ትራምፕ የደም ሥር ችግር እንዳጋጠማቸው ዋይት ሐውስ አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በደም ሥር የጤና እክል እንደታመሙ ዋይት ሐውስ ለቀናት እጃቸው ላይ የተከሰተው ጠባሳ መነጋገሪያ ከሆነ በኋላ አስታወቀ።
በቅርቡ እግራቸው ላይ እብጠት መከሰቱን ተከትሎ ትራምፕ የደም ቧንቧ ምርመራን ጨምሮ "አጠቃላይ የጤና ምርመራ" ማድረጋቸውን የዋይት ሐውስ የፕሬስ ሴክሬታሪያት ካሮላይን ሌቪት ተናግረዋል።
ኃላፊዋ ትራምፕ እጅ ላይ የተከሰተው ጠባሳ "የተለመደ የልብ እና የደም ሥር መከላከያ ዘዴ" የሆነውን አስፕሪን እየወሰዱ "በተደጋጋሚ እጅ በመጨባበጣቸው የደረሰ የሕብረ ሕዋስ ጉዳት" ነው ብለዋል።
የ79 ዓመት እድሜ ያላቸው ትራምፕ ስለ መልካም ጤናቸው በተደጋጋሚ የሚያነሱ ሲሆን፤ በአንድ ወቅት "በሕይወት ከኖሩ ፕሬዝዳንቶች ጤናማው ነኝ" በማለት ራሳቸውን ገልፀዋል።
ፕሬዝዳንቱ የገጠማቸው የእግር የደም ሥሮች ወደ ልብ መላክ ያለባቸውን ደም ማሰራጨት ሳይችሉ ሲቀር የሚከሰተው 'ሥር የሰደደ የደም ሥር እጥረት' ( chronic venous insufficiency) የተባለ የጤና እክል ሲሆን ይህም እጅ እና እግር ላይ እብጠት ሊያስከትል ይችላል።
በቴክሳስ ዩኒቨርስቲ የደም ቧንቧ ቀዶ ሕክምና ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት መሪል ሞርጋን ለቢቢሲ የደም ቧንባዎች እና ቫልቮች "ወደ እግር ደም እንዲወርድ እና እንዲወጣ" ያደርጋሉ ብለዋል።
ከእግር ወደ ልብ የሚጓዘው ደም የስበት ኃይል ሳይገድበው መንቀሳቀሱ ሂደቱን የበለጠ አስቸጋሪ ያደርገዋል።
"ሥር የሰደደ የደም ሥር እጥረት ማለት የደም ቧንባዎች እና ቫልቮች መስራት ሳይችሉ ሲቀር እና ደም መልሶ ወደ እግር ሲሄድ ነው" ብለዋል።
"ጥልቅ የደም ቧንቧ ችግር ወይም የደም ቧንቧ በሽታ" እንዳልሆነ የተናገሩት የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪያት የምርመራ ውጤቶች "መደበኛ ገደብ ውስጥ" የሚገኙ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
የዋይት ሐውስ ሐኪም የሆኑት ሿን ባርቤላ ለጋዜጠኛች ይፋ ባደረጉት የማስታወሻ ጽሑፍ እክሉ በተለይም በ70ዎቹ የእድሜ ክልል ላይ ባሉ ሰዎች "የተለመደ ነው" ነው ብለዋል።
ለትራምፕ የተደረጉ ተጨማሪ ምርመራዎች የልብ ድካም፣ የኩላሊት ሕመም ወይም ሌሎች ሕመሞችን መኖራቸውን አላሳዩም ያሉት ሐኪሙ፤ የፕሬስ ሴክሬታሪያት አስቀድሞው ያሳወቁትን መረጃ አጠናክረዋል።
ሐኪሙ በአጠቃላይ ትራምፕ "በጣም ጥሩ ጤንነት" ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት በተደረገው የፊፋ የክለቦች የዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ላይ ትራምፕ ያበጠ እግራቸውን የሚያሳዩ ምስሎች ይፋ ሆነዋል።
ከቀናት በፊትም የባሕሬንን ጠቅላይ ሚኒስትር ሲያገኙ እጃቸው ላይ ጠባሳ ታይቷል።
ይህ ጠባሳ ከዚህም ቀደም ብሎ ባለፈው የካቲት ወር ትራምፕ የፈረንሳዩን ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን ሲያገኙ በፎቶ አንሽዎች ዕይታ ውስጥ ገብቶ ነበር።
ያበጠው እግራቸው እና የእጃቸው ጠባሳ ፕሬዝዳንቱ ይፋ ባልሆነ ሕመም እየተሰቃዩ ነው በሚል የበይነ መረብ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል።
ባለፈው ሚያዚያ ባካሄዱት አጠቃላይ ምርመራ በመልካም የኮግኒቲቭ (እውቀት) እና አካላዊ ጤና መሆናቸውን ሐኪማቸው ጽፈው ነበር።
ትራምፕ ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመናቸው ቃለ መሀላ ሲፈፅሙ 78 ዓመት ከሰባት ወር እድሜ ላይ የነበሩ ሲሆን፤ ይህም በእድሜ ትልቁ የዩናይትድ ስቴት መሪ አድርጓቸዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሕክምና ባለሙያዎች የትራምፕ ሐኪም ባቀረቡት ሥር የሰደደ የደም ሥር እክል ይስማማሉ።
በዌክ ፎረስት ዩኒቨርስቲ የደም ቧንቧ ቀዶ ሕክምና ትምህርት ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ማቲው ኤድዋርድስ "ከከባድ ሕመም ጋር ሊያያዝ ይችላል። ነገር ግን ብቻውን የሚያሰጋ አይደለም" በማለት የተለመደ እክል መሆኑን ገልፀዋል።
በተለይም በትራም የእድሜ ክልል ላይ ባሉ ከ10 እስከ 35 በመቶው በሚሆኑ ሰዎች ላይ የሚከሰት የጤና እክል መሆኑን ተናግረዋል።
ባለሙያዎች የጤና እክሉ ከፍተኛ ክብደት፣ የደም መርጋት ታሪክ ባላቸው እና ለረጅም ሰዓታት በመቆም ስራዎችን የሚሰሩ ሰዎች ላይ ይከሰታል ይላሉ።















