ትራምፕ ለካፒቶል ዓመጽ ሁከት ቀስቃሾች ያደረጉት ይቅርታ

ትራምፕ በርካታ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዞችን ፈርመዋል

የፎቶው ባለመብት, EPA

የዶናልድ ትራምፕ ቡድን አባላት ጭምር እስከ ሰኞ ድረስ እንኳ በካፒቶል ሂል ተፈጥሮ በነበረው አመጽ የታሰሩትን ሁሉ እንደሚፈቱ ያመኑ አይመስሉም ነበር።

"በዚያን ቀን ሁለት ከፈጸሙ ይቅርታ ሊደረግልዎት አይገባም" ሲሉ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ከአንድ ሳምንት በፊት ተናግረው ነበር።

ከጥቂት ቀናት በኋላ ደግሞ በኮንግረስ ፊት ምስክርነት የሰጡት ዕጩዋ የትራምፕ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ፓም ቦንዲ በዕለቱ የተፈጠረውን ሁከት እንዲያወግዙ ከዲሞክራቲክ ፓርቲ ሴናተር ከቀረበላቸው ጠያቂ ጋር ተስማምተዋል።

"በማንኛውም የፖሊስ አባል ላይ በሚፈጸም ጥቃት አልስማማም" ከማለት ባለፈ ከአንድ ሺህ 500 በላይ የሁከት ፈጣሪዎችን ጉዳይ በተናጠል ለመመልከት ፈቃደኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ትራምፕ ግን በመጀመሪያ ቀን የስልጣን ዘመናቸው ጉዳዮቹን በተመለከተ ትልቅ እርምጃ ወስደዋል።

ሁሉንም ሁከት ፈጣሪዎች ነፃ ያወጣ እና በአሜሪካ ታሪክ ትልቁን የወንጀል የምርመራ ስራ የሰረዘ ይቅርታ አስተላልፈዋል።

ሰኞ ዕለት የሰጡት ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ አንዳንድ እስረኞች ከጠየቁት የመንግስት የገንዘብ ካሳ ክፍያ ውጭ ሁከት ፈጣሪዎቹ እና ደጋፊዎቻቸውን ሲጠይቁ የነበሩትን ነገሮች በሙሉ የሰጠ ነው ማለት ይቻላል።

ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት በዋይት ሃውስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "እነዚህ ሰዎች በእስር ቤት ዓመታትን በመጥፎ ሁኔታ አሳልፈዋል።

"አስጸያፊ እስር ቤት ነው። በጣም አሰቃቂ ነበር። ኢሰብአዊ ነው" ብለዋል።

በርከት ያሉ በሁከቱ የተያዙ ሰዎች በታሰሩበት በዋሽንግተን ዲሲ እስር ቤት፤ በተከሳሾቹ እና በደጋፊዎቻቸው በሚዘወሩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ብዙዎች ደስታቸውን ገልጸዋል።

ማክሰኞ የተለቀቀው የፕራውድ ቦይስ መሪው ኤንሪኬ ታሪዮ እናት ስለልጇ በመደበኛነት መረጃዎችን ስታጋራ ቆይታለች።

"የእኛ ፕሬዝደንት ልጄን እና ለሌሎቹም ሕይወታቸውን መልሰዋል! እንደገና መኖር ይችላሉ! እንደገና ንጹህ አየር ይተነፍሳሉ! እንደገና የፀሐይ ብርሃን ያገኛሉ" ስትል ዙኒ ታሪዮ 22 ዓመት ተፈርዶበት በፕሬዝዳንቱ ይቅርታ በነጻ ስለተለቀቀው ልጇ ጽፋለች።

ካፒቶል ሂል አመጽ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ማክሰኞ ዕለት ከዋሽንግተን ዲሲ እስር ቤት ከተፈቱት አንዷ የፔንስልቬንያ ነዋሪ የሆነችው ራቸል ፓውል ስትሆን የካፒቶል ሂል መስኮትን በበረዶ መጥረቢያ በመስበር ከአራት ዓመት በላይ እስራት ተፈርዶባት ነበር።

ከእስር ቤት ውጭ ለቢቢሲ እንደገለጸችው ከሆነ አሁን ለልጇ ልደት በሰዓቱ ቤት እንደምትደርስ ተናግራ ትራምፕ የገቡትን ቃል በመጠበቃቸው "ከማስበው በላይ ለእኔ ትልቅ በረከት ናቸው" ስትል አመስግናቸዋለች።

አንዳንድ ታዛቢዎች፣ የፖሊሲ ባለሙያዎች እና የሁከት ፈጣሪዎቹ ጠበቆች ጭምር በፕሬዚዳንቱ የትዕዛዝ መጠን ተገርመዋል።

ይቅርታውን የሚቃወመው እና ለትርፍ ያልተቋቋመ ፐብሊክ ሲቲዝንን በፕሬዝዳንት የሚመሩት ሊዛ ጊልበርት "አመጽ በፈጸሙት እና ባላጠፉት መካከል ያለውን ልዩነት ለማየት እንድንችል አጠቃላይ መግባባት ነበር" ብለዋል።

"ዶናልድ ትራምፕ በህግ እና በስርአት ለስልጣን ተወዳድረዋል። ስለዚህ ወንጀለኞችን ይቅርታ ለማድረግ እርምጃ ሲወስድ ማየት አስደንጋጭ እና አሳዛኝም ነው" ብለዋል።

በጣም ከባድ በሆኑ ወንጀሎች የተከሰሱ 14 ሰዎች ቅጣታቸው ተቀይሮ ከእስር ቢለቀቁም ጥፋታቸው ተመዝግቦ ይቆያል ተብሏል።

የፍትህ ቢሮ ባወጣው ዘገባ አንድ ሺህ 583 ሰዎች ከአመጹ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ታስረዋል ወይም ተፈርዶባቸዋል።

ከ600 በላይ የሚሆኑት ፖሊስን በማጥቃት፣ በመቃወም ወይም በማደናቀፍ የተከሰሱ ሲሆን ከነዚህም መካከል 175 የሚሆኑት መሳሪያ በመጠቀም ወይም ፖሊስ ላይ ከባድ ጉዳት በማድረስ የተከሰሱ ናቸው።

አብዛኛዎቹ ጥፋተኛ ተብለው የተፈረደባቸው ሰዎች ፍርዳቸውን አጠናቀዋል ወይም ምንም ዓይነት እስር አልተላለፈባቸው። እስካሁን በእስር ላይ የሚገኙት 250 የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ መፈታት ጀምረዋል።

ተጨማሪ ምርመራዎች ለማድርግ ኤፍቢአይ ቢያንስ 13 ተጠርጣሪዎችን እየፈለገ የነበር ቢሆንም ሂደቱ ይቋረጣል።

እስረኞቹ በመፈታታታቸው ደስታቸውን የሚገልጹ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Image

ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዝዳንቱ ኤድ ማርቲንን የዋሽንግተን ዲሲ ተጠባባቂ የዩናይትድ ስቴትስ ዓቃቤ ህግ አድርገው ሰይመዋል። ሹመቱ የአመጽ ጉዳዮችን ለመከታተል ቀዳሚውን ሚና ይወስዳል።

ማርቲን ከአመጹ አንድ ቀን በፊት ለትራምፕ የተዘጋጀ የድጋፍ ሰልፍ ያካሄዱ ሲሆን የአመጹን አጠቃላይ ምርመራም አጥብቀው ሲተቹ ነበር።

በምርጫ ዘመቻው ወቅት ትራምፕ ስለ ሁከት ፈጣሪዎቹ የተለያዩ መግለጫዎችን ሰጥተዋል። አንዳንድ ጊዜ ሙሉ ምህረት እንደሚደረግላቸው ቃል ሲገቡ ግን አልፎ አልፎ ደግሞ አንዳንዶቹን እስር ቤት እንዲቆዩ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ሲያሳዩ ነበር።

የሁከት ፈጣሪዎች ደጋፊዎች ይቅርታውን በተመለከተ ሰኞ ዕለት ደስታቸውን ገልጸዋል። አመጸኞቹን "የጄ6 ታጋቾች" እና "የፖለቲካ እስረኞች" ከማለት ባለፈ ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው እና ጭካኔ የሞላበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

አንዳንድ እስረኞችን የወከለው ጠበቃው ኖርም ፓትስ ለቢቢሲ ኒውስ ሃወር እንደተናገረው ከሆነ "ይህ ክስተት አገሪቱን ያስፈራራል የሚለው አስተሳሰብ ከልክ ያለፈ ነው" ከማለት ባለፈ የኮንፌደሬት አማፂያን ከእርስ በርስ ጦርነት በኋላ ይቅርታ እንደተደረገላቸው ተናግሯል።

"ከእንዲህ ዓይነቱ የጥቃት ድርጊት እና ሰዎች በግልፅ መሳሪያ አንስተው እርስበርስ ከተገዳደሉ በኋላ እንደ አገር አንድ ላይ ከተሰባሰብን... አንድ ከሰኣት ከተፈጠረ ሁከት ከአራት ዓመት በኋላ ከሰአት በኋላ ሰዎችን ለምን በወንጀል መክሰስ ጀመርን?" በማለት አክሏል።

ለወንጀለኞች በሙሉ ይቅርታ መደረጉ ተቀባይነት እንደሌለው የሕዝብ አስተያየት መስጫዎች ይጠቁማሉ። በቅርቡ የተደረገ የአሶሼትድ ፕሬስ ጥናት እንደሚያመለክተው ከ10 አሜሪካውያን መካከል ሁለቱ ብቻ ለአብዛኛዎቹ ይቅርታ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

በእለቱ በቡጢ የተመታ እና በርበሬ የተረጨበት የካፒቶል ፖሊስ አባል ዊንስተን ፒንግዮን ለኒውስሃወር እንደተናገረው ከሆነ ይቅርታው "ያልተጠበቀ እና የሚያናድድ ነው" ብሏል።

"በአገሪቱም ሆነ በመላው ዓለም የፈጸሙት ነገር የታየባቸው እነዚህ በዳኞች የተፈረደባቸው ወንጀሎች በነፃነት እንደሚወጡ ማድረጉ ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ ነገር ነው" ብሏል።

ትራምፕ በፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዙ ለ14ቱ ወንጀለኞች ሙሉ ይቅርታ ከመስጠት ይልቅ ጉዳዩን ለመቀነስ የመረጡበትን ምክንያት አብራርተዋል። ዝርዝሩ የቀኝ አክራሪው ፕራውድ ቦይስ እና የኦዝ ኪፐርስ ሚሊሻ አባላትን ያካትታል። የኦዝ ኪፐርስ መሪው ስቱዋርት ሮድስ በዝርዝሩ ውስጥ የነበረ ሲሆን ማክሰኞ ረፋድ ላይ እንደተለቀቀ ጠበቃው ተናግረዋል።

የቀድሞ የአሜሪካ ጦር አባል እና ዬል ዩኒቨርሲቲ የተማረው የህግ ባለሙያው ሮድስ አመጹ ከመፈጠሩ ጥቂት ቀናት በፊት ኦዝ ኪፐርስን ወደ ዋሽንግተን መርቷል። ቡድኑ በቨርጂኒያ ከፖቶማክ ወንዝ ማዶ በሚገኝ የሆቴል ክፍል ውስጥ መሣሪዎያዎችን መደበቁን ፍርድ ቤት ማስረጃዎች ያስረዳሉ። ሮድስ ወደ ካፒቶል ሂል ባይገባም ግን አባላቱን ከውጭ ሆኖ በመምራት እአአ በ2023 የ18 ዓመት እስራት ተፈርዶበታል።

የሮድስ ጠበቃ ጀምስ ሊ ብራይት ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሆነ የይቅርታው ስፋት፣ ባህሪ እና እስረኞች የሚፈቱበት ፍጥነት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውንም ሰዎች ጭምር አስገርሟቸዋል።

"ምንም እንኳን ከፕሬዚዳንቱ ጋር ቅርበት ካላቸው ሰዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት ቢኖረንም ከፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዙ በፊት ትንፍስ አላሉም ነበር" ብለዋል።

ይቅርታ ከተደረገላቸው መካከል የፕራውድ ቦይስ መሪው ኤንሪኬ ታሪዮ ይገኝበታል

የፎቶው ባለመብት, Getty Image

የፕራውድ ቦይስ የቀድሞ መሪው ታሪዮ ሙሉ ይቅርታ አግኝቷል። አምስት የቡድኑ አባላት ውሳኔ በተቀነሰላቸው ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ነበሩ። ከከተማው ታግዶ ስለነበር ታሪዮ በዕለቱ በቦታው አልነበረም። ይልቁንም በአቅራቢያው ከሚገኘው ባልቲሞር ሆቴል ከፕራውድ ቦይስ ጋር ይነጋገር ነበር።

ሮድስ ከታሰረ በኋላ በአብዛኛው የኦዝ ኪፐርስ እንቅስቃሴ የቆመ ሲሆን ፕራውድ ቦይስ ግን በአካባቢው በተደረጉ ተቃውሞዎች ላይ አተኩሮ ነበር። ፕራውድ ቦይስ በመስራች አባላት እና በግልጽ የነጭ ብሔርተንነት አስተሳሰብን በሚደግፉ ቡድኖች መካከል በተፈጠረ ሽኩቻ ተከፋፍለው ነበር።

አዲስ የተለቀቁት የሚሊሻ አባላት ተግባራቸውን ለመቀጠል ሊሞክሩ እንደሚችሉ እና በአብዛኛው የተበታተኑትን የቀኝ አክራሪ ቡድኖችን ወደ ቀድሞ ተግባራቸው ሊመልሳቸው እንደሚችል የጸረ ጥላቻ እና አክራሪነት ግሎባል ፕሮጄክት መስራች የሆኑት ዌንዲ ቪያ ተናግረዋል።

ሰኞ ዕለት በርካታ የፕራውድ ቦይስ አባላት ትራምፕን በዓለ ሲመት ለማክበር በዋሽንግተን ሲዘዋወሩ ታይተዋል።

"ፕራውድ ቦይስ ድርጅቱ በ2021 ወደ ነበረው ማዕከላዊነት ለመመለስ ሊሞክሩ ይችላሉ? ይህ ትልቅ ጥያቄ ይሆናል" ሲሉ ገልጸዋል።

"የእነዚህ ይቅርታዎች ችግር ትራምፕ አመጽ ሁነኛ የለውጥ መሳሪያ ነው በማለት መልዕክት ማስተላለፋቸው ነው" ሲሉ አጠቃለዋል።