ኤሎን መስክ በዓለም ታሪክ ከፍተኛው ኪሳራ የደረሰበት ግለሰብ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኤሎን መስክ በአጭር ጊዜ ውስጥ በግል ሀብቱ ላይ በታሪክ ከፍተኛው ኪሳራ የደረሰበት ግለሰብ በመሆን የዓለምን ክብረወሰን መስበሩ ተነገረ።
የዓለም ክብረ ወሰኖችን የሚመዘግበው ‘ጊነስ ዎርልድ ረከርድስ’ በድረገጹ ላይ እንዳሰፈረው መስክ በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ አንድ ዓመት ውስጥ ብቻ 165 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ሀብት በኪሳራ አጥቷል።
ይህ የኪሳራ አሃዝ የተገኘው ፎርብስ የተባለው መጽሔት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት ሲሆን፣ ጊነስ እና ሌሎች ምንጮች እንደሚሉት ግን መስክ የገጠመው ኪሳራ ከዚህም ከፍ ሊል ይችላል።
መስክ በተጠናቀቀው የፈረንጆች ዓመት ላይ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኩን ትዊተርን መግዛቱን ተከትሎ የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ኩባንያው የቴስላ የአክሲዮን ዋጋ ወድቋል። በዚህም ነው ከፍተኛው ኪሳራ የተመዘገበው።
መስክ 44 ቢሊዮን ዶላር በመክፈል ትዊተርን ሲገዛ በዘመናዊው መኪና አምራች ድርጅቱ ቴስላ ውስጥ ያሉ ባለድርሻዎች፣ መስክ ለኩባንያው የሚያስፈልገውን ትኩረት አይሰጠውም የሚል ስጋት ፈጥሯል። ይህም የቴስላ የአክስዮን ዋጋው ላይ ኪሳራ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል።
ካለፈው ዓመት ኅዳር ወዲህ መስክ የገጠመው ኪሳራ አስካሁን በዓለም ላይ በግለሰብ ደረጃ የተመዘገበውን ክስረት በከፍተኛ መጠን የሚበልጥ ሆኗል።
ከመስክ ኪሳራ በፊት ከፍተኛው ተብሎ ተመዝግቦ የነበረው በአውሮፓውያኑ 2000 ላይ ጃፓናዊው የቴክኖሎጂ ባለሀብት ማሳዮሺ ሰን ያጋጠመው የ58.6 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ነበር።
የኤሎን መስክ ኪሳራ የተሰላው ዋጋቸውን ባጡት የኩባንያው አክሲዮኖች ሲሆን፣ የመዋዕለ ነዋይ አፍሳሾች እምነት ከተሻሻለ እና በተገቢው ዋጋ ድርሻዎቹን መግዛት ከፈቀዱ ግን ካጋጠመው ኪሳራ መልሶ ሊያገግም ይችላል።
የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለሀብት ሆኖ የቆየው መስክ ባለፈው ታኅሣሥ ወር በፈረንሳያዊው የፋሽን እና የቅንጦት እቃዎች አምራች ኩባንያዎች ባለቤት በሆነው በርናርድ አርኖት ቦታውን መነጠቁ አይዘነጋም።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አምራቹ ቴስላ የአክሲዮን ዋጋ በተጠናቀቀው የፈረንጆች ዓመት በ65 በመቶ የወደቀ ሲሆን፣ የዚህም ምክንያቱ ኩባንያው የተጠበቀውን ያህል ተሽከርካሪዎችን ባለማምረቱ ነው።
ይህን ተከትሎም መስክ ትዊተርን ከፍተኛ በሚባል ወጪ ከገዛ በኋላ የማኅበራዊው ሚዲያ በርካታ ሠራተኞችን በማሰናበት እና ትዊተር ላይ የሚደረገውን የይዘት ቁጥጥር ፖሊሲ በመቀየሩ ውዝግብ አጋጥሞታል።
ይህ ሁኔታም የድርጅቱ የአክሲዮን ዋጋ እንዲያሽቆለቁል ምክንያት እንደሆነ ይነገራል።
በቴስላ ውስጥ ድርሻ ያላቸው ባለሀብቶች መስክ ከማኅበራዊ ሚዲያው ይልቅ በኤሌክትሪክ መኪና ምርቱ ላይ ቢያተኩር የገበያ መዳከሙን፣ ያለውን ፉክክር እና ኮሮና ያስከተለውን ተግዳሮት ለመቋቋም ይቻላል ብለዋል።












