'ታዳጊዎችን በወሲብ ንግድ ካሰማራው' ኤፕስቴይን ጋር የተጠቀሱት ትራምፕ ዋል ስትሪት ጆርናልን ከሰሱ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ታዳጊዎችን በወሲብ ንግድ ማሰማራት ጨምሮ በሌሎች ወሲባዊ ወንጀሎች ክስ ተመስርተውበት የነበረው ጄፈሪ ኤፕስቴይን ጋር የነበራቸውን ጓደኝነት አስመልክቶ ባወጣው ዘገባ ዋል ስትሪት ጆርናል እና ባለቤቱን ሩፐርት መርዶክን ከሰሱ።

ዶናልድ ትራምፕ ባቀረቡት "የስም ማጥፋት ክስ" ቢያንስ 10 ቢሊዮን ዶላር የጉዳት ካሳ እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል።

በኤፕስቴይን ዙሪያ ያለው ቅሌት የበለጠ እንዳይዛመት እና የፖለቲካ ዋጋ እንዳያስከፍላቸው በመከላከል ላይ ያሉት ትራምፕ ክሳቸውን አርብ ዕለት በፍሎሪዳ በሚገኘው የፌደራል ፍርድ ቤት አቅርበዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ከስድስት ዓመታት ገደማ በፊት በእስር ቤት የራሱን ሕይወት ያጠፋው የጄፌሪ ኤፕስቴይንን ጉዳይ የያዘበት መንገድ ከፍተኛ ትችት መቅረቡን ተከትሎ የአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ዳኞች የክሱን ሰነዶች ይፋ እንዲያደርጉ ውሳኔ ሰጥቷል።

በኤፕስቴይን ላይ ለወሲብ ንግድ ታዳጊዎችን በሕገወጥ መንገድ በማዘዋወር እና ታዳጊዎችን በወሲብ ንግድ ማሰማራት መንግሥት ያቀረበው የ2019 ክስ ግልባጭ የሚመለከት ሲሆን፣ እነዚህ ሰነዶች አብዛኛውን ጊዜ በምሥጢር የሚያዙ እና በሕግም ጥበቃ የሚደረግላቸው ናቸው።

ይህ ውሳኔ የመጣው ትራምፕ በአውሮፓውያኑ 2003 ለኤፕስቴይን "ወሲባዊ ቀልድ" ይዘት ያለው የግል ማስታወሻ ጽፈዋል በሚል ዋል ስትሪት ጆርናል ማስነበቡን ተከትሎ በህትመቱ፣ ባለቤት በሆነው ኩባንያው ዶው ጆንስ፣ በባለቤቱ በሩበርት መርዶክ እና ሁለት ጋዜጠኞች ላይ ክስ መመሥረታቸውን ተከትሎ ነው።

ትራምፕ ለኤፕስቴይን 50ኛ የልደት በዓል ልከውታል ብሎ ጋዜጣው የዘገበው ማስታወሻ "ሐሰት" ነው ብለዋል።

ኤፕስቴይን በወሲባዊ ወንጀሎች ከመከሰሱ በፊት ነው ትራምፕ ማስታወሻውን ልከውለታለል የተባለው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዶው ጆንስ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ በላከው መግለጫ "በሪፖርታችን ጥንካሬ እና ትክክለኛነት ሙሉ እምነት አለን፤ እናም ማንኛውንም የሚቀርብብን ክስ አጥብቀን እንከላከላለን" ብሏል።

ሐሙስ ዕለት ትራምፕ በኤፕስቴይን ከቀረቡ ምሥጢራዊ ምስክርነቶች ጋር የተያያዙ ሰነዶች ይፋ እንዲሆኑ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፓም ቦንዲን አዘዋል።

ኤፕስቴይን የ14 ዓመትን ጨምሮ በርካታ ታዳጊዎችን ለወሲብ ንግድ በሚል በሕገወጥ መንገድ በማዘዋወር የተከሰሰበት የወንጀል ክስ "ለሕዝብ ጥቅም" ይፋ መሆናቸው አስፈላጊ መሆኑን የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ በኒው ዮርክ ለሚገኝ ዳኛ ጥያቄውን አቅርቧል።

የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሕጻናት የወሲብ ንግድ ሴራ ጋር ክስ የቀረበባት የኤፕስቴይን ባልደረባ ጊዝላኔ ማክስዌል ሰነዶች ይፋ እንዲደረግ እየጠየቀ ነው።

በአሜሪካ 'ግራንጅድ ጁሪ' የሚሰኘው ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍል የተውጣጡ ግለሰቦች ሲሆኑ፣ አንድን ሰው በወንጀል ለመክሰስ በቂ ማስረጃ መኖሩን ከማጣራት በተጨማሪ በምሥጢር መረጃ ይቀበላሉ እንዲሁም ለደኅንነታቸው ሲባል ማንነታቸው ይፋ ከማይሆኑ ሰዎችም ምስክርነትን ይቀበላሉ።

በዚህ 'ግራንድ ጁሪ' የሚቀርቡ ሰነዶች በሕጉ መሠረት በምሥጢር የሚጠበቁ ቢሆንም ነገር ግን ለብሔራዊ ጥቅም ሲባል እነዚሀ የህግ ከለላዎች የሚነሱ ይሆናል።

ያም ሆነ ይህ እነዚህ ሰነዶች መቼ ይፋ እንደሚሆኑ ወይም የትራምፕ ደጋፊዎች የሚጠይቋቸውን በርካታ ዝርዝሮች ስለማካተታቸው ግልጽ አይደለም።

ጄፈሪ ኤፕስቴይን ለአስርት አመታት ያህል ታዳጊዎችን በወሲብ ንግድ አሰማርቷል በሚል ክስ ቀርቦበት የፍርድ ውሳኔም ሳያገኝ ራሱን አወዛጋቢ በሆነ መልኩ በአውሮፓውያኑ 2019 አጥፍቷል መባሉ ይታወሳል።

ግለሰቡ አስራ ስምንት ዓመት ያልሞላቸውን ታዳጊዎች እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2002-2005 በማንሃተን እና በፍሎሪዳ በሚገኘው ቤቱ እየከፈለ በወሲብ ንግድ ላይ አሰማርቷቸዋል የሚል ክስ ቀርቦበት ነበር።

ጄፈሪ ከአስራ ሰባት ዓመት በፊት አነጋጋሪ በተባለው ምሥጢራዊ ስምምነት ጥፋተኛ መሆኑንም አምኖ ክሱን ማስቀረት ችሏል ተብሎ ነበር።

ይህ ምስጢራዊ ስምምነት ከስድስት ዓመታት በፊት አነጋጋሪ የነበረ ሲሆን በወቅቱም የቀድሞው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አሌክስ አኮስታ በፈቃዳቸው ከሥልጣናቸው መልቀቃቸው ይታወሳል።

ጀፍሪ ኤፕሰትን ጥፋተኛ ሆኖ ቢገኝ ኖሮ 45 ዓመታት እስር ይጠብቀው ነበር።

ኒውዮርክ የተወለደው ጄፈሪ ኤፕስቴይን ወደ ንግዱ ዓለም ከመቀላቀሉ በፊት መምህር ነበር።

ከቀረበበት የወንጀል ክስ በተጨማሪ ከቱጃሮች እና ከባለሥልጣናት ጋር ባለው ግንኙነት ይታወቃል።

ከእነዚህም መካከል የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን እና የእንግሊዙ ልዑል አንድሪው ጋር በተለያዩ አጋጣሚዎችም ይታያል ተብሏል።

በአውሮፓውያኑ 2002 ዶናልድ ትራምፕ ኤፕስቴይን ለአስራ አምስት ዓመታት ጓደኛቸው እንደሆነ እና "አስደናቂ ሰው ነው፤ እንደኔ ቆንጆ ሴቶችን ይወዳል፤ እሱ እንዳውም በዕድሜ አነስ ያሉትን" ሲሉ መናገራቸውን የኒው ዮርክ ማጋዚን አስነብቧል።

ነገር ግን ፕሬዚዳንቱ ቃላቸውን አጥፈው የኤፕስቴይን አድናቂ እንዳልሆኑ እና ከአስር ዓመታትም በላይ አውርተው እንደማያቁ ከዚህ ቀደም ተናግረዋል።