የትራምፕ አስተዳደር ከቀናት በፊት ያባረራቸውን የኒውክሌር ደኅንነት ሠራተኞች መልሶ ለመቅጠር ተቸገረ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ከቀናት በፊት ከሥራ ያሰናበታቸውን የኒውክሌር ደኅንነት ሠራተኞች መልሶ ለመቅጠር መቸገሩን አንድ የአሜሪካ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘገበ።
ብሔራዊ የኒውክሌር ደኅንነት አስተዳደር ከቀናት በፊት ነው በመቶዎች ለሚቆጠሩ የድርጅቱ ሠራተኞች የስንብት ደብዳቤ የላከው።
ኤንቢሲ የተባለው ጣቢያ ያገኘው ደብዳቤ እንደሚያሳየው "አንዳንድ ሠራተኞች ተመልሰው እንዲቀጠሩ ሙከራ ቢደረግም በምን መንገድ እንደምናገኛቸው ማወቅ አልተቻለም።"
ሠራተኞቹ ከሥራ የተባረሩት ሥልጣን ከጨበጡ አንድ ወር ያልሞላቸው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የፌዴራል ሠራተኞችን ቁጥር ለመቀነስ ባወጡት ትዕዛዝ መሠረት ነው።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ባለፈው ወር ብቻ ከ10 ሺህ በላይ የፌዴራል መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ከሥራ መደባቸው ተባረዋል።
ዋይት ኃውስ የፌዴራል ሠራተኞች ጥቅማጥቅም ተቀብለው በገዛ ፈቃዳቸው ሥራቸውን እንዲለቁ ማስታወቁን ተከትሎ ከ75 ሺህ በላይ ሠራተኞች ሥራቸውን ለመልቀቅ ፈቃደኛ መሆናቸውን ማሳወቃቸው ተነግሯል።
በሀገሪቱ ያሉ ኒውክሌር ክምችቶችን ደኅንነት የሚቆጣጠሩት ሠራተኞች ባለፈው ሐሙስ ነው የስንብት ደብዳቤ የደረሳቸው። ሲኤንኤን እንደዘገባው አንዳንድ ሠራተኞች የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ያለበት ቦታ የሚሠሩ ናቸው።
ሠራተኞቹን መልሶ ለመቅጠር የተላከው ደብዳቤ እንዲደርሳቸው በሚል አሁን ሥራ ላሉ ሠራተኞች ኢሜል እንደተላከላቸው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ሀገር ቤት እና ከሀገር ውጭ ያሉ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞችን ለመቀንስ ጥረት እያደረገ ሲሆን የትምህርት ሚኒስቴርን ለማጥፋትም ቆርጦ የተነሳ ይመስላል።
ትራምፕ ይህ ዕቅዳቸው እንዲሳካ የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለሀብት የሆነው ኢላን መስክን የቀጠሩ ሲሆን ዶጅ የተባለው ለመስክ የተቋቋመው መሥሪያ ቤት የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች እና የተራድዖ ድርጅቶችን እያመሰ ይገኛል።
ባለፈው ሳምንት የትራምፕ አስተዳደር የሙከራ ጊዜ ላይ ያሉ አሊያም ሥራቸው ላይ አንድ ዓመት ያልሞላቸው የፌዴራል ኤጀንሲ ሠራተኞች እንዲባረሩ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
በጠቅላላው በትራምፕ አስተዳደር ውሳኔ ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ሥራ አልባ ሊሆን እንደሚችሉ ይገመታል።
ትራምፕ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶችን የቅጥር አቅም ለመቀነስ የሚያደርጉት ሙከራ ከፍርድ ቤት ፈተና ገጥሞታል።
ፕሬዝደንቱ ባለፈው የአውሮፓውያኑ ጥር 20 ሥልጣን ከጨበጡ የወሰኗቸው ውሳኔዎችን ተከትሎ ከ60 በላይ ክሶች ተመሥርተዋል።












