የዋሽንግተን ከንቲባ ተቃውሞ ያሰሙባቸው የአሜሪካ ብሔራዊ ዘብ አባላት በከተማዋ መታየት ጀመሩ

የአሜሪካ ወታደር በዋሽንግተን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወታደሮችን ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ካሰማሩ እንዲሁም የሚፈጸሙ ወንጀሎች ከቁጥጥር ውጪ ሆነዋል በሚል የከተማዋን የፖሊስ ኃይል ከተቆጣጠሩ ከቀናት በኋላ፤ የአሜሪካ ብሔራዊ ዘብ ወታደሮች በዋሽንግተን ዲሲ ጎዳናዎች ላይ መታየት ጀመሩ።

ማክሰኞ ምሽት የታጠቁ ተሽከርካሪዎች በአሜሪካዋ ዋና ከተማ ዙሪያ በሚገኙ የከተማ ማዕከላት እና የቱሪስት ቦታዎች ላይ ታይተዋል።

ዋሽንግተን ውስጥ 800 የብሔራዊ ዘብ ወታደሮች እና 500 የፌዴራል የሕግ አስከባሪ አካላት ይሰማራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

በከተማዋ ውስጥ የሚፈጸመው ወንጀል ከቁጥጥር ውጪ አለመሆኑን በመግለጽ የሚከራከሩት ዲሞክራቷ የዋሽንግተን ከንቲባ ሙሪየል ቦውሰር፤ ወታደሮች መሰማራታቸውን "አምባገነናዊ እርምጃ" ሲሉ ገልጸውታል።

ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው በኒው ዮርክ እና በቺካጎ ሌሎች በዲሞክራቶች ቁጥጥር ስር ባሉ ሁለት ከተሞች ውስጥም በተመሳሳይ መልኩ ወታደሮችን የማሰማራት እርምጃ እንደሚወስዱ ዝተዋል።

ሰኞ ዕለት ትራምፕ ይህንን ውሳኔ ማሳወቃቸውን ተከትሎ፤ የሠራዊት ልብስ የለበሱ ወታደሮች ወደ አሜሪካዋ ዋና ከተማ እየገቡ ነው።

በበርካታ የመንግሥት ህንጻዎች መግቢያ ላይ የእገዳ አጥር ሲያስቀምጡ እና ከቱሪስቶች ጋር ፎቶ ሲነሱ ታይተዋል።

የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት፤ የፌዴራል የፀጥታ አካላት ሰኞ ዕለት 23 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን ተናግረዋል።

የፌዴራል አካላቱ የከተማዋን ሕግ አስከባሪ አባላት እያገዙ መሆኑን አክለዋል።

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ከግድያ፣ ከጦር መሳሪያ ወንጀል፣ ከአደንዛዥ እፅ ዝውውር፣ ከወሲብ ነክ ድርጊቶች፣ ሰዎችን ከመከታተል፣ ከቁጥጥር ውጪ በሆነ መንገድ ከማሽከርከር እና ከሌሎች ወንጀሎች ጋር በተያያዘ እንደሆነም ቃል አቀባይዋ ገልጸዋል።

ሌቪት፤ "ይህ ገና ጅማሬ ነው" ሲሉም ተደምጠዋል።

"በሚቀጥለው ወር ውስጥ የትራምፕ አስተዳደር ሕግን የሚጥሱ፣ የሕዝብን ደኅንነት የሚያደፈርሱ እና ሕግን የሚያከብሩ አሜሪካውያንን አደጋ ላይ የሚጥሉ ወንጀለኞችን ያለመታከት ይከታተላል፣ ይይዛል" በማለት ተናግረዋል።

የአሜሪካ ወታደሮች በዋሽንግተን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ካሽ ፓቴል በበኩላቸው የተቋማቸው አባላት ከተፈጸሙት እስሮች ውስጥ ግማሽ ያህሉ ላይ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

የዋሽንግተን ከንቲባ እና የከተማው የፖሊስ ኃላፊ፤ ከፌዴራል አካላት ጋር ተመሳሳይ ዓላማ እንዳላቸው ከዚህ ቀደም ተናግረው ነበር።

ከንቲባዋ ቦውሰር፤ "እኔ ትኩረት ያደረግኩት በፌዴራል አካላት መጨመር እንዲሁም ያሉትን የፌዴራል አካላት እንዴት በተሻለ ሁኔታ መጠቀም እንችላለን የሚለው ላይ ነው" ሲሉ ማክሰኞ ዕለት ከሀገሪቱ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፓም ቦንዲ ጋር ከተገናኙ በኋላ ባደረጉት ንግግር አስረድተዋል።

የከተማዋ ሜትሮፖሊታን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ፓሜላ ስሚዝም "ሕገወጥ የጦር መሳሪያዎችን ከጎዳናዎቻችን ላይ ማስወገድ እንዳለብን እናውቃለን። እና የበለጠ [የፀጥታ አካላት] ስምሪት ካለን ከተማችንን የበለጠ የተሻለ እንደሚያደርጋት እናውቃለን" ብለዋል።

ከንቲባዋ ግን ማክሰኞ ማሽት ባደረጉት ንግግር በትራምፕ ላይ የሰነዘሩትን ወቀሳ አጠናክረዋል።

ቦውዘር ፤ "የራስ ገዝ አስተዳደራችንን ለመጠበቅ፣ የራሳችንን ሕግ ለማስጠበቅ እና ከዚህ ግለሰብ የሥልጣን ጊዜ ለማሳለፍ ከተማችንን ጠብቁ። እንዲሁም ይህንን አምባገነናዊ እርምጃ መከላከል እንድንችል የዴሞክራቲክ ምክር ቤትን እንደምትመርጡ እርግጠኛ ሁኑ" ሲሉ ለማኅበረሰቡ አባላትን ጥሪ ማቅረባቸውን ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል።

የዋሽንግተን ዲሲ ሜትሮፖሊታን ፖሊስ የወንጀል መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በ2023 የአመፅ የተቀላቀለባቸው ወንጀሎች ቁጥር ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረ ቢሆንም ባለፈው ዓመት 35 በመቶ በመቀነስ ከሶስት አስርት ዓመታት ወዲህ ዝቅተኛ በሆነው ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ነገር ግን የዲሲ ፖሊስ ማኅበር ሊቀመንበር ግሬግ ፔምበርተን ግን ይህንን ቁጥር ተቃውመውታል።

የከተማዋ ፖሊስ "ሆነ ብሎ የወንጀል መረጃን በማጭበርበር" እንዲሁም "ማኅበረቡ እየተሰቃየ ባለበት ሁኔታ ወንጀል ቀንሷል የሚል የተሳሳተ ትረካ በመፍጠር" ድርጊቶች ከስሷል።

የኤፍቢአይ መረጃዎች ባለፈው ዓመት የዋሽንግተን ዲሲ የወንጀል መጠን በዘጠኝ በመቶ እንደቀነሰ ያሳያሉ። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በዋና ከተማዋ የሚፈጸመው የግድያ ወንጀል ብዛት ከሌሎች የአሜሪካ ዋና ዋና ከተሞች ጋር ሲነጻጸር ከአማካይ ከፍ ያለ ነው።