የአሜሪካ መሪዎች የሚያወጧቸው ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዞች ምንድን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, EPA
የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች በመንግሥት ፖሊሲ ላይ አሻራቸውን ለማሳረፍ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዞች ቁልፍ መሳሪያዎቻቸው ናቸው። ዶናልድ ትራምፕም ወደ ዋይት ሐውስ ተመልሰው ጊዜ ሳያጠፉ ተግባራዊ እያደረጓቸው ነው።
ትራምፕ ሥልጣን በተረከቡበት ሰኞ ዕለት ብቻ ከ200 በላይ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዞችን ይፈርማሉ ተብሎ ሲጠበቅ ነበር። ይህም በሕጋዊ መንገድ አስገዳጅ የሆኑ ትዕዛዞችን እና እንደ አዋጆች ያሉ እንዲሁም በአብዛኛው አስገዳጅ ያልሆኑ ሌሎች ፕሬዝዳንታዊ ት መመሪያዎችን ያካትታል።
ትራምፕ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ፕሮግራሞችን እንደሚያሳድጉ፣ የመንግሥትን ብቃት የሚገመግም አዲስ መሥሪያ ቤት እንደሚያቋቁሙ፣ ከጆን ኤፍ ኬኔዲ ግድያ ጋር የተያያዙ ሰነዶችን ይፋ እንሚያደርጉ፣ ሠራዊታቸው አይረን ዶም የተባለውን የሚሳዔል መከላከያ ሥርዓት እንዲገነባ እንዲሁም በአሜሪካ ሠራዊት ውስጥ ብዝኃነት፣ ፍትሃዊነት እና አሳታፊነትን የሚለው ፖሊሲ እንዲቀር ያደርጋሉ።
ትራምፕ ከአራት ዓመት በፊት በነበረው የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው 220 ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዞችን የፈረሙ ሲሆን፣ አንዳንዶቹም ውድቅ እንዲደረጉ ወደ ፍርድ ቤት ተወስደዋል።
ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ምንድን ነው?
ይህ በፕሬዝዳንቱ የሚተላለፈው ትዕዛዝ በፌዴራል መንግሥቱ የሥልጣን ክልል ውስጥ የሚጸም ሲሆን፣ የአገሪቱን ምክር ቤት (ኮንግረስ) ይሁንታን የማይፈልግ ነው።
ትዕዛዞቹ ከከፍተኛ የፖሊሲ ለውጦች (ለምሳሌ ትራምፕ እአአ በ2017 ውዝግብ የተነሳባቸው ሁለት የነዳጅ ማስተላለፊኣ ቧንቧዎችን ለመገንባት ፈቅደዋል) እስከ አነስተኛ ጉዳዮች (ለምሳሌ ባራክ ኦባማ በ2015 የገና ዋዜማ ዕለት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለግማሽ ቀን ብቻ እንዲሠሩ አዘዋል) ያሉትን ያካትታሉ።
ትዕዛዙን የመስጠት ሥልጣን በዩናይትድ ስቴትስ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 2 ላይ የተመሠረተ ነው። "የአስፈጻሚው ሥልጣን የሚሰጠው ለዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ፕሬዚዳንት ነው" ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዝዳንቶች ለምን ትዕዛዞቹን ያወጣሉ?
አንዳንድ ጊዜ ትዕዛዞቹ የሚወጡት በጦርነት ጊዜ ወይም የአገር ውስጥ ችግርን ለማስወገድ ነው። እአአ በ1942 ፕሬዝዳንት ፍራንክሊን ዲ ሩዝቬልት ወደ 120 ሺህ የሚጠጉ ጃፓናውያን አሜሪካውያንን ለማሰር እስር ቤቶች እንዲገነቡ የሚያደርግ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ፈርመዋል።
እአአ በ1952 ፕሬዚደንት ሃሪ ትሩማን የሥራ ማቆም አድማን ለማስቀረት የብረታ ብረት ኢንዱስትሪውን በመንግሥት ቁጥጥር ስር የሚያደርግ ትዕዛዝ አውጥተዋል።
እአአ ጥር 20 ቀን 2021 ባይደን በመጀመሪያዋ ሥልጣን ቀናቸው አሜሪካ የ2015 የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነትን እንደገና እንድትቀላቀል የሚያስችል ሂደትን የሚያስጀምር ትዕዛዝ ፈርመዋል።
አሜሪካ የዓለም ሙቀት መጠንን ለመቆጣጠር ያስችላል ከተባለው ስምምነት እንድትወጣ አድርገው የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ ናቸው።የባይደን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን "ሁላችንም ከአደጋ የሚያርቅ የዓለም ሙቀት መጨመርን እንድንከላከል ይረዳናል" በማለት አሜሪካ ወደ ስምምነቱ የመመለሷን አስፈላጊነትን በተመለከተ ተናግረው ነበር።
ትዕዛዙን ማን ሊሽረው ይችላል?
በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ በአገሪቱ ሕግ ወሰን ውስጥ መተላለፍ አለበት። እያንዳንዱ ትዕዛዝም በአገሪቱ የሕግ አማካሪ ቢሮ አማካይነት ሕጋዊነቱ ይገመገማል፤ ነገር ግን ይህ ሁልጊዜ የሚሆን አይደለም።
ትዕዛዙ ተቀባይነት ካለው የሕግ ወሰን ውጪ እንደወጣ ከታሰበ ሕጋዊ ግምገማ ሊደረግበት ይችላል።
የአገሪቱ ምክር ቤትም (ኮንግረሱ) የፕሬዝዳንቱን ትዕዛዝ የሚሽር ሕግ ሊያፀድቅ ይችላል። ፕሬዝዳንቱ ግን አሁንም ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት እንዳላቸው የሕገ-መንግሥት ማዕከል ገልጿል።

ለምንድነው ፖለቲካዊ የሚሆኑት?
ከኮንግረስ የሚሰጠውን ድጋፍ በማለፍ ፕሬዝዳንቱ በራሳቸው እርምጃ እንዲወስዱ ስለሚያስችላቸው ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዞች አወዛጋቢ ናቸው።
ኦባማ በ2010 ያወጡትን የጤና አጠባበቅ ትዕዛዝ በመቃወም ሪፐብሊካኖች ክስ አቅርበው ነበር። የጤና መድን ሽፋን ቀነ ገደቡን በማዘግየት ከሕገ መንግሥታዊ ሥልጣናቸውን አልፈዋል ሲሉም ተከራክረዋል።
የትራምፕ በአንዳንድ በርካታ ሙስሊም ሕዝብ ካላቸው አገራት ወደ አሜሪካ በሚመጡ ሰዎች ላይ የጣሉት የጉዞ እገዳም በጣም አወዛጋቢ ነበር። ባይደን ወደ ዋይት ሐውስ ሲገቡ ይህንን ውሳኔ ውድቅ አድርገውታል።
የኮንግረሱ አባላት በጣም በዝግታ ሲሠሩ ወይም ፕሬዝዳንቱ አዲስ ስለሚወጣ ሕግ ዝርዝር መግለጫ መስጠት እንዳለባቸው ሲሰማቸው ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላሉ።
ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዞች ምን ያህል በተደጋጋሚ ይወጣሉ?
ፍራንክሊን ዲ ሩዝቬልት በ12 ዓመታት የሥልጣን ዘመናቸው 3721 ያህሉ ትዕዛዞችን አውጥተዋል። ዉድሮው ዊልሰን እና ካልቪን ኩሊጅ 1803 እና 1203 ጊዜ በማውጣት ይከተላሉ።
ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው 220 ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዞችን ፈርመዋል።
ጆ ባይደን በአራት ዓመት ሥልጣን ዘመናቸው 160 ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዞችን የሰጡ ሲሆን፣ ሁለት የሥልጣን ዘመን የነበራቸው ባራክ ኦባማ (277) እና ጆርጅ ደብሊው ቡሽ (291) ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዞችን አስተላልፈዋል።
አዲስ ፕሬዝደንት የቀድሞውን ትዕዛዝ መቀልበስ ይችላልን?
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፕሬዝዳንቶች ከእነሱ ቀድመው የነበሩትን መሪዎች ያወጧቸውን ሕጎች ለመቀልበስ የፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዞችን የማውጣታቸው ሂደት እየጨመረ ነው።
ትራምፕ እአአ በ2017 በኦባማኬር (የጤና እንክብካቤን የሚመለከት ሕግ) ላይ ያነጣጠረ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ በማውጣት ጀምረዋል።
ባይደን በሜክሲኮ ድንበር ላይ ለሚገነባው አጥር የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ያለመውን የትራምፕ አስተዳደር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ሽረዋል። በአንዳንድ የሙስሊም አገራት ላይ ተጣለውን የጉዞ እገዳንም አንስተዋል።
አሜሪካንንም ወደ ፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነት መልሰዋል።
ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሥልጣን ሲመለሱ ከበርካታ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዞችን ለመፈረም ቃል በገቡት መሠረት ተግባራዊ ማድረግ ጀምረዋል።












