የዓለማችን የሃብት እና የፖለቲካ ኃያላን ፍጥጫ በማን አሸናፊነት ይቋጭ ይሆን?

ኤለን መስክ እና ዶናልድ ትራምፕ
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ገንዘብ የማይገዛው ነገር የለም፤ የማያሽከረክረው የዓለም ፖለቲካ አይኖርም። በአሜሪካ የምርጫ ፖለቲካ ውስጥ ደግሞ ገንዘብ የእናት ጡት ወተት ማለት ነው።

ኤሎን መስክ በመቶዎች ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላሩን ያፈሰሰው ከራሱ ይልቅ ሌላ ሰው ወደ ሥልጣን እንዲመጣ ነው።

ዶናልድ ትራምፕን ለሁለተኛ ጊዜ የፕሬዝዳንትነት ሥልጣኑን እንዲቆጣጠሩ ለመደገፍ ከ250 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ አድርጓል። በምትኩም ለፕሬዝዳንቱ ቅርብ መሆን ብቻ ሳይሆን ወሳኝ የሆነ ውሳኔን ያሳለፈ ሥልጣንም ጨብጦ ነበር።

ነገር ግን በሁለቱ ወዳጃሞች መካከል ንፋስ የገባው ትራምፕ ሥልጣን ከያዙ በወራት ውስጥ ነው። በዚህም ምክንያት መስክ ከፍተኛ ድርሻ ያለው ቅንጡ የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ኩባንያ ቴስላ የአክሲዮን ድርሻ በፍጥነት አሽቆልቁሏል።

መስክ ከትራምፕ ጋር ወዳጅነታቸው ከሻከረ በኋላ ራሳቸውን እና በንግድ ሥራዎቻቸው ላይ መዋዕለ ነዋያቸውን ያፈሰሱትን በሙሉ ለአደጋ አጋልጠዋል።

የዓለማችን ኃያል አገር ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የዓለማችን ቁጥር አንድ የሃብት ባለቤት ቢሊየነሩ ኢሎን መስክ ፀብ ተካርሮ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እንካ ሰላንትያ ገጥመዋል።

ይህ አለመግባባት ተካርሮ መስክን በአሜሪካ ለዘመናት የቆየውን የሁለት ፓርቲዎች የበላይነት ያበቃል ያለውን አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ መሥርቻለሁ እስከ ማለት ደርሷል።

ይህም በዓለም እጅግ ሃብታም የሆነው ሰው እና የምድራችን ከፍተኛውን ሥልጣን በጨበጡት ሰው መካከል እፍ ያለ ፍቅር ሲመሠረት ሊፈጠር የሚችለውን አደጋ አመልክቷል።

መስክ የፕሬዝዳንቱ የቅርብ አጋር በነበረበት ወቅት አስተደደራቸው የአሜሪካ መንግሥት ወጪዎችን ለመቀነስ በሚወስደው እርምጃ ላይ ቀዳሚ በመሆን ተሰልፏል።

በዚህም በዓለም ዙሪያ በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ የአሜሪካ መንግሥት ተቋማትን የገንዘብ አቅም መቀነስ እንዲሁም አስከ መዝጋት የደረሰ ውሳኔን መስክ አስተላልፏል።

ትራምፕም ይህንን የመስክን እርምጃ "ጎሽ" ከማለት አልፈው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሲያንቆለጳጵሱት በሄዱበት ሁሉ በፕሬዝዳንታዊ አውሮፕላናቸው ይዘውት ሲሽከረከሩ ቆይተዋል።

ነገር ግን የሁለቱ የዓላማችን ኃያላን ወዳጅነት ከወራት አልዘለቀም። የፕሬዝዳንቱ አዲስ ሃሳብ መስክን አስኮርፎት ነገሮች አደባባይ ወጡ።

መስክ የቅርብ ወዳጁ ትራምፕ ላይ ፊቱን ያጠቆረው፣ ድምፁን ከፍ አድርጎ መናገር የጀመረው ፕሬዝዳንቱ "ትልቅ እና ቆንጆ" ያሉት የበጀት ሕግን ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው።

ከዚህ በኋላ መስክ ከተሾመበት የሥራ ቅልጥፍና ቢሮ ሥልጣኑ ሲለቅ፣ ዋይት ሐውስ በፈገግታ ቢሸኘውም ከፕሬዘዳንቱ ጋር ግን በነገር መጠዛጠዝ እንዲሁም ተቀናቃኝ ፓርቲ መመሥረት ውስጥ ገብቷል።

የቀድሞው ትዊተር የአሁኑ ኤክስ ባለቤት መስክ እንዲሁም ትሩዝ የተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ያላቸው ትራምፕ በየበኩላቸው እንኪያ ሰላምታቸውን በማኅበራዊው ሚዲያ ላይ አሰጡት።

ኤለን መስክ እና ዶናልድ ትራምፕ በዋይት ሐውስ ቢሯቸው ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እንደ ፎርብስ መረጃ ከሆነ የኤለን መስክ ሃብት 400 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል።

በአውሮፓውያኑ 2002 ሥራ የጀመረው የመስክ ንብረት የሆነው ስፔስ ኤክስ እስካሁን በርካታ ነገሮችን አሳክቷል። የሩቅ ዓላማው የሰው ልጅ በሌላ ፕላኔት መኖር እንዲችል ማድረግ ነው።

ይህንን ዓላማውን ለማሳካትም ከናሳ ጋር የቢሊዮን ዶላሮች የንግድ ስምምነት አለው።

ኢሎን መስክ ከቴስላ በተጨማሪ ፔይ ፓል የተባለውን የክፍያ ዘዴን ከጀመሩት አንዱ ነው። ታዋቂወን የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ትዊተርን በ44 ቢሊዮን ዶላር በመግዛት የግል ንብረቱ ካደረገ በኋላ ኤክስ ሲል ሰይሞታል።

በትዊተር ላይ በሚያሰፍሯቸው አወዛጋቢ አስተያየቶች የተነሳ ታግደው የነገሩት ትራምፕን ነጻ አውጥቷቸዋል። በተጨማሪም ትዊተርን (ኤክስ) ለፕሬዳንቱ እና ለደጋፊዎቻቸው የሚመች የማኅበራዊ ሚዲያ አድርጎታል።

አዳዲስ ነገሮችን ለመሞከር ሚሊዮን ዶላሮችን የሚያፈሰው መስክ የሳይንስ ልቦለድ የፈጣራ ፊልሞች ፊልም ብቻ ሆነው መቅረት የለባቸውም ብሎ ያምናል።

የሳይንስ ፈጠራ ፊልሞችን ልንኖራቸው፣ ልንፈጥራቸው ካልቻልንማ ቅዥቶች ሆኑ ማለት ነው ይላል።

ከትራምፕ ጋር ባዳበረው የቅርብ ወዳጅነት ንብረቱ የሆነው ቴስላ የሚያመርታቸው የኤሌክትሪክ መኪኖች ገበያን የሚያጠናክር እርምጃ የአሜሪካ መንግሥት እንዲወስድ ፍላጎት ነበረው።

በተጨማሪም ከመንግሥት በቢሊዮኖች ዶላር የሚገመት ድጋፍ እና የታክስ ማበረታቻ ያገኛል ተብሎ ሲጠበቅ ነው ትራምፕ አዲስ የበጀት ሕግ ያስተዋወቁት።

ይህም ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ያለው አለመግባባት ከማካረር አልፎ ሕልሙን ቅዠት ሳያደርግበት አይቀርም።

መስክ ይህንን የፕሬዝዳንቱን እርምጃ ጠንከር ባሉ ቃላት በመተቸት ፍጥጫውን በማባባሱ ትራምፕ የቀረውንም የአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ ከማቋረጥ ባሻገር ከአሜሪካም ሊያባርሩት እንደሚችሉ እስከመናገር ደርሰዋል።

እንዲሁም የአሜሪካ መንግሥት አባካኝ ወጪዎችን ለመቀነስ በሚል ተቋቁሞ በራሱ በመስክ ሲመራ የነበረው መሥሪያ ቤት ፊቱን በመስክ ላይ እንዲያዞር በማድረግ ሊቀጡትም እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

ይህ ደግሞ ትክክለኛው የኃይል ሚዛን በየት በኩል እንዳለ ያሳያል።

የሮይተርስ የዜና ወኪል የአሜሪካ መንግሥት ከመስክ ስፔስ ኤክስ ጋር 22 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የንግድ ስምምነቶች ተፈራርሟል ሲል ዘግቧል።

ከቻይና ጋር ጥብቅ የንግድ ግንኙነት ያለው ቴስላ ባለፈው ዓመት ብቻ ለአገሪቱ አምስተኛ ደረጃን የያዘ ገቢን ማስገባት ችሏል።

ይህ ደግሞ ከቤይጂንግ ጋር በንግድ ጦርነት ውስጥ ያሉት የፕሬዝዳንት ትራምፕ ቁጣ ላይ ውሃ ሊቸልስ ይችላል።

የፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ አጸፋም እንዲሁ አሜሪካ በቀላሉ የምትቋቋመው አይደለም። በዚህ መካከል የመስክ ኩባንያዎች የሚደርስባቸው ኪሳራ በቀላሉ የሚገመት አይሆንም።

የአሜሪካ መንግሥት እንደዛተው ለመስክ ፕሮጀክቶች የሚያደርገውን ድጎማ፣ ከናሳ ጋር ያለውን የቢሊዮኖች የንግድ ሥምምነት የሚያቋርጥ ከሆነ ደግሞ የኢለን መስክ ሃብት ያሽቆለቁላል።

እርሱን አምነው፣ የንግድ ሃሳቡን አዋጪነት መዝነው ገንዘባቸውን ፈሰስ ያደረጉ ባለሃብቶች ደግሞ ኪሳራን ይከናነባሉ።

መስክ ያለምንም ትግል መውደቅ አልፈለገም። እስከ መጨረሻው ድረስ የመፋለም አቋም ያለው ይመስላል።

በእርግጥ ይህ ትግል በመላላጥ ብቻ የሚወጣው እንዳልሆነ ያውቃል።

መስክ እና ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, መስክ እና ትራምፕ በፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት

መስክ ታዳሽ ኃይልን የሚደግፉ ዲሞክራቶችን መወዳጀት ጀምሯል። በዚህም የትራምፕ ደጋፊዎች እንዲሁም ሪፐብሊካንን ፍርሃት ሊነዛባቸው ይችላል።

የስፔስ ኤክስ ጉዳይ ደግሞ በቀጥታ የሚጎዳው የናሳ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችን ነው።

በእርግጥ ለሰው ሠራሽ አስተውሎት ምርምሩ ገንዘብ ላያገኝ፣ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር ያለውን የንግድ ስምምነት ላያስጠብቅ ይችላል።

መስክ እስካሁን የገጠሙትን እክሎች እያለፈ የንግድ ኢምፓየሩን የገነባ ቢሆንም፤ ከዚህ በኋላ የሚገጥመውን የገንዘብ ተግዳሮት እንዴት ይወጣው ይሆን?

መስክ ከፕሬዝዳንቱ ጋር ባለመግባባት ከተለያየ በኋላ በአሜሪካ ሪፐብሊካን እና ዲሞክራቲክ ፓርቲን የሚገዳደር ሦስተኛ የፖለቲካ ፓርቲ የመመሥረት ሀሳብን ይዞ ብቅ ብሏል።

ይህ ደግሞ የመስክ እና የተራምፕ ግብግብ ከንግድ እና ከገንዘብ ባሻገር ወደ አሜሪካ የፖለቲካ መድረክም ሊሸጋገር ይችላል።

ይህ ትራምፕን ላመብሸቅ በመስክ መመሥረቱ የተነገረለት "ዩኒ ፓርቲ" የተባለ የፖለቲካ ፓርቲ በዘመናት የአሜሪካ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የበላይነቱን ተቆጣጥረው የመንግሥት ሥልጣንን እየተቀባበሉ ሲመሩ የቆዩትን አንጋፋዎቹን ፓርቲዎች የሚፎካከር ነው ተብሏል።

መስክ እንዳሰበው አዲሱ ፓርቲው እንሚጠብቀው ተፎካካሪ መሆን ይችል እንደሆነ በጊዜ ሂደት የሚታይ ቢሆንም፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን የቀድሞ የቅርብ አጋራቸው አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመሥረት ማቀዱን "አስቂኝ" ሲሉ ተሳልቀውበታል።

የዓለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር እና የፕሬዝዳንት ትራምፕ ቁልፍ ሰው የነበረው ኢለን መስክ ፕሬዝዳንቱ ያጸደቁትን የግብር እፎይታ ሕግ ከተቸ በኋላ ነው ከአስተዳደራቸው ራሱን ያገለለው።

መስክ በሺዎች የሚቆጠሩ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች የተባረሩበት ዶጅ እየተባለ የሚጠራው የአሜሪካ የብክንት ቅነሳ መሥሪያ ቤት ለአራት ወራት በኃላፊነት መርቷል።

መስክ ያለ እርሱ ድጋፍ ዶናልድ ትራምፕ "ምርጫውን ሊሸነፉ አይችሉም ነበር" ሲል ተናግሯል።

ትራምፕ በበኩላቸው ለዚህ ንግግሩ ምላሽ ሲሰጡ "ገንዘብ ለመቆጠብ ቀላሉ መንገድ" አስተዳደራቸው "ከመስክ ኩባንያዎች ጋር የገባውን የንግድ ስምምነቶችን እና የሚሰጣቸውን ጎማዎች፣ ለሮኬት ኩባንያው ስፔስ ኤክስ ጨምሮ፣ ማቋረጥ" መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንን እሰጥ አገባ ተከትሎ የቴስላ የአክሲዮን ገበያ ድርሻ በከፍተኛ ደረጃ አስቆልቁሏል።

በቅርቡ ሕግ ሆኖ የጸደቀው የፕሬዝዳንቱ የግብር እና ወጪ ዕቅድ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የነበረውን የግብር እፎይታ እንዲያከትም አድርጎታል።

የግብር እፎይታውን በዋነኝነት የሰረዙበትን ምክንያት ያብራራሩት ትራምፕ ቀድሞውኑ መስክ ያቀረበውን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ትዕዛዝ (Electric Vehicle mandate) ከጅምሩ መቃወማቸውን አክለዋል።

"ሰዎች የፈለጉትን መኪና፤ በቤንዚን፣ በናፍጣ የሚሠራ ወይም ሌሎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ሲመጡ መግዛት ይችላሉ። ከአሁኑ በኋላ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ትዕዛዝ የሚባል የለም" ብለዋል።

በቅርቡ የጸደቀው በጀት ለድንበር ቁጥጥር፣ ለመከላከያ እንዲሁም ለኃይል ምርቶች ጭማሪ ያደረገ ሲሆን፣ በአወዛጋቢ ሁኔታም የጤና አጠባበቅ እና የምግብ ድጋፍ መርሃ ግብሮችን በጀት ቀንሷል።

ምንም እንኳን በሁለቱ ኃያላን መካከል ያለው አለመግባበት እንዲህ ቢጦዝም፣ መስክም አዲስ ፓርቲ መሥርቻለሁ እያለ ቢያስፈራራም፣ እስካሁን ለፌዴራል ምርጫ ኮሚሽን ፓርቲውን ለማስመዝገብ መደበኛ ሂደት ስለመጀመሩ ግልፅ የሆነ ነገር የለም።

ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ከተመለሱ ከጥር ወዲህ ዩኤስኤይድን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት ተቋማት አባካኝ ናቸው በሚል አቅማቸውን ቀመቀነስ አንስቶ አስከ መዝጋት የደረሰ ውሳኔ ሲያሳልፍ ቆይቷል።

አሁን ደግሞ የተራው የእርሱ የሆነ ይመስላል፤ በዋይት ሐውስ ውስጥ በፕሬዝዳንት ትራምፕ የነበረው ሞገስ ተገፍፎ፣ ኩባንያዎቹ ከአሜሪካ መንግሥት የሚያገኙት ድጋፍ ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ከሪፐብሊካኑ መንግሥት ተሰናብቷል።

ነገር ግን የዓለምችን ቁጥር አንድ ባለጸጋው መስክ ከምድራችን ኃያሉ ፖለቲከኛ ጋር የጀመረውን እስጥ አገባ በቀላሉ በተሸናፊነት ለማብቃት አልፈለገም። በዚህም የትራምፕን ሥልጣን እና ክብርን የሚገዳደሩ እርምጃዎችን ለመውሰድ የቆረጠ ይመስላል።

ከእነዚህም መካከል ውዝግብ እና ክስ የማያጣቸው ፕሬዝዳንቱን የሚመለከት ከበድ ያሉ ምሥጢሮችን ይፋ እንሚያደርግ እንዲሁም ፓርቲ መሥርቶ ወደ ሥልጣን መውጣትን አንድ አማራጭ አድርጎታል።

በሁለቱ ዝሆኖች ፍልሚያ ማን ያሸነፍ ይሆን?

ኤሎን መስክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images