በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ያልተመለሱ ጥያቄዎች

የጋዛ እና እስራኤል ነዋሪዎች ደስታቸውን ሲገልጹ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu / Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የጋዛ እና እስራኤል ነዋሪዎች ደስታቸውን ሲገልጹ

የእስራኤልና ሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነት የ15 ወራቱን የጋዛ ጦርነት ያስቆማል ተብሎ ይጠበቃል።

የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሼኽ መሐመድ ቢን አብዱል ራሕማን አል ታሕኒ እንዳሉት ስምምነቱ በእስራኤል ካቢኔ ከፀደቀ የፊታችን እሑድ መተግበር ይጀምራል።

ሐማስ በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7/2023 እስራኤል ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ የተነሳውን ጦርነት ለማስቆም ለወራት ጥረት ሲደረግ ነበር።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ስምምነቱ "በጋዛ ግጭት ያስቆማል፣ የሰብአዊ እርዳታ ለንጹሃን ፍልስጤማውያን ዜጎች ያደርሳል፣ ታጋቾችን ከ15 ወራት ይዞታ አስለቅቆ ከቤተሰባቸው እንዲቀላቀሉ ያስችላል" ብለዋል።

እስራኤልና ሐማስ አንደኛቸው ሌላኛቸውን ለማጥፋት የገቡበትን ጦርነት ለመግታት በቀጥታና በተዘዋዋሪ ለወራት ድርድር ሲካሄድ ነበር።

ሐማስ፤ እስራኤል ጦርነቱን ካላቆመች ታጋቾችን እንደማይለቅ ሲያሳውቅ ቆይቷል። እስራኤል ይሄን ቅድመ ሁኔታ አልተቀበለችም።

ስምምነቱን ተከትሎ ጦርነቱ እስከወዲያኛው ማክተሙ እርግጥ አይደለም።

የሐማስን ወታደራዊና አስተዳደራዊ አቅም ማሽመድመድ የእስራኤል ዓለማ ነበር። ሀማስ ላይ እስራኤል ከፍተኛ ጉዳት ብታደርስም አሁንም ቡድኑ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚያስችል አቅም አለው።

የታጋቾችና እስረኞች መለቀቅ

የትኞቹ ታጋቾች በሕይወት እንዳሉና ሐማስ በሕይወት ያሉት ታጋቾች የት እንደሚገኙ ስለማወቁ ግልጽ አይደለም።

እስራኤል መልቀቅ የማትፈልጋቸውን እስረኞች ለማስፈታት ሐማስ ቆርጦ ተነስቷል። ከታሰሩት መካከል ጥቅምት 7 እስራኤል ላይ ጥቃት ያደረሱ ይገኙበታል።

እስራኤል በተሰጠው ጊዜ ከጦር ቀጣና አካባቢ ትወጣለች የሚለውም ግልጽ አይደለም።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ ስሱ ነው ማለት ነው።

ጋዛ

የፎቶው ባለመብት, Mohammed Saber / EPA

ከዚህ ቀደምም የተኩስ አቁም ተደርጎ ጦርነቱ ቆሞ የነበረ ሲሆን፣ ግጭቶች ሲነሱ ስምምነቱ ፈርሷል።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ በጊዜ የተከፋፈለበት መንገድ ውስብስብነቱ ትንሽ ነገርም ቢከሰት ለሰላም ስጋት ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንዴት ይሠራል?

የተኩስ አቁም ስምምነቱ በሦስት ደረጃ ይተገበራል።

አሁን ሁለቱም ወገኖች በዚህ ተስማምተዋል። ሆኖም የእስራኤል መንግሥት ስምምነቱን ከመተግበሩ በፊት ከካቢኔው ይሁንታ ማግኘት ይኖርበታል።

የእስራኤል መንግሥት ቃል አቀባይ ዴቪድ መንስር እንዳሉት በሁለተኛው የስምምነቱ ክፍል ሴቶች፣ ሕጻናት፣ ሕሙማን፣ የተጎዱ ሰዎች እና አዛውንቶችን ጨምሮ 33 ታጋቾች ይለቀቃሉ።

እስራኤል በምላሹ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ትለቃለች።

የፍልስጤም ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንደገለጹት ሦስት ታጋቾች በአፋጣኝ ይለቀቃሉ። የተቀሩት በስድስት ሳምንታት ውስጥ ይለቀቃሉ።

በዚህ ጊዜ የእስራኤል ጦር ከጋዛ በሕዝብ የተጨናነቁ አካባቢዎች ለቆ ይወጣል። ይሄ ሒደት ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድ ግልጽ አይደለም።

ከጋዛ 2.3 ሚሊዮን ነዋሪዎች መካከል አብዛኞቹም ተፈናቅለዋል

የፎቶው ባለመብት, Bashar Taleb / AFP / Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከጋዛ 2.3 ሚሊዮን ነዋሪዎች መካከል አብዛኞቹም ተፈናቅለዋል

የእስራኤል ጦር ከምሥራቃዊ የጋዛ ክፍል እንደሚወጣ እና የተፈናቀሉ ሰዎች ወደቀያቸው እንዲመለሱ እንደሚፈቀድላቸው ተገልጿል።

እስካሁን እስራኤል በጋዛ ውስጥ ባካሄደችው ጦርነት ከ46,700 በላይ ሰዎች መገደላቸው ሪፖርት ተደርጓል። ከጋዛ 2.3 ሚሊዮን ነዋሪዎች መካከል አብዛኞቹም ተፈናቅለዋል።

በእስራኤል መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ በጋዛ ከፍተኛ ውድመት ከመድረሱ ባሻገር የምግብ፣ የመድኃኒት፣ የነዳጅ አና የመጠለያ እጥረት ተከስቷል።

የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሼኽ መሐመድ ቢን አብዱል ራሕማን አል ታሕኒ እንዳሉት፣ የእርዳታ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ ሰርጥ እንዲገቡ ይፈቀዳል። ሆስፒታሎችም መልሰው ይገነባሉ።

ምን ያህል እርዳታ እንደሚገባ በግልጽ አልተነገረም።

አደራዳሪዎቹ ስምምነቱ ይጸናል ብለው ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል። "ሁሉም ወገኖች ስምምነቱን ያከብራሉ ብለን እናምናለን" ብለዋል።

የተኩስ አቁሙ 16 ቀናት ሲሞላው ሁለተኛው የድርድር ደረጃ ይተገበራል።

የእስራል ጦር መቼና እንዴት ግብፅ ድንበር ካለው የፈላደርፊ አካባቢ ጥሎ እንደሚወጣ አልታወቀም።

ሰልፍ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የትኞቹ ታጋቾች በሕይወት እንዳሉና ሐማስ በሕይወት ያሉት ታጋቾች የት እንደሚገኙ ስለማወቁ ግልጽ አይደለም

የስምምነቱ ሁለተኛ ክፍል

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እንዳሉት ሁለተኛው የስምምነት ክፍል "ጦርነቱ እስከወዲያኛው" የሚቆምበት ይሆናል።

ድርድሩ ከስድስት ሳምንት በላይ ከዘለቀ የተኩስ አቁሙም እንደሚቀጥል ባይደን ተናግረዋል።

በቀጣይ ወታደሮችና ንጹኃን ዜጎችን ጨምሮ ወንድ ፍልስጤማውያን እስረኞችን እስራኤል ትለቃለች።

እስራኤል በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን እስረኞችን እንደምትለቅ ብትገልጽም የፍልስጤም ባለሥልጣን ግን ከ1,000 ፍልስጤማውያን እስረኞችን ይለቀቃሉ ብለዋል።

ጋዛ

የፎቶው ባለመብት, Mahmoud Issa / Reuters

የምስሉ መግለጫ, በእስራኤል መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ በጋዛ ከፍተኛ ውድመት ከመድረሱ ባሻገር የምግብ፣ የመድኃኒት፣ የነዳጅ አና የመጠለያ እጥረት ተከስቷል

ከ15 ዓመታት በላይ እስራት የተፈረደባቸው ወደ 190 የሚጠጉ እስረኞች የሚለቀቁ ይሆናል።

የእስራኤል ባለሥልጣን እንዳሉት በግድያ የተፈረደባቸው እስረኞች ወደ ዌስት ባንክ አይለቀቁም።

የእስራኤል ወታደሮች በአጠቃላይ ከጋዛ ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። "ዘላቂነት ያለው ሰላም" ይጀመራል ተብሎም ይጠበቃል።

የእስራል ጦር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የእስራል ጦር መቼና እንዴት ግብፅ ድንበር ካው የፈላደርፊ አካባቢ ጥሎ እንደሚወጣ አልታወቀም

የስምምነቱ ሦስተኛ ክፍል፡ ጋዛን መልሶ መገንባት

የመጨረሻውና ሦስተኛው የስምምነቱ ክፍል ጋዛን መልሶ መገንባት ነው። ይሄም ዓመታት ይወስዳል።

ባይደን እንዳሉት በዚህ ወቅት ፍልስጤማውያን በጋዛ ሁሉም አካባቢዎች መመለስ ይችላሉ።

የታጋቾች አስክሬን እንደሚመለስም ተናግረዋል።

ጋዛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የትራምፕ ሚና ምንድን ነው?

ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ለስምምነቱ ሚና እንደነበራቸው ባይደን ጠቁመዋል።

በሁለቱም ወገኖች ላይ ጫና በማሳደር ስምምነቱ እንዲፈረም ትራምፕ ማስቻላቸው ተገልጿል።

ስምምነቱ መደረጉን ከኳታር እና ጆ ባይደን ጽህፈት ቤት ቀድመው ይፋ ካደረጉት መካከል ትራምፕ አንዱ ናቸው። ስምምነቱን "ታላቅ" ሲሉም ገልጸዋል።

"በኅዳር ምርጫ አስደናቂ ድል በማግኘታችን የመጣ ስምምነት ነው" ብለዋል ትራምፕ።

ታጋቾች እንዲለቀቁ የሚጠይቅ ሥነ ሥርዓት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ታጋቾች እንዲለቀቁ የሚጠይቅ ሥነ ሥርዓት

ኔታንያሁም ትራምፕ ታጋቾችን ለማስለቀቅ ባደረጉት ጫና አመስግነዋቸዋል።

የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳሉት ትራምፕ ካደረጉት ጫና ባሻገር ኳታር ባለፉት ወራት ስምምነት ላይ እንዲደረስ ከፍተኛ ግፊት አድርጋለች።

"እስካሁን ድረስ ከአሜሪካ ሲሰጥ የነበረው ድጋፍ ቀጥሏል" ብለዋል።

ሁለቱን ወገኖች በማቀራረብና ለስምምነቱ ተገዢ እንዲሆኑ በማስቻል ረገድ ባለፉት ቀናት አሜሪካ ሚና መጫወቷንም አክለዋል።

ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በሁለቱም ወገኖች ላይ ጫና በማሳደር ስምምነቱ እንዲፈረም ትራምፕ ማስቻላቸው ተገልጿል።

እንዴት ስምምነቱ ይተገበራል?

የእስራኤል ካቢኔ ዛሬ ድምጽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። ቀኝ ዘመም የፓርቲው አባላት ግን ስምምነቱን አውግዘዋል።

የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳሉት ለስምምነቱ ተፈጻሚነት የሁለቱ ወገኖች ቁርጠኛነት አስፈላጊ ነው።

ኳታር፣ አሜሪካ እና ግብፅ ስምምነቱ እንዲደረስ አግዘዋል። እስራኤል እና ሐማስ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚከታተሉም ይሆናል።

"ይህ የጦርነቱ ማብቂያ ነው ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ሁሉም ወገኖች ስምምነቱን ያከብራሉ ብለን እናምናለን" ብለዋል ሦስቱ አገራት።

የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሼኽ መሐመድ ቢን አብዱል ራሕማን አል ታሕኒ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሼኽ መሐመድ ቢን አብዱል ራሕማን አል ታሕኒ

ጋዛን ማን ይመራል?

ከጦርነቱ መገባደድ በኋላ ጋዛን ማን ይመራል? የሚለው ጥያቄ ምላሽ አላገኘም።

ከጦርነቱ በኋላ የፍልስጤም አስተዳደር ጋዛን የማስተዳደር ሥልጣን ያለው ብቸኛው አካል እንደሆነ የፍልስጤም ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ሙስጠፋ ተናግረዋል።

ይህን ያሉት የተኩስ አቁም ስምምነቱ እውን ከመሆኑ ቀድሞ ነው።

እስራኤል ሐማስ አካባቢውን እንዲመራ እንደማትፈቅድ ገልጻለች።

ጋዛ በፍልስጤም አስተዳደር እንዲመራም እስራኤል ፍላጎት የላትም። በዌስት ባንክ በግዳጅ የተያዙ ቦታዎችን የፍልስጤም አስተዳደር ይመራል።

እስራኤል ከጦርነቱ በኋላ የጋዛን ፀጥታ መቆጣጠር ትፈልጋለች።

ሆኖም ግን የፍልስጤም አስተዳደር ማስተካከያ እስከሚደረግበት በጋዛ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ከአሜሪካና ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጋር እየሠራች ነው።