጉዳተኛ ሰዎች "ከመሥራት ይልቅ መለመን" የሚመርጡ እንደሆኑ ያስቡ ነበር።

በወቅቱ የወጡ ሕጎችን የተራድኦ ድርጅቶች ሳይቀር ይደግፏቸው ነበር።

በቴምፕል ዩኒቨርስቲ በሚገኘው ኢንስቲትዩት ኦን ዲሰብሊቲ አጥኚ የሆኑት ራቄል ማንጌል "ተቋማዊ በመሆነ መንገድ አስቀያሚ የሆኑ ሰዎችን ለማስወጣት ሕጎች ጥቅም ላይ ውለዋል" ይላሉ።

አደባባይ ላይ የሚታዩ የታመሙ ወይም አካል ጉዳተኛ ሰዎችን ገንዘብ መቅጣትና ማሰር፤ እነዚህ ሰዎች ወደ የአእምሮ ሕሙማን መጠለያ አልያም በድህነት አረንቋ ውስጥ ያሉ ሰዎች ወደሚኖሩባቸው አካባቢዎች እንዲገቡ ማድረጉን ያስረዳሉ።

የታመሙ፣ አካላቸው የጎደለ ወይም ሰውነታቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን የሚቀጣ ሕግ ነበር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የታመሙ፣ አካላቸው የጎደለ ወይም ሰውነታቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን የሚቀጣ ሕግ ነበር

ድሆችን ዒላማ ማድረግ

ራቄል ማንጌል እንደሚሉት እነዚህ ሕግጋት ሲወጡ አስቀያሚ የተባሉ ሰዎችን ዒላማ ለማድረግ በሚል ሳይሆን አካል ጉዳተኞችን፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን እና የሚጥል በሽታን የመሰለ ሕመም ያለባቸው ሰዎችን ከመንገድ ላይ ለማራቅ በሚል ነበር የወጡት።

"የጎዳና ተዳዳሪዎች አልያም አካል ጉዳተኞች በአብዛኛው በድህነት ስለሚኖሩ የግድ መለመን ነበረባቸው። ሰዎች መንገድ ላይ ሲያዩዋቸው ይጸየፏቸው ነበር" በማለት ያስረዳሉ።

'አስቀያሚ ወይም አስጸያፊ' የተባሉት ሰዎች መንገድ ላይ ፓርኮች ውስጥ እንዳይገኙ ከማድረግ በተጨማሪ እንዳይለምኑ በማድረግም ሕይወታቸውን ፈተና ውስጥ የሚከቱ ሕግጋት ወጥተዋል።

ጎዳና ዳርቻ የነበሩ ነጋዴዎችም የገፈቱ ቀማሽ ሆነዋል።

ሱዛን እንደ ማሳያ የሚጠቅሱት በበአውሮፓውያኑ 1910 በክሊቭላንድ የተከሰተውን ነው።

እጅ እና እግሩ የተጎዳ ሰው ጋዜጣ መንገድ ላይ በመሸጥ ይተዳደራል። ሥራው "የአካል ጉዳተኛ አይደለም" ተብሎ ከሽያጩ ታግዷል።

ከዓመታት በኋላ በፖርትላንድ አንድ መንገድ ዳር ጋዜጣ የምትሸጥ ሴት "ልጆች ሲያዩዋት አስቀያሚ ሆና ስለሚያገኟት" ወደ ሌላ ከተማ ወይም ወደ እርሻ ቦታ እንድታዘወር ተነግሯታል።

ጋዜጣ ሻጯ ወደ ሎስ አንጀለስ ገብታ የአካል ጉዳተኛ አግብታ ኑሮዋን ቀጥላለች።

የአካል ጉዳተኞችን የእኩልነት መብት ለመጠየቅ የተደረገ ሕዝባዊ ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአካል ጉዳተኞችን የእኩልነት መብት ለመጠየቅ የተደረገ ሕዝባዊ ተቃውሞ

ለመድልዎ በር መክፈት

በወቅቱ በወጣው ሕግ ምን ያህል ሰዎች እንደተጎዱ በግልጽ በቁጥር የተቀመጠ መረጃ አልተገኘም። ፖሊሶች እና ፍርድ ቤቶችም መረጃ የላቸውም።

"ሕግጋቱ የሌሎች መርሆች አካል ሆነው ነው በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ አካባቢ የወጡት። በሕዝብ አደባባይ መታየት ያለባቸውን ሰዎች ለመወሰን ተተግብረዋል" ይላሉ ሱዛን።

ሕግጋቱ የዘር ክፍፍል እና መድልዎን በሕግ ከሚደግፉ ሌሎች መርሆች ጋር እንደሚያያዙም ያስረዳሉ።

ራቄል በበኩላቸው "በ19ኛው ክፍለ ዘመን በአንዳንድ የአሜሪካ ግዛቶች የፀደቁ ሰዎችን በዘረ መል የሚለያዩ ሕጎችም ከእነዚህ ሕግጋት ጋር ይተሳሰራሉ" ይላሉ።

አካል ጉዳተኞች እና የአእምሮ ሕሙማን ዘራቸው እንዳይቀጥል በግዳጅ መሃን ማድረግ የዚህ አካል ነበር።

እነዚህ ሕግጋት ዒላማ ያደረጉት አካል ጉዳተኞችን ቢሆንም በዋናነት ማስወገድ የፈለጉት ድሆችን እንደሆነ ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ።

በአውሮፓውያኑ 1921፤ በ39 ዓመታቸው የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት ፖሊዮ ይዟቸው ነበር። ከወገባቸው በታች ፓራላይዝድ ሆነው በዊልቸር ነበር የሚንቀሳቀሱት።

ሕመማቸው ከሕዝቡ ተደብቆ በአደባባይ ሲታዩ በክራንች ብቻ ተደግፈው እንደነበር ይታወሳል።

ትራምፕ ከጎዳና ተዳዳሪ ጎን ሲያልፉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ትራምፕ ከጎዳና ተዳዳሪ ጎን ሲያልፉ

ቢሞቱም አልተረሱም

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በ20ኛው ክፍለ ዘመን እነዚህ ሕግጋት ተግባራዊነታቸው እየቀነሰ መጥቷል። በ1970ዎቹ የአካል ጉዳተኞች መብት ተሟጋቾች ሕጎቹ እንዲሰረዙ ታግለው ስኬታማ ሆነዋል።

ሱዛን እንደሚያስረዱት፣ በአውሮፓውያኑ 1970 በኦማሀ፣ ኔብራስካ ፖሊስ የጎዳና ተዳዳሪ ለማሰር ሲሞክር ምክንያት ማግኘት አልቻለም።

የጎዳና ተዳዳሪው ምንም ጥፋት ባያጠፋም 'አስቀያሚዎችን ለመቅጣት' የወጣውን ሕግ ፖሊሱ ተጠቀመ። ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኛ ግን 'የጎረቤቶቼን ልጆችም አስቀያሚ ናቸው' ብለህ ልታስር ነው? ብለው የፖሊሱን እስራት አጣጣሉ።

የዳኛው ውሳኔ በጋዜጣ ከወጣ በኋላ ነበር የአካል ጉዳተኞች መብት ተሟጋቾች ትግላቸው የተፋፋመው።

ሁሉም ከተሞች ሕጉን ባይሽሩም አሜሪካ የአካል ጉዳተኞችን መብት የሚያስከብረውን ሕግ (Americans with Disabilities Act ወይም ADA) በ1990 ካፀደቀች በኋላ ቀድሞ የወጡት ሕግጋት ተሰርዘዋል።

ሆኖም ግን ሕግጋቱ ያሳደሩት ጫና ለዓመታት መዝለቁ አልቀረም።

ራቄል "አካል ጉዳተኞች የሚታዩበትን መንገድ ስንመለከተ የቀድሞው ሕግ በሰዎች አእምሮ እና በተቋማት አሠራር ውስጥ ሕጉ ያሳደረው ጫና አሁንም አለ" ሲሉ ያስረዳሉ።

ሱዛን በበኩላቸው "ሕጉ ባይኖርም አሠራሩ አሁንም አለ። ትራምፕ በቅርቡ ያስተላለፉት ትዕዛዝ ከዚህ ጋር ይተሳሰራል" ይላሉ።

ትራምፕ በ1990ዎቹ የፖለቲካ ሕይወታቸውን ሲጀምሩ የጎዳና ተዳዳሪዎችን እና አካል ጉዳተኞችን ከኒው ዮርክ፣ ፊፍዝ አቬኑ 'ለማስወገድ' ቃል በመግባት ነበር።

እነዚህ ሰዎች በአካባቢው ያለውን ትራምፕ ታወር 'አጠልሽተዋል' ሲሉ ነበር የገለጹት።

አሁን ደግሞ ሰዎችን 'አስቀያሚ' በማለት ሳይሆን ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ቤት አልባ ሰዎችን ለማግለል የሚውሉ አሠራሮች ይተገበራሉ። ጎዳና ተዳዳሪዎች በፓርኮች ወይም ባቡር ጣቢያዎች እንዳይተኙ አግዳሚ ወንበሮችን ምቹ አለማድረግ አንደኛው መንገድ ነው።