የትራምፕ አስተዳደር አሜሪካን በድጋሚ ከዩኔስኮ አባልነት አስወጣ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካ፤ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅትን (ዩኔስኮ) "ከፋፋይ ባህላዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮችን" ይደግፋል በማለት ከስሳ፤ ኤጀንሲውን ለቅቃ እንደምትወጣ አስታወቀች።
የዩኔስኮ ዋና ዳይሬክተር ኦድሬ አዙሌይ ውሳኔውን "የሚያሳዝን" ሲሉ የገለጹት ሲሆን ነገር ግን "የሚጠበቅ" እንደነበረ ተናግረዋል።
ይህ እርምጃ የትራምፕ አስተዳደር አሜሪካ ከዓለም አቀፍ አካላት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማቋረጥ የወሰደው አዲስ እርምጃ ሆኑ ተመዝግቧል።
የፕሬዝዳንቱ አስተዳደር ከዚህ ቀደም ሀገሪቱን ከዓለም የጤና ድርጅት አባልነት እና ከፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነት ፈራሚነት ያስወጡ ሲሆን ለውጭ የእርዳታ ጥረቶች የሚደረገውን ድጋፍም ቀንሷል።
በዓለም ዙሪያ 194 አባል ሀገራት ያሉት ዩኔስኮ፤ የዓለም ቅርስ ቦታዎችን በመመዝገብ ስራው ይበልጥ ይታወቃል። ይህ የአሜሪካ ውሳኔ ከታህሳስ 2026 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሆን ተገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ የዩኔስኮ "ለዓለም አቀፋዊ የልማት አጀንዳ ያለው ዓለም አቀፋዊነት፣ ርዕዮተ ዓለም"፤ "ቅድሚያ ለአሜሪካ [ከሚለው] የውጭ ፖሊሲያችን ጋር የሚጋጭ ነው" ብሏል።
እ.አ.አ በ2011 ፍልስጤማውያን ዩኔስኮ ውስጥ እንዲካተቱ መደረጋቸውንም በምክንያትነት ያነሳው ሚኒስቴሩ፤ ይህንን ውሳኔ "በጣም ችግር ያለበት፣ ከአሜሪካ ፖሊሲ ጋር የሚቃረን እና በድርጅቱ ውስጥ ፀረ-እስራኤል ንግግሮች ለመስፋፋቱ አስተዋጽኦ ያበረከተ ነው" በማለት ከስሷል።
የተቋሙ ኃላፊ ኦድሬ አዙሌይ ግን እነዚህ ወቀሳዎች "የዩኔስኮን ጥረት፤ በተለይም በሆሎኮስት ትምህርት እና ፀረ-ሴማዊነትን በመዋጋት ረገድ [ያለውን] እውነታውን የሚቃረኑ ናቸው" ሲሉ አጣጥለዋል።
"ይህ ውሳኔ የሀገራት ትብብር መሰረታዊ መርሆዎችን የሚቃረን እንዲሁም ስፍራዎቻቸው ፈጠራ የተሞላበት ከተማ ደረጃን አግኝተው በዓለም ቅርስ ዝርዝር ውስጥ እንዲመዘገቡ የሚፈልጉ በአሜሪካ የሚገኙ ማህበረሰቦችን እና የዩኒቨርሲቲ አመራሮችን በዋነኛነት ሊጎዳ ይችላል" ብለዋል።
ዩኔስኮ ይህንን የዋሽንግተንን እርምጃ በተመለከተ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን የገለጹት ኃላፊዋ፤ ተቋሙ የገንዘብ ምንጮቹን በማስፋት ላይ መሆኑን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ዩኔስኮ 8 በመቶ የሚሆነውን በጀቱን የሚያገኘው ከአሜሪካ እንደሆነም አክለዋል።
ትራምፕ፤ እ.አ.አ በ2017 በመጀመሪያ ፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው ወቅት በተመሳሳይ አሜሪካን ከዩኔስኮ አባልነት አስወጥተው የነበረ ቢሆንም የባይደን አስተዳደር ወደ ስልጣን ሲመጣ ውሳኔው ተቀልብሷል።
በ2011፣ በኦባማ አስተዳደር ጊዜ፤ አሜሪካ ለዩኔስኮ የመደበችው 60 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ እንዳይተላለፍ አግዳ ነበር።
በወቅቱ የነበሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፤ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት፤ ዩኔስኮ ለፍልስጤም የሙሉ አባልነት ባለስልጣን መስጠቱን ተከትሎ አሜሪካ ለተቋሙ ገንዘብ እንዳታስተላልፍ በሚከለክል የሀገሪቱ ህግ እጃቸውን ተጠምዝዘው መሆኑን ተናግረው ነበር።
መቀመጫውን ፓሪስ ያደረገው ይህ የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲ የተቋቋመው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅ በኋላ እ.አ.አ በህዳር 1945 ነው።
ተቋሙ የተመሰረተው በትምህርት፣ በኪነጥበብ፣ በሳይንስ እና በባህል ዓለም አቀፍ ትብብር፤ ሰላምን እና ደህንነትን የማስተዋወቅ ዓላማን ይዞ ነው።















