የተኩስ አቁም ስምምነት በተደረሰባት ጋዛ እስራኤል በፈጸመችው የአየር ጥቃት 73 ሰዎች ተገደሉ

በጋዛ የተፈጸመው ጥቃት

የተኩስ አቁም ስምምነት በተደረሰባት ጋዛ እስራኤል በፈጸመችው የአየር ጥቃት 73 ፍልስጤማውያን መገደላቸው ተገለጸ።

እስራኤል እና ሐማስ የደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነት በመጪው እሁድ፣ ጥር 11/2017 ዓ.ም. ተግባራዊ መሆን ይጀምራል የተባለ ሲሆን፣ እስራኤል በጋዛ እየፈጸመችው ያለው ጥቃት እንደቀጠለ ነው።

ሁለቱ ወገኖች የደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነት ከእስራኤል በኩል የምክር ቤቱን ይሁንታ ማግኘት አለበት ተብሏል።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ ረቡዕ፣ ጥር 7/2017 ዓ.ም. ይፋ መሆኑን ተከትሎ እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት 73 ፍልስጤማውያን በአንድ ምሽት መገደላቸውን በሐማስ የሚተዳደረው የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ አስታውቋል።

ከተገደሉት መካከል በጋዛ ከተማ ሼክ ራድዋን ሰፈር በአንድ መኖሪያ ህንጻ ነዋሪ የነበሩ 12 ሰዎች እንደሚገኙበት የጋዛ የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።

የእስራኤል መከላከያ በበኩሉ በደቡባዊ እስራኤል "የወደቀ ሚሳኤል" ማግኘቱን መጀመሪያ ላይ አስታውቆ የነበረ ቢሆንም በኋላ ግን ስህተት ነው ብሏል።

እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነቱ ጫፍ ላይ ደርሷል በተባለበት ወቅትም እየፈጸመችው ያለውን የአየር ጥቃት ቀጥላለች።

በጋዛ ብቻ ሳይሆን በኅዳር ወር በሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት ሊደረግ ጥቂት ሰዓታት ሲቀረው እስራኤል በመዲናዋ ቤይሩት ውስጥ ከባድ የአየር ጥቃት ፈጽማለች።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሐሙስ፣ ጥር 8/2017 ዓ.ም. የጋዛን የተኩስ አቁም ስምምነት በፓርላማ ያጸድቃሉ ተብሎ ቢጠበቅም፣ ጽህፈት ቤታቸው ሐማስ የስምምነቱን አንዳንድ ክፍሎች "እንደሻረ" በመግለጽ "የመጨረሻ ደቂቃ ቀውስ" እንዲፈጠር አድርጓል ሲሉ ወቅሰዋል።

ሐማስ ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ እስካልተቀበለ ድረስ ካቢኔው እንደማይሰበሰብም ጽህፈት ቤታቸው አክሏል።

የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሐማስ በአደራዳሪዎቹ ይፋ ለተደረገው ስምምነት ቁርጠኛ መሆኑን እና የልዑካን ቡድኑ መሪ ኻሊል አል ሃያ የስምምነቱን ውሎች ሙሉ በሙሉ መቀበላቸውን ለኳታር እና ግብፅ በይፋ አሳውቀዋል ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሁለት የእስራኤል የቀኝ ክንፍ አክራሪ ሚኒስትሮች የገንዘብ ሚኒስትሩ ቤዛሌል ስሞትሪች እና የብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስርሩ ኢታማር ቤን ጊቪር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ የሚደረስ ከሆነ ከጥምር መንግሥቱ ራሳቸውን እንደሚያገሉ ለረጅም ጊዜ ሲዝቱ ቆይተዋል።

የሚኒስትሮቹ መልቀቅ በእስራኤል ውስጥ አዲስ ምርጫ እንዲደረግ በር ከመክፈት ውጭ ኔታንያሁ ከፈለጉ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተግባራዊ ከመሆን አያግደውም ይላሉ ታዛቢዎች።

የተኩስ አቁም ስምምነቱን ያደራደሩት የኳታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር በበኩላቸው ስድስት ምዕራፍ ያለው ስምምነት ከመጀመሩ በፊት ሁለቱም ወገኖች እንዲረጋጉ ጠይቀዋል።

በዚህ የመጀመሪያው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ሴቶች፣ ህጻናት እና አዛውንቶችን ጨምሮ 33 ታጋቾች ይለቀቃሉ።

እስራኤል በምላሹ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ትለቃለች።

የእስራኤል ጦር ከምሥራቃዊ የጋዛ ክፍል እንደሚወጣ እና የተፈናቀሉ ሰዎች ወደቀያቸው እንዲመለሱ እንደሚፈቀድላቸው ተገልጿል።

በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ የእርዳታ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ ሰርጥ እንዲገቡም ይፈቀዳል።

በሁለተኛው የስምምነቱ ዙር ተጨማሪ ታጋቾች የሚለቀቁ ሲሆን፣ ይህም የመጀመሪያው ዙር ስምምነት የሚተገበረው 16 ቀን ሲሞላው ነው።

ሦስተኛው እና የመጨረሻው ደረጃ ጋዛን መልሶ መገንባት ሲሆን፣ ይህም ዓመታት ይወስዳል።

በዚህ ምዕራፍ የታጋቾች አስክሬንም ይመለሳል።

ሼኸ መሐመድ እንዳሉት ሁለተኛ እና ሦስተኛውን ምዕራፍ ለመደራደር ግልጽ አሠራር ተቀምጧል።

ዝርዝር መረጃው በቀጣይ ቀናት ይፋ ይሆናል።

ኳታር፣ አሜሪካ እና ግብፅ ስምምነቱ እንዲደረስ አግዘዋል። እስራኤል እና ሐማስ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚከታተሉም ይሆናል።

እስራኤል በጋዛ ጦርነት በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመች ነው ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ መግለጹ ይታወሳል። እስራኤል ይህንን አልተቀበለችውም።

መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም የእስራኤል ባለሥልጣናት ፍልስጤማውያንን ከሰብዓዊነት ባወረደ መልኩ የሚሰጧቸው ትርክቶች እንዲሁም እስራኤል ሆን ብላ ተቋማት ላይ ካደረሰቻቸው ውድመቶች እና እልቂቶች በመነሳት የዘር ጭፍጨፋ ድምዳሜ ላይ መድረሱን ገልጾ ነበር።

በተጨማሪም በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንን ሆን ብላ በገፍ በማፈናቀል የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል መፈጸሟን ሂውማን ራይትሰ ዋች አስታውቆ ነበር።

እስራኤል በበኩሏ ሪፖርቱን አጣጥላ "ሙሉ በሙሉ ስህተት እና ከእውነታ የራቀ ነው" ማለቷ ይታወሳል።

እስራኤል በጋዛ ውስጥ እየፈጸመችው ባለው ጥቃት ከ46,700 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።

ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።